ሲዳማ ቡና በተጫዋች ተገቢነት ጉዳይ ፎርፌ ሊተላለፍበት ይችላል

በትናንትናው ዕለት በድሬደዋ ከተማ ሽንፈት ያስተናገድው ሲዳማ ቡና በተጫዋች ተገቢነት ጉዳይ ፎርፌ ሊሰጥበት እንደሚችል ተሰምቷል።

\"\"

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአስራ ስድስተኛ ሳምንት የትናንት የድሬደዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በባለ ሜዳዎቹ ድሬደዋ ከተማዎች ሁለት ለምንም አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። ታዲያ በዚህ ጨዋታ ላይ ሲዳማ ቡናዎች ከተቀመጠው ደንብ ውጭ በአረንጓዴ መታወቂያ አራት ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባታቸው ፎርፌ ሊሰጥባቸው እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

\"\"

በጨዋታው ሲዳማዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉዓለም መስፍንን በሙሉቀን አዲሱን፣ 46ኛው ደቂቃ ላይ አቤል እንዳለን በቴዎድሮስ ታፈሰን እንዲሁም በ55ኛው ደቂቃ ላይ ቡልቻ ሹራን በይስቅ ካኖ እና ፀጋዬ አበራን በሳላዲን ሰዒድ ቀይረው ነበር። ይህን ተከትሎ አንድ ቡድን በአንድ ጨዋታ ላይ ሦስት በአረንጓዴ ሁለት በቢጫ መታወቂያ የተጫዋች ቅያሪን መጠቀም አለበት የሚለውን ደንብ በመተላለፍ አራት ተጫዋቾችን በአረንጓዴ መታወቂያ አስገብተዋል። በዚህም አወዳዳሪው አካል የተቀመጠው ደንብ ሲዳማ ቡናዎች በመተላለፋቸው ምንም እንኳን ድሬደዋ ጨዋታውን አሸንፈው የወጡ ቢሆንም በደንቡ መሠረት ለብርትካናማዎቹ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ንፁህ ጎሎችን እንደሚሰጥ ተጠቁሟል። ይህንን ተከትሎ ድሬዳዋ ትናንት ካገኘው ሁለት ጎሎች አንድ ተጨማሪ ጎል የሚያገኝ ይሆናል።