ሪፖርት| ኃይቆቹ ከሦስት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል

ሀዋሳ ከተማ በተከላካዩ ብቸኛ ግብ ለገጣፎ ለገዳዲን አሸንፏል።

አዳዲስ ያስፈረምኳቸውን ተጫዋቾች ማሰለፍ ይገባኛል በሚል ውዝግብ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታውን አለማድረጉን ተከትሎ ለመቻል የፎርፌ ውጤትን ያስረከበው ለገጣፎ ለገዳዲ በ14ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና ሲረታ ከተጠቀመው ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አዳዲስ ካስፈረማቸው ስምንት ተጫዋቾች መካከል በዛሬው ጨዋታ ሰባቱን ማካተት ችሏል። በዚህም ኮፊ ሜንሳህ ፣ ተስፋዬ ነጋሽ ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ ዘነበ ከድር ፣ ያሬድ ሀሰን ፣ ሱራፌል ዐወል እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እንዲሁም ነባሮቹን ተፈራ አንለይ ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ጋብሬል አህመድን በማካተት ለጨዋታው ሲቀርቡ ሀዋሳ ከአርባምንጩ ጨዋታ አቤኔዘር ኦቴ እና አብዱልባሲጥ ከማልን በማሳረፍ በረከት ሳሙኤል እና ተባረክ ሄፋሞን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።

\"\"

10፡00 ሰዓት ሲል በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አጀማመሩ ለገጣፎ ለገዳዲዎች ባደረጉት ፈጣን የመልሶ ማጥቃት የመስመር አጨዋወት ይጀምር እንጂ በሒደት ግን አሰልቺ ይዘትን የተላበሰ እና ከሙከራዎች ቁጥብ የሆነን አጋማሽ ያስመለከተን ሆኗል። ያልተረጋጉ እንቅስቃሴዎች የተበራከቱበት ፣ የሚቆራረጡ እንዲሁም አሰልቺ ይዘቶችን አቅፎ ከሙከራ ድርቅ ረጅሙን ደቂቃ ባሳለፈው በዚህ ጨዋታ ወደ ራሳቸው ቁጥጥር ስር በማድረግ በሁለቱ ኮሪደሮች በኩል ረጃጅም ኳስን በመጣል ለገጣፎ ለገዳዲዎች ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም እንቅስቃሴያቸው ወጥነት የጎደለው በመሆኑ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ደርሰው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራን ለማድረግ ግን የሀዋሳን የኋላ ግድግዳ ለማለፍ አልታደሉም።

በአንፃሩ የትኩረት ማዕከላቸው ሙጂብ ቃሲም ላይ አድርገው ለመጫወት መታተር ውስጥ ቢገቡም ልዩነት ለመፍጠር ብዙም ያልነበሩት ሀዋሳዎች ከቆመ ኳስ ያገኟትን ብቸኛ አጋጣሚ ወደ ጎልነት ለውጠው መሪ ሆነዋል። 43ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ላይ ከቀኝ የለገጣፎ ሜዳ አካባቢ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት እዮብ አለማየሁ በረጅሙ ወደ ግብ ክልል ሲያሻማ ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል የጋናዊው ግብ ጠባቂ ኮፊ ሜንሳህ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ሀዋሳን መሪ አድርጓል። ለዕይታ ሳቢነቱ በእጅጉ የተቀዛቀዘው የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽም በሀዋሳ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴዎቹ ብዙም ያልተቀየረው ሁለተኛው አጋማሽ ቀጥሎ ከኳስ ቁጥጥሮች አንፃር ለገጣፎዎች ተሽለው የታዩበት ሲሆን በተለይ ተሻጋሪ ኳሶችን አጥቂው ካርሎስ ዳምጠውን ዋነኛ የማጥቂያ ምንጫቸው አድርገው ሲንቀሳቀሱ ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው እግራቸው ስር የሚገባውን ኳስ በቶሎ ተጠቅሞ ልዩነቱን ለማስፋት ኤፍሬም እና እዮብን በአሊ ሱለይማን እና አዲሱ አቱላ በመተካት ለማሻሻል ቢሞክሩም ቅያሪያቸው ግን እምብዛም ነበር። በተሻለ ንቃት ወደ ጨዋታ ቅኝት ውስጥ ቀስ በቀስ የገቡት ለገጣፎዎች 63ኛው ደቂቃ ላይ ካርሎስ ዳምጠው ከቀኝ የሜዳው ክፍል የደረሰውን ኳስ ወደ ጎል መቶ ሰለሞን ያወጣበት እና ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሱራፌል ያደረሰውን ካርሎስ በድጋሚ ሞክሮ ሙንታሪ ያዳነበት ይጠቀሳሉ።

የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎችን በጥብቅ መከላከል ውስጥ የተጠመዱትን ሀዋሳ ከተማዎችን ጫና ውስጥ በመክተት ሲጫወቱ የተስተዋሉት ለገጣፎዎች በተለይ ኢብሳ በፍቃዱን እና አማኑኤል አረቦን ወደ ሜዳ ካስገቡ በኋላ ይበልጥ ለሀዋሳ ተከላካዮች የስጋት ምንጭ ሆነው ተስተውሏል። 79ኛው ደቂቃ ኢብሳ የሀዋሳን ተከላካዮች አስፍቶ በቀጥታ ወደ ጎል መቶ ሙንታሪ ሲመልስ አማኑኤል በግንባር የደረሰውን በድጋሚ ሞክሮ ሙንታሪ ከእቅፉ የሾለከችዋን ኳስ ሰይድ ሀሰን ከግቡ መስመር ላይ አውጥቷታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ከሳጥኑ ጠርዝ አማኑኤል አረቦ አክርሮ መቶ ሙንታሪ የያዘበት የጨዋታው መደምደሚያ ደቂቃ ላይ አማኑኤል እና ካርሎስ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ተከላካይ ለውጠው ያስገቡት ሀዋሳዎች ጥብቅ መከላከላቸው ፍሬ አፍርቶ ከሦስት ተከታታይ አቻዎች በኋላ 1ለ0 በመርታት ወሳኝ ሙሉ ነጥብን አሳክተዋል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች ሽንፈት የገጠመው ለገጣፎ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በቡድናቸው ላይ የተወሰኑ መሻሻሎች እንዳሉ ገልፀው የፊት መስመራቸው ላይ በነበረው ድክመት ጎል አለማስቆጠራቸውን በማንሳት ከዕረፍት መልስ ግን ቡድኑ ጥሩ እንደነበር እና የታየውን የአጨራረስ ድክመት በማሻሻል ለማሸነፍ በቀጣይ እንደሚጫወቱ ጠቁመዋል። ድልን ያሳካው ሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ የሆኑት ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው ጨዋታው ሁለት መልክ እንደነበረው ከጠቆሙ በኋላ ሦስት አቻ ውጤትን አስመዝግበው ስለ ነበር ወደ አሸናፊ ለመመለስ ጥንቃቄ ማድረግ ስለ ነበረባቸው ከጎሉ በኋላ ጥንቃቄ በመምረጣቸው በተጋጣሚያቸው ጫና ውስጥ መግባታቸውን በተጫዋቾቻቸው ላይም ፍርዓት መፍጠሩንም ተናግረው ወደ አሸናፊነት ለመምጣት ጭንቀት ውስጥ በጨዋታው ገብተው እንደነበርም በንግግራቸው ገልፀዋል።