ሊግ ካምፓኒው የፎርፌ ውሳኔ አስተላልፏል

በ16ኛው ሳምንት የተደረጉ ጨዋታዎችን ተከትሎ የሊጉ አወዳዳሪ አካል ባስተላለፋቸው ውሳኔዎች ሱራፌል ዳኛቸው እንዲሁም የሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ቡድን አባላት ጠንከር ያለ ቅጣት አግኝቷቸዋል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና እና ስነ ሥርዐት ኮሚቴ በያዝነው ሳምንት ተደርገው በተጠናቀቀቁ የ16ኛ ሳምንት የፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ ግድፈት በታየባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የቅጣት ውሳኔን ሲያስተላልፍ የፋሲል ከነማው አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው እና የሲዳማ ቡናው ረዳት አሰልጣኝ ቾንቤ ገብረህይወት የቅጣት ሰለባ ሆነዋል።

\"\"

አዳማ ከተማ ፋሲልን 2-1 በረታበት ጨዋታ የፋሲሉ አማካይ ሱራፌል ዳኛቸው ተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ የዕለቱን ዳኛ ተፈሪ አለባቸውን አፀያፊ ስድብ በመሳድቡ ቀይ ካርድ አይቶ የነበረ በመሆኑ ሦስት ጨዋታዎችን እንዲታገድ እና ሦስት ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኗል። በሌላ የቅጣት ዜና የወላይታ ድቻው ቡድን መሪ ዘላለም ማቲዮስ ክለቡ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው የዳኛን ውሳኔ በመቃወም ከጨዋታ በቀይ የተወገደ በመሆኑ አንድ ጨዋታ እንዲታገድ እና ስድስት ሺ ብር እንዲከፍል ተወስኖበታል።

ሲዳማ ቡና በድሬዳዋ 2ለ0 ሲረታ ከተፈቀደው ደንብ ውጪ ሲዳማዎች በአረንጓዴ ቲሴራ የተመዘገቡትን አራት ተጫዋቾችን ቀይረው ስለማስገባታቸው ከዳኞች ሪፖርት ተረጋግጦ በክለቡ ላይ የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ተላልፈውበታል።

\"\"

በመሆኑም ሲዳማ ቡና ለፈፀመው ጥፋት በፕሪምየር ሊጉ የውድድር ደንብ መሰረት ምንም እንኳ ጨዋታው በድሬዳዋ 2-0 አሸናፊነት ቢጠናቀቅም የዕለቱ ውጤት ተሰርዞ በፎርፌ ሲዳማ ተሸናፊ እንዲሆን ለክለቡ ዜሮ ነጥብ እና ሦስት የግብ ዕዳ እንዲሁም ለተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ተጨማሪ ግብ እንዲመዘገብ ፣ በዕለቱ የተመዘገቡት ጎል አግቢዎችም እንዲሰረዙ ፣ በዕለቱ የተመዘገቡት የዲሲፕሊን ውሳኔዎች እንዲፀኑና የቡድን መሪ እና ምክትል አሰልጣኝ የሆኑት ቾምቤ ገብረ ህይወት ለ6ወር እንዲታገዱ እንዲሁም ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር ሀያ አምስት ሺህ እንዲከፍሉ ተወስኗል፡፡