ቅድመ ዳሰሳ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ መድን

በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ በተከታታይ የተቀመጡትን ክለቦች የሚያገናኘውን ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

በሁለት ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ብቻ ተለያይተው በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ እና ሁለተኛ ቦታ ላይ የተቀመጡት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ መድን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ትልቅ ተፅዕኖ ሊያመጣ የሚችለውን የእርስ በእርስ ፍልሚያ ነገ ምሽት 1 ሰዓት ያከናውናሉ። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ይህንን ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነ የነጥብ ልዩነቱን ወደ አምስት አስፍተው በጥሩ ሁኔታ የሚደላደሉ ሲሆን ኢትዮጵያ መድኖች ከረቱ ደግሞ በአንድ ነጥብ መሪነቱን የሚረከቡ ይሆናል።

\"\"

የሁለቱ ቡድኖች የዘንድሮ የውድድር ዘመን የመጀመሪያ የእርስ በእርስ ጨዋታ ውጤት በሁለተኛው ዙር ግንኙነት በዚህን ያክል መቀራረብ ይደረጋል ተብሎ እንዲገመት ያስቻለ አልነበረም። በአጠቃላይ ስምንት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታም ጊዮርጊሶች በድምሩ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ያገኙትን ግብ ሸምተው የወጡበት ነበር። ኢትዮጵያ መድኖችም ከታችኛው የሊግ እርከን ባደጉበት የመጀመሪያ ጨዋታ አሰቃቂ የሚባል ሽንፈት አስተናግደው የወጡበት ውጤት ተመዝግቦ ነበር።

ሽንፈት ካስተናገዱ አስር የጨዋታ ሳምንታት ያስቆጠሩት ጊዮርጊሶች ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከተጋጣሚዎቻቸው መጠነኛ ፈተና ቢገጥማቸውም በአንዱ ብቻ አቻ ወጥተው ሁለቱን አሸንፈዋል። በእነዚህ ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ተጋጣሚዎቻቸው እነሱ በሚታወቁበት ቀጥተኛ አጨዋወት እየቀረቡ በመጠኑ እየፈተኗቸው የነበረ ሲሆን ይህንን ባህሪ እየተላመዱ ለአቀራረቡ ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ። ምናልባት የነገ ተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ መድኖች የአጨዋወት ለውጥ ካላደረጉ ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ የሚመርጡ ስለሆነ በአደገኛ ቀጠና ኳሶችን እየነጠቁ በፈጣን እና ቀጥተኛ አጨዋወት የግብ ዕድል ለመፍጠር ሊመቻቸው ይችላል። በዚህ ሂደት ደግሞ የመድን ጠንካራ ጎን የሆነውን የአማካይ መስመር በሚፈልጉት መልኩ እንዲጫወት ካላደረጉት ሊጠቀሙ ይችላሉ። ከዚህ አልፎም በመስመር አጨዋወታቸው እንዲሁም የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እስማኤል ኦሮ-አጎሮን መአከል ያደረጉ ኳሶች በመጠቀም ውጤት ለማግኘት እንደሚንቀሳቀሱ ይታሰባል።

ምንም እንኳን ሽንፈት ባያስተናግዱም ባለፉት ስድስት የጨዋታ ሳምንታት በአንፃራዊነት ወጥ ብቃት እና ውጤት ማሳየት ያልቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች በጠቀስናቸው ጨዋታዎች የአቻ እና የድል ውጤት እያፈራረቁ ይዘው ከሜዳ ወጥተዋል። ቡድኑ በእንቅስቃሴ ረገድም መጠነኛ መንገራገጭ የገጠነው የሚመስል ሲሆን በተለይ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ተጋጣሚው ከ35 ደቂቃዎች በላይ በጎዶሎ ተጫዋች ተጫውቶ የቁጥር ብልጫውን በአስተማማኝ ውጤት አላማሳጀቡ ያነሳነውን ሀሳብ የሚያጠናክር ምክንያት ነው። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ በጠባብ ስብስቡ እዚህ ደረጃ መድረሱ አድናቆት የሚያስቸረው ነው። ከላይ እንደገለፅነው የመድን ዋነኛ ጠንካራ ጎን የአማካይ መስመሩ የጨዋታ ቁጥጥር እና የመስመር ተጫዋቾቹ ፍጥነት ሲሆን በነገውም ወሳኝ ፍልሚያ ይህንን አዎንታዊ ጎን በመጠቀም ጨዋታውን በእጁ ለማስገባት እንደሚጥር ይገመታል። በተቃራኒው ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያዘወትረውን የመስመር አጨዋወት እና የሚልካቸውን ረጃጅም ኳስ መመከት ዋነኛ ትኩረት ሊሰጡ የሚገባው ነጥብ መሆኑ እሙን ነው።

\"\"

በልምምድ ላይ ጉዳት የገጠመው ዳግማዊ አረዓያ ለነገው ጨዋታ መድረሱ አጠራጣሪ ሲሆን በመጨረሻው ጨዋታ ተጎድቶ የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል ልምምድ በሟሟላቱ ለጨዋታው የመድረስ ዕድል እንዳለው ለማወቅ ችለናል። ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው በነገው ጨዋታ ሁለቱን ወሳኝ የመስመር ተከላካዮቻቸውን ያሬድ ካሳዬ እና አብዱልከሪም መሀመድን ግልጋሎት አያገኙም።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 24 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ሲኖራቸው 17 ጊዜ ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ 45 ጎሎች ፣ 2 ጊዜ ያሸነፈው መድን ደግሞ 13 ግቦችን አስቆጥረው አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። ኢትዮጵያ መድን በዚህ ግንኙነት የመጨረሻውን ድል 1996 ላይ ሲያስመዘግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከላይ እንደገለፅነው በዘንድሮ የሊጉ ሦስተኛ ጨዋታ ድል ተቀዳጅቷል።

ወሳኙን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አበራ አብርደው እና ወጋየው አየለ በረዳትነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በአራተኛ ዳኝነት ግልጋሎት እንዲሰጡ ተመድበዋል።