ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ ከመመራት ተነስተው ድል አድርገዋል

ባህር ዳር ከተማ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ሦስት ጎሎች ከመመራት ተነስቶ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3-1 ረቷል።

ባህር ዳሮች ከወላይታ ድቻ ጋር ያለ ጎል ባጠናቀቁበት ወቅት ከተጠቀሙት አሰላለፍ መካከል በሁለቱ ላይ ለውጥን አድርገዋል። በዚህም በተስፋዬ ታምራት እና ፋሲል አስማማው ፈቱዲን ጀማል እና ሀብታሙ ታደሰን ሲተኩ በሲዳማ ቡና ሽንፈት የገጠማቸው ኤሌክትሪኮች የ7 ተጫዋቾች ቅያሪ ሲያደርጉ ሦስቱ አዳዲስ ፈራሚዎች ነበሩ። ታፈሰ ሰርካ ፣ ማታይ ሉል ፣ አማረ በቀለ ፣ ነፃነት ገብረመድህን ፣ ፀጋ ደርቤ ፣ ናትናኤል ሰለሞን እና አብዱራህማን ሙባረክን በዛሬው አሰላለፍ ውስጥ ተካተዋል።

\"\"

ቀዝቀዝ ባለ የእንቅስቃሴ ይዘት ጅምሩን ያደረገው የሁለቱ ቡድኖች የ10፡00 ሰዓቱ ጨዋታ ከፉክክር አንፃር የተገደበ በተጨማሪም ያልተሳኩ ተሻጋሪ ኳሶች በርክተው ያየንበት ነበር። በመስመር ላይ ባጋደለ አጨዋወት በተመሳሳይ ቅርፅ ቡድኖቹ ለመጫወት ቢተጉም የማጥቂያ መንገዳቸው ወጥ ካለመሆኑ አኳያ ልዩነቶችን በነፃነት ፈጥረው እንዳንመለከት ጋርዶናል። 6ኛው ደቂቃ ላይ ባህር ዳሮች በፍፁም ጥላሁን አማካኝነት ጎል ቢያስቆጥሩም አወዛጋቢ በሆነ የረዳት ዳኛው ሻረው ጌታቸው ውሳኔ ከጨዋታ ውጪ መቧሏ የጨዋታው ደቂቃ ብዙም ሳይጓዝ ያስተዋልናት አስገራሚ ክስተት ነበረች። በሁለቱ ኮሪደሮች በኩል ኳስን በሚያገኙበት ወቅት ፀጋ እና አብዱራህማንን ተጠቅመው ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ የሚጥሩት ኤሌክትሪኮች ሁለት ያልተሳኩ ሙከራዎችን በሁለት ደቂቃ ልዩነት ፈጥረው ታይተዋል።

10ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋ ደርቤ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ሲመታ ታፔ አልዛየር በቀላሉ የተቆጣጠራት እና ከሁለት ደቂቃ በኋላ አብዱራህማን የግል ጥረቱን ተጠቅሞ የሰጠውን ስንታየው ወደ ግብ ሞክሮ ታፔ ዳግም የመለሳት የቡድኑ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ። ጥራት ያላቸውን አጋጣሚዎች እምብዛም ያላስመለከተን ፣ እንቅስቃሴዎች ብቻ ጎልተው መታየት የቻሉበት ይህ አጋማሽ ከ25 ደቂቃዎች በኋላ በይበልጥ ወደ ቀኝ የሜዳው ክፍል ለመጫወት ባህር ዳሮች መሞከራቸው በተወሰነ መልኩ የኳስ ቁጥጥሩን ወደ ራሳቸው እንዲያደርጉ አስችሏቸው ተስተውሏል። 

\"\"

14ኛው ደቂቃ ላይም ከተጠቀሰው የሜዳ ክፍል መሳይ ወደ ውስጥ ሰብሮ የሰጠውን ፍፁም ጥላሁን በግራ እግሩ አክርሮ መትቶ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰበት ጠንካራዋ የቡድኑ ሙከራ ሆናለች። ጨዋታው ሊገባደድ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩ የኤሌክትሪኩ ፀጋ በግንባሩ ጨርፎ የሰጠውን ከርቀት ስንታየው መቶ ታፔ ከመለሰበት በኋላ ከፉክክሮች አንፃር ብዙም ወጥነቶች የተሳነው የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ጎል ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ ብዙም ሳይጓዝ ኳስ እና መረብ ተዋህደዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ቀኝ መስመር በኩል የደረሰችውን ኳስ ጌቱ ኃይለማርያም ወደ ሳጥን ውስጥ ሲያሻማ ከባህርዳር ተከላካዮች ተነጥሎ ነፃ ቦታ ላይ የነበረው አብነት ደምሴ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ባልተሻሻሉ እና በሚቆራረጡ እንቅስቃሴዎች ጨዋታው ቢቀጥልም ጎል ማስተናገዳቸው ያነቃቸው ባህር ዳሮች ኳስን በመቆጣጠሩ እና ጫናዎችን በማሳደሩ ረገድ ሻል ያሉ ሆነዋል። ፈቱዲን ባደረጋት የርቀት ሙከራ ማድረግ የጀመረው ቡድኑ 61ኛው ደቂቃ ላይም ፈቱዲን በረጅሙ ሲያሻግር ዱሬሳ በሚገርም ቅልበሳ በቀኙ ሲመታ ዘሪሁን በሚገርም ቅልጥፍና ኳሷን አውጥቷታል። ኤሌክትሪኮች ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውን የጠቀማቸው የጣና ሞገደኞቹ አማካይ ክፍሉን መነሻ ለማድረግ በማሰብ ቻርልስን በአብስራ ከለወጡ በኋላ ይበልጥ ተነቃቅተዋል።

66ኛው ደቂቃ ላይ ኤሌክትሪኮች በግቡ ትይዩ ሳጥን ጠርዝ አብነት ደምሴ ተቀይሮ የገባው አብስራ ተስፋዬ ላይ ጥፋት በመስራቱ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ በቀይ ወጥቷል። በጥፋቱ የተገኘችውን የቅጣት ምት ፉዓድ አክርሮ ሲመታ የላይኛው አግዳሚ ብረትን ጨርፋ ወደ ውጪ ወጥታለች። 

ተጨማሪ የተጫዋች ለውጥን ካደረጉ በኋላ በሀብታሙ ታደሰ አስቆጪ ሙከራን ካደረጉ ሁለት ደቂቃ እንደ ተቆጠረ ፣ 83ኛ ደቂቃ መሳይ ከማዕዘን ምት አሻምቶ ሀብታሙ ውስጥ አሻምቶ ፍፁም ጨረፍ ካደረጋት በኋላ ፉአድ ዘሪሁን መረብ ላይ አሳርፏታል።

የኤሌክትሪክን አጥር ቶሎ ቶሎ ያስከፍቱ የነበሩት ባህር ዳሮች ከተመሪነት ወደ መሪነት መጥተዋል 87ኛ ደቂቃ ከቀኝ መስመር በረጅሙ የደረሰውን ሀብታሙ ታደሰ በቀላሉ አስቆጥሯል። በጭማሪ ደቂቃ ደግሞ ራሱ ሀብታሙ ለቡድኑ ሦስተኛ ለራሱ ሁለተኛ ጎል አክሎ ጨዋታው 3-1 የባህር ዳር አሸናፊነት ተፈፅሟል።

የኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ በጨዋታው የተሻሉ እንደነበሩ ጠቁመው ከጨዋታ ውጪ የተባለች እና አግባብ ባልሆነ መልኩ አብነት ያገኘው ቀይ ካርድ ተፅዕኖ በቡድናቸው እንደፈጠረባቸው በሁለቱ ምክንያቶችም በተፈጠረው የሥነ ልቦና ክፍተት ውጤት እንዳጡ ከቀዩ በኋላም አጨዋወታቸውን ለመቀየር አስበው ያሰቡትን መፈፀም እንዳልቻሉ ጭምር ተናግረዋል። የባህር ዳር አቻቸው ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው የሥነ ልቦና ጥንካሬ በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ በቡድናቸው ባለመኖሩ ወደ ጨዋታ ለመግባት መቸገራቸውን ጠቅሰው በሁለተኛው አጋማሽ ለመቅረፍ ባደረጉት ጥረት ውጤት ማግኘታቸውን እንደሚገባቸው እና ከቀዩ በኋላ አድቫንቴጁን ተጠቅመው ማሸነፋቸውን ገልፀው ውጤቱም ለክለቡ ደጋፊዎች ይገባቸዋል በማለት ሀሳባቸውን አገባደዋል።