ሪፖርት | በይደር የቆየው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል

ጥሩ ፉክክር ያስተናገደው የአርባምንጭ ከተማ እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ 2-2 ተቋጭቷል።

አርባምንጭ ከተማ ከሀዋሳ ከተማው የአቻ ውጤት አንፃር ባደረገው የአሰላለፍ ለውጥ አበበ ጥላሁን ፣ ሱራፌል ዳንኤል እና አላዛር መምሩ በወርቅይታደስ አበበ ፣ ሙና በቀለ እና መላኩ ኤልያስ ቦታ ገብተዋል።

\"\"

በደመወዝ ጉዳይ ከልምምድ ርቀው በሰነበቱት ወልቂጤዎች በኩል በአዳማው ሽንፈት የተሰለፉት ፋሲል አበባየሁ ፣ አስራት መገርሳ ፣ ብዙአየሁ ሰይፈ እና አቡበከር ሳኒ በብርሀኑ ቦጋለ ፣ አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ እና አፈወርቅ ኃይሉ ተተክተዋል።

በዝናብ ምክንያት ለዛሬ የተዘዋወረው ጨዋታ ሲጀምር አዞዎቹ ከወትሮው በተሻለ የኳስ ምስረታ አህመድ ሁሴንን መዳረሻ ባደረጉ ጥቃቶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ ጀምረዋል። ሂደቱ ቀጥሎ ምልክት ሲሰጥ የነበረው የቡድኑ ጥቃት 12ኛ ደቂቃ ላይ ግብ ፈጥሯል። ከአርባምንጭ ሜዳ በረጅሙ የተላከን ኳስ ተመስገን ደረሰ እና አህመድ ሁሴን ተቀባብለውት አህመድ ጀማል ጣሰውን በማለፍ የመጀመሪያ ግብ አድርጎታል።

\"\"

ከግቡ በኋላ ወልቂጤዎች የተሻለ ኳስ መስርተው የመውጣት አዝማሚያ ማሳየት ቢጀምሩም ሰብረው መግባት ቸግሯቸዋል። ይልቁኑም ፈጣን ጥቃታቸው የቀጠለው አርባምንጮች ከቆሙ ኳሶች ዕድል ፈጥረዋል። 17ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ደረሰ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ሲወጣ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሱራፌል ዳንኤል ከሌላ ቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ አሸናፊ ፊዳ በግንባር ለመጭረፍ ሞክሮ ጀማል ጣሰው አድኖበታል።

በቀሪው የአጋማሹ ደቂቃዎች የጨዋታው ፉክክር በአመዛኙ በሁለቱ ሳጥኖች መካከል ተገድቧል። አርባምንጮች 36ኛ ደቂቃ ላይ እንዳልካቸው መስፍን በግንባር ካደረገው ሙከራ ውጪ እንደቀደመው ደጋግመው ወደ ሳጥን አልገቡም። 

\"\"

በሦስት አጋጣሚዎች በአዞዎቹ የኋላ መስመር ስህተቶች ዕድሎችን አግኝተው የነበሩት ሰራተኞቹም አጋጣሚዎቹን ወደ ሙከራነት መቀየር አልቻሉም። ቡድኑ ወደ አጋማሹ ማብቂያ ላይ የተሻለ ጫና ቢፈጥርም ለግብ ይቀረበ ሙከራ ሳያደርግ ጨዋታው ተጋምሷል።

ሰራተኞቹ ሁለተኛውን አጋማሽ ካቋረጡበት ቀጥለው የተነቃቃ ጫና ፈጥረዋል። 51ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ መላኩ ከረጅም ርቀት በጠንካራ ምት መኮንን መርዶኪዎስን የፈተነ ሲሆን የቡድኑ ለአርባምንጭ ሳጥን የቀረበ እንቅስቃሴ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ጎል አስገኝቷል።

\"\"

አሸናፊ ፊዳ በሳጥኑ መግቢያ ላይ የነበረው የወልቂጤዎችን ቅብብል ለማቋረጥ ሞክሮ ኳስ ወደ ጌታነህ ከበደ ያመራች ሲሆን የወልቂጤው አምበል በቀጥታ አክርሮ በመምታት አስቆጥሮታል። ከአስር ደቂቃ በኋላ ደግሞ የአርባምንጭ ከተማ የኋላ ክፍል ትኩረቱን ባጣበት ቅፅበት ተስፋዬ መላኩ ከጀርባቸው የጣለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አቤል ነጋሽ ሁለተኛ ግብ አድርጎ ወልቂጤን ወደ መሪነት አምጥቷል።

\"\"

በቀሪ ደቂቃዎች ውጤት የተገለበጠባቸው አርባምንጮች ራሳቸውን ወደ ማጥቃት መንፈስ ለማስገባት ጥረዋል። በተለይም 80ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን 81ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተመስገን ደረሰ ከርቀት ያደረጋቸው ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ቢሆንም በጀማል ጥረት ድነዋል። ለአርባምንጮች ጫና ከማፈግፈግ ይልቅ መልሶ ማጥቃትን የመረጡት ወልቂጤዎች ጨዋታውን ለመግደል ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ይልቁኑም ግብ አስተናግደዋል። ተቀይሮ ከገባው ቡጣቃ ሸመና የተሻገረውን ኳስ ተመስገን በጨዋታው ለሁለተኛ ጊዜ ሲያመቻች ሌላኛው ተቀያሪ ኤሪክ ካፓይቶ አዞዎቹን ነጥብ ያጋራች ግብ አስቆጥሯል። ጥሩ ፉክክር ያስመለከተን ጨዋታም በዚሁ በ2-2 ውጤት ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የቡድናቸው ትኩረት ማጣት በሁለተኛው አጋማሽ መስተካከሉን አንስተው ከልምምድ መራቅ በመጨረሻ የትኩረት ደረጃቸውን እንዳወረደው የጠቆሙ ሲሆን \’አሁን ላይ ቁጥር አንድ አጥቂ ነው\’ ያሉት ጌታነህ ከበደን አሞካሽተዋል። አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እና ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩበትን መንገድ ማሻሻል እንዳለባቸው አብራርተዋል።