በጭቃማ ሜዳ የተደረገው የሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ያለግብ ተደምድሟል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲን አንድ ለምንም የረቱት ሀዋሳ ከተማዎች ሦስት ነጥብ ካገኙበት ፍልሚያ ሦስት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ሰዒድ ሀሰን፣ በቃሉ ገነነ እና ኢዮብ አለማየሁን በፀጋአብ ዮሐንስ፣ አቤኔዘር ኦቴ እና አብዱልባሲጥ ከማል ተክተዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ከወላይታ ድቻ ጋር አራተኛ ተከታታይ የአቻ ውጤታቸውን ካስመዘገቡበት ፍልሚያ በ55ኛው ደቂቃ በጉዳት ተቀይሮ የወጣውን መስፍን ታፈሰ ቀይሮት ወደ ሜዳ በገባው አንተነህ ተፈራ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ለሊት እና ረፋድ በድሬዳዋ በጣለው ዝናብ ምክንያት ሁለቱ ቡድኖች ጭቃ በሆነው ሜዳ ለመጫወት ተገደዋል። ገና ጨዋታው እንደተጀመረም ኢትዮጵያ ቡናዎች በራምኬል ጀምስ የግንባር ኳስ ግብ ለማስቆጠር ጥረው ነበር። ቀጣዩቹንም ሙከራዎች ከቆመ ኳስ በ13ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ እንዲሁም በ14ኛው ደቂቃ በክፍት ጨዋታ ሮቤል ተክለሚካኤል አድርገው ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጫናዎች የበዛባቸው ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ታች ወረድ ብለው ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ አልፎ አልፎም ቀጥተኝነትን በመጠቀም ግብ ለማግኘት ጥረዋል ፤ ነገርግን እስከ 41ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
ምንም እንኳን የመጫወቻ ሜዳው ምቹ ባይሆንም ቡናማዎቹ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና ቅብብል ኃይቆቹን ለማስከፈት ሲጥሩ ተስተውሏል። በተለይ በ30ኛው ደቂቃ መባቻ ጠጣሩን የተጋጣሚ የኋላ መስመር ለማስከፈት ያደረጉት እንቅስቃሴ በጎል ለመታጀብ እጅግ የተቃረበ ማራኪ ቅብብል ነበር። 35ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ራቅ ካለ ቦታ ሮቤል የላከው የቅጣት ምት ተጎድቶ የወጣውን የግብ ዘብ ሙንታሪን የተካው አላዛር የፈተነ አጋጣሚ ሆኗል።
በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በሙከራዎች ብልጫ የተወሰደባቸው ሀዋሳዎች ከላይ በጠቀስነው 41ኛው ደቂቃ ሕዝቄል ሞራኬን የፈተነ የመጀመሪያውን ሙከራ በሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ሰንዝረው ተመልሰዋል። አጋማሹ ሊገባደድ ሲል ደግሞ ቡናዎች በአብዱልከሪም እና ብሩክ ጥምር ሙከራ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በፈጣን ሁለት ጥቃቶች የጀመረ ነበር። በቅድሚያ አብዱልባሲጥ ከማል ከርቀት ሲሞክር ከሰከንዶች በኋላ ደግሞ በተቃራኒ ሳጥን ብሩክ ከመስመር መሬት ለመሬት የተሻማን ኳስ መረብ ላይ ለማሳረፍ ዳድቶ ነበር። ቡናዎች ግብ ባያስቆጥሩም ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ እየከወኑ ባሉበት ሰዓት ወሳኝ አማካኛቸው አማኑኤል ዩሐንስን በ59ኛው ደቂቃ አጥተዋል። ተጫዋቹም በቅድሚያ በ51ኛው ደቂቃ የዳኛን ውሳኔ በመቃወም ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በጥፋት ምክንያት ከሜዳው ሊወገድ ችሏል።
ቡናዎች የሁለተኛውን አጋማሽ በጥሩ ሁኔታ ቢጀምሩም ደቂቃ በደቂቃ በተለያዩ ምክንያቶች ከዳኛ ጋር ንግግር ውስጥ ሲገቡ ታይቷል። ከአምበሉ ቀይ ካርድ ውጪም የቡድኑ አሠልጣኝ ዮሴፍ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል። የቁጥሩን ብልጫ ለመጠቀም የወጠኑት ሀዋሳዎች የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን አስወጥተው የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን አስገብተዋል። ይህ ቢሆንም ቡናዎች በ73ኛው ደቂቃ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት በመሐመድኑር አማካኝነት ግብ ለማግኘት ቢጥሩም ሰለሞን ወዴሳ ውጥናቸውን አምክኖባቸዋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም በእንቅስቃሴ ድፍረት በተሞላበት አጨዋወት ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። ሀዋሳዎችም የቡናን ቁጥጥር በመስበር ከተከላካይ ጀርባ ተደጋጋሚ ሩጫዎችን ለማድረግ ቢሞክሩም ሀሳባቸው ብዙም ስኬታማ መሆን አልቻሉም። ይባስ ሙሉ ዘጠና ደቂቃው ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ አንተነህ ያሻማውን ኳስ ሮቤል በግንባሩ መረብ ላይ ለማዋሀድ ከጫፍ ደርሶ አላዛር እንደምንም ባያመክነው ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። በቀሪ ደቂቃዎች ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው አቻ ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ የሀዋሳ ከተማው አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በመጀመሪያው አጋማሽ ግብ ላለማስተናገድ ሲጥሩ እንደነበር ገልፀው በሁለተኛው አጋማሽ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች በቀይ ወጥቶ የቁጥር ብልጫውን አለመጠቀማቸው እንዳበሳጫቸው በመናገር ሜዳው ባይመችም ጨዋታውን ማሸነፍ እንደነበረባቸው ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ ቡናው ጊዜያዊ አሠልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በበኩላቸው በአጨራረስ ረገድ ቡድናቸው ላይ ክፍተት እንዳለ አውስተው የነበረ ሲሆን በጨዋታው አማካኛቸው አማኑኤል በቀይ መውጣቱ እንደጎዳቸው ተናግረው እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ግን የተሻለ ለመጫወት እንደጣሩ አመላክተዋል።