ኢትዮጵያውያን ዓለምአቀፍ ዳኞች ነገ ታንዛኒያ ላይ የሚደረገውን የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታ እንዲመሩ ተመርጠዋል።
የ2022/23 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ የማጣሪያ ጨዋታዎች መደረግ ከጀመሩ ሦስት ወራት ተቆጥሯል። የአራተኛ ዙር የምድብ ጨዋታዎች መደረግ የጀመሩ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ ሁለት ክለቦችን በያዘው ምድብ ሦስት ስር ተደልድለው የሚገኙትን የዩጋንዳው ቫይፐርስ እና የታንዛኒያው ሲምባ ክለብ የፊታችን ማክሰኞ በቤንጃሚን ሞካፖ ስታዲየም አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ የሚያደርጉትን ጨዋታ አራት ኢትዮጵያዊያን አለም አቀፍ ዳኞች እንዲመሩት በካፍ ስለ መመረጣቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ከቀናቶች በፊት ግብፅ ላይ አልሀሊ እና ማሜሎ ዲ ሰንዳውንስ ያደረጉት ጨዋታ መርተው የነበሩት ሦስቱ ዳኞች ማለትም በአምላክ ተሰማ በመሀል ዳኝነት ትግል ግዛው እና ተመስገን ሳሙኤል በረዳት ዳኝነት በድጋሚ ይህን ጨዋታ እንዲመሩ ሲመረጡ አብሯቸው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ በላይ ታደሰ አራተኛ ዳኛ በመሆን ለጨዋታው ተመድበዋል።
በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ቫይፐርስ በሜዳው ሴንት ሜሪ ስታዲየም ላይ ሲሞባን 1-0 የተረታ ሲሆን ምድቡን የሞሮኮው ራጃ ካዛብላንካ በዘጠኝ ነጥብ ሲመራው የጊኒው ሆሮያ በአራት ሲምባ በሦስት እና ቫይፐርስ በአንድ ነጥብ ተቀምጠዋል።