ለአንጋፋው ጋዜጠኛ የመታሰቢያ ዝግጅቶች ሊደረጉ ነው

በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው አንጋፋ የስፖርት ጋዜጠኛ የተለያዩ የመታሰቢያ ፕሮግራሞች ሊዘጋጁ መሆኑ ታውቋል።

በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ በተለይ በእግር ኳሱ ረጅሙን የህይወት ዘመኑን ያሳለፈው እንዲሁም ለቀጣዩ ትውልድ መረጃዎችን ከትቦ በማቅረብ በብዙሀኑ ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈው እና በቅርቡ በድንገት ህይወቱ ያለፈው አንጋፋ የስፖርት ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በተለያዩ ስነ ስርዓቶች የመታሰቢያ ዝግጅቶች ሊደረግለት ስለመሆኑ ከአዘጋጅ ኮሚቴዎቹ የደረሰን መረጃ ያሳያል።

\"\"

ከኮሚቴው መሀል አንዱ የሆነው የጋዜጠኛው የቅርብ ወዳጅ አሰልጣኝ ብዙዓየው ዋዳ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደተናገሩት ከሆነ የቀድሞው አንጋፋ የእግር ኳስ ዳኛ ጌታቸው ገብረማርያም እና አሰልጣኝ ወርቁ ደርገባን የመሳሳሉ አንጋፋ ባለሙያዎችን ያቀፈ በስሩም በርካታ የእግር ኳሱ ሰዎችን ያካተተ የኮሚቴ መዋቅር ያሉት ስብስብ መቋቋሙን ገልፀው ጋዜጠኛውን ለማሰብም ሦስት መርሀግብሮችን በዋናነት ለመከወን እንደታሰበ እና ከዝግጅቱ የሚገኙትን ገቢዎች ቤተሰቡን ለመርዳትም ጭምር ያለመ መሰናዶ እንደሆነ ተናግርዋል።

በቀጣዩ ወርሀ መጋቢት 2 ህልፈቱ ከተሰማ አርባ ቀናቶች የሚሞሉት አንጋፋው ጋዜጠኛ ቀኑን ምክንያት በማድረግ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና የተስፋ ቡድኖች መካከል ጨዋታ የሚደረግ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በየዓመቱ የማይቋረጥ ከሀያ በላይ የጤና ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር በስሙ እንደተዘጋጀ እና በአሁኑ ሰዓትም ምዝገባ እየተደረገ መሆኑን የገለፁልን ሲሆን በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በፕሪምየር ሊጉ ፣ በከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊጉ አልፎም የሴት ቡድን እርሱ በህይወት እያለ ቃለ-መጠይቅ ያደረገላቸው ተጫዋቾችን የያዘ ውድድርንም በዓመቱ መገባደጃ ላይ ለማዘጋጀት ወደ ስራ ስለ መገባቱ ጨምረው የኮሚቴው አባል ነግረውናል።

\"\"

ያለፉትን ሰላሳ ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በትጋት በመዘገብ አንቱታን ያተረፈው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በመታሰቢያ ውድድሩም ሆነ ከስፖንሰሮች የሚገኘው ገቢ በስሩ ያስተዳድራቸው ለነበሩ ሁለት ታናናሽ ወንድሞቹ እንደሚውል ታውቋል።