መረጃዎች | 67ኛ የጨዋታ ቀን

በ17ኛው ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የሚደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና

17ኛው የጨዋታ ሳምንት ከፕሪምየር ሊጉ ጅማሮ አንስቶ በሊጉ ያለመቋረጥ እየተሳተፉ የሚገኙትን ሁለት ቡድኖች የሚያገናኝ ይሆናል። በሀዋሳ ብልጫ በመካከላቸው የሦስት ነጥብ ልዩነት ላይ ሆነው የተገናኙት ቡና እና ሀዋሳ 30 እና ከዛ በላይ ነጥብ ከሰበሰቡት ሦስት የሊጉ ቡድኖች ላለመራቅ ከፍ ያለ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ቡና ከአራት ተከታታይ አቻዎች በኋላ ለዚህ ጨዋታ ደርሷል። ዘንድሮ በርከት ያለ ዝውውሮችን ፈፅሞ ወደ ውድድር የገባው ቡና አሁንም የሚፈልገው የውህደት ደረጃ ላይ ለመድረስ እየተቸገረ ይገኛል። አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በተከታታይ ጨዋታዎች ወጥ የመጀመሪያ አሰላለፍ በመጠቀም ውህደቱን ለማምጣት ያሰቡ ይመስላሉ። ሆኖም መስፍን ታፈሰ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ በመሆኑ በሀዋሳው ጨዋታ አንድ ቅያሪ ለማድረግ መገደዳቸው አይቀርም። ቡድኑ በድቻው ጨዋታም ፈጣን ሽግግርን ቀላቅሎ ተገማችነቱን ቀንሶ ቢታይም ይበልጥ የተሻለ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የሚያስችል ተከታታይ ጫናን መፍጠር የነገ የቤት ሥራው ይመስላል። ኢትዮጵያ ቡና ከመስፍን ውጪ ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሰነበተው አስራት ቱንጆን ከማጣቱ በቀር ቀሪ ስብስቡ ለጨዋታው ዝግጁ ነው።

\"\"

ሀዋሳ ከተማ እንደነገ ተጋጣሚው ሁሉ ተከታታይ አቻ ሲያስመዘግብ ቢቆይም በመጨረሻ ለገጣፎ ለገዳዲን መርታት ችሏል። እንደአሰልጣኝ ዘርዓይ ገለፃ በአቻ ውስጥ መቆየቱ የፈጠረበት ጫና በመጨረሻ ደቂቃዎች በገጣፎ ለገዳዲን በጥልቀት በመከላከል ለመቋቋም እንዲገደድ አድርጎት ታይቷል። ሁኔታው በነገው ጨዋታም የሚደገም ከሆነ ግን ይበልጥ እንዳይፈተን ያሰጋዋል። ሀዋሳ ወደ ድል ይመለስ እንጂ በተከላካይ መስመር ተጫዋች ግብ ማስቆጠሩ በበጎው ካልተወሰደ በቀር እንደ አቻዎቹ ጨዋታዎች እና ከዚያ ቀደም እንደነበረው የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ ሁሉ ከአንድ በላይ ግብ አለማስቆጠሩ እንደድክመት ይነሳል። ሀዋሳ ከተማ በነገው ጨዋታ ወንድማገኝ ኃይሉ እና ብርሀኑ አሻሞን በጉዳት ሲያጣ ዳንኤል ደርቤ ከግል ጉዳዩ መልስ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 48ኛ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ 16 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 15 ድሎችን ሲያስመዘግቡ 16 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ቡና 56 ሀዋሳ ደግሞ 50 ግቦችን አስመዝግበዋል።

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በዋና ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አበራ አብርደው እና ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ጨዋታ የሚመራው እያሱ ካሳሁን በረዳትነት ፣ ተፈሪ አለባቸው በአራተኛ ዳኝነት እንዲመሩት ተመድበዋል።

ሲዳማ ቡና ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ሽንፈት የገጠማቸው ሀዲያ ሆሳዕና እና ሲዳማ ቡና ነገ ምሽት ከውድድሩ መቋረጥ በፊት እጅግ አስፈላጊያቸው የሆኑ ሦስት ነጥቦችን ለማግኘት ይገናኛሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና በደካማ ወቅታዊ አቋም ውስጥ ይገኛል። በሊጉ ከገጠሙት አጠቃላይ አምስት ሽንፈቶች ሦስቱን በተከታታይ የመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች አስመዝግቧል። ከዚህም ባለፈ ቡድኑ በመጨረሻው የመቻል ጨዋታ ካስቆጠራት ግብ ውጪ ከዚያ ቀደም በነበሩት አምስት ጨዋታዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኖት ቆይቷል። ይህንንም ተከትሎ ለሊጉ መሪዎች ቀርቦ ከነበረበት አሁን ላይ የሰንጠረዡን አጋማሽ ተሻግሮ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በመሆኑም ቡድኑ እያሳለፈ ካለው ደካማ የውድድር ጊዜ አንፃር የነገው ጨዋታ ውጤት አብዝቶ ያስፈልገዋል።

\"\"

ሲዳማ ቡና ሁሉንም ጥሩ ነገሮቹን ያጣበትን የድሬዳዋ ከተማን ጨዋታ ለመርሳት ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በወራጅ ቀጠና ውስጥ ያሉት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ለገጠፎ ለገዳዲን በመርታት ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰው የነበሩት ሲዳማዎች በድሬው ጨዋታ በተለይም ተሻሽለው የታዩበት የመስመሮች ጥቃት እና የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው መናበብ መደገም ሳይችል ቀርቷል። ከዚህም በላይ በተጫዋች ተገቢነት ምክንያት ጨዋታውን በሦስት ጎል ዕዳ በፎርፌ ለማጣት ተገዷል። ከወትሮው ጠንካራ ተፎካካሪነቱ ወርዶ ከወራጅ ቀጠናው አንድ ነጥብ ርቀት ላይ የሚገኘው ሲዳማ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከአስጊው ዞን ፈቀቅ ያደርገዋል።

በነገው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ቤዛ መድህንን በጉዳት ሲያጣ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ አዲስ ያስፈረመው ፊልፕ አጃህ የወረቀት ሥራው ባለመጠናቀቁ ለጨዋታው መድረሱ አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ሰባት ጨዋታዎች አድርገዋል። ሁለቴ ነጥብ ሲጋሩ 14 ግቦች ያሉት ሀዲያ ሆሳዕና ሦስት ፣ 8 ግቦች ያሉት ሲዳማ ቡና ደግሞ ሁለት ድሎችን አስመዝግበዋል።

ይህንን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሀል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ሸዋንግዛው ይልማ በረዳትነት ፣ ዳንኤል ግርማይ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ለመምራት ኃላፉነት ተሰጥቷቸዋል።