የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን አከናውኗል

ከተመሠረተ ሁለተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።

\"\"

ተጠሪነታቸውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ካደረጉ የክልል ፌዴሬሽኖች መካከል አንዱ የሆነው እና ከተመሠረተ የሁለት ዓመት ዕድሜ ላይ ብቻ የሚገኘው የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን በትናንትናው ዕለት በሀዋሳ ሮሪ ሆቴል አከናውኗል። በጉባኤው ላይ የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም እንዲሁም ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃጎ አገኘው ፣ አቶ ሸረፋ ደልቾ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ስራ አስፈፃሚ እና የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ ፣ የክልሉ ስፖርት ኮሚሽነር ፍሬው አሬራ እና የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አንበሴ አበበን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የጉባኤው አባላት ተገኝተዋል።

ረፋድ 3 ሰዓት ሲል ጉባኤውን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያስጀመሩ ሲሆን በመቀጠል የባህል እና ቱሪዝም ቢሮው ሀላፊ አቶ ጃጎ እና የስፖርት ኮሚሽነር ፍሬው በቅደም ተከተላቸው ንግግርን አድርገዋል። አስከትሎም የፌድሬሽኑ የፅህፈት ቤት ሀላፊ የነበሩት እና የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አቶ አቡሽ አሰፋ በፌድሬሽኑ ያለፈውን ዓመት የተሰሩ ስራዎችን ጠንካራውን እና የነበሩ ተግዳሮቶችን ለታዳሚው በዝርዝር ያብራሩ ሲሆን በንግግራቸውም በተቋቋመ አጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ውድድሮችን አልፎም የእግር ኳስ መሠረት ልማቶችን የታዳጊ ፕሮጀክት ድጋፎችን በወጥነት ፌዴሬሽኑ እየሰራ እንዳሳለፈ እና ለዚህም ግብ መሳካት በዋናነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን እና የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ከፌዴሬሽኑ ጎን ሆነው በቁሳቁስ እና በገንዘብ መደገፋቸውን ስራዎችን በንቃት መስራት እንዲችሉ እንደረዳቸው አቶ አቡሽ በዝርዝር በገለፃቸው ጠቁመዋል።

\"\"

ፌዴሬሽኑ አሁን እየሰራ ካለው ስራ በበለጠ ለመስራት እንዲያስችለው በርካታ ውጥኖችን ይዞ እንዳለ ገልፀው በቀጣይም በክልሉም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሆነ የእግር ኳስ ልማቶችን እንዲሁም ውድድሮችን ለማዘጋጀትም ሆነ ለማወዳደር ከመንግሥት እና ከስፖንሰሮች 7.190.100 ብር በመሰብሰብ በቀጣይ በጀት ሊሰራ በዕቅድ ደረጃ ተይዟል ያሉ ሲሆን የታሰቡ ስራዎችም ምን እንደሆኑ አሰረድተዋል።

በጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተሰሩ ስራዎችን የሚዳስስ ዶክመንተሪ ፊልም ፣ ለፌዴሬሽኑ በአንድ እግር መቆም አሰተዋጽኦ ላደረጉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽንን ጨምሮ ለድርጅቶች፣ ለግለሰቦች እና ሌሎች አካላት የሽልማት መርሀግብር የተከናወነ ሲሆን በትጥቅ ጉዳዮችም ስምምነት ፈፅሟል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ከዚህም በተሻለ ስራዎችን ለመስራት ጉባኤው መነሳሳት ፈጥሮሎናል ያሉ ሲሆን የስፖርት ኮሚሽነሩ አቶ ፍሬው በበኩላቸው በቀዳሚነት የሚጠቀሰውን ፌዴሬሽን አጠናክረው ለመደገፍ እንደተዘጋጁ በተለይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል።