ከፍተኛ ሊግ | በፕሪምየር ሊጉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በምድብ ለ የሚሳተፈውን ክለብ ተቀላቅለዋል

በዋናው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲጫወቱ የሚታወቁ ተጫዋቾች ወደ ከፍተኛ ሊግ ክለብ አምርተዋል።

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ካለፉትን ዓመታት ስህተቶቹ ራሱን አርሞ በተፎካካሪ ተርታ ከተቀመጡ ክለቦች መካከል ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ተጠቃሹ ነው። በምድብ ለ ከመሪው አዲስአበባ በሁለት ነጥቦች ብቻ ዝቅ ብሎ በ22 ነጥብ አራተኛ ላይ የተቀመጠው ክለቡ በአሰልጣኝ ሰለሞን አየለ እየተመራ ሀዋሳ ላይ በሚደረገው የምድቡ የሁለተኛ ዙር ውድድር ላይ ይበልጥ ጠንካራ ሆኖ ለመገኘት በፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ስድስት ተጫዋቾችን በይፋ አስፈርሟል።

\"\"

በተከላካይ እና በአማካይ ስፍራ ላይ የሚጫወተው ቢያድግልኝ ኤልያስ በይፋ የቡድኑ አዲሱ ተጫዋች ሆኗል። በሲዳማ ቡና ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ጅማ አባቡና ፣ አርባምንጭ ከተማ ፣ ወልድያ ከተማ ፣ መቐለ 70 እንደርታ እንዲሁም ባለፈው ዓመት የሰበታ ከተማ ተጫዋቹ ቀዳሚው ፈራሚ ነው።

የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ጅማ አባጅፋር ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ አዳማ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ አማካይ የነበረው ኤልያስ ማሞም መዳረሻው ደብረብርሀን ኖኗል። በኢትዮጵያ ቡና የግራ መስመር ተከላካይ በመሆን ከእግር ኳሱ ቤተሰብ ጋር ከተዋወቀ በኋላ በመቐለ 70 እንደርታ ፣ ባህርዳር ከተማ እና ጅማ አባጅፋር የተጫወተው አስናቀ ሞገስ ደግሞ ሦስተኛው የክለቡ ፈራሚ ተጫዋች መሆን ችሏል።

\"\"

ከሱሉልታ ከተማ ከተገኘ በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ጅማ አባጅፋር ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና በሀድያ ሆሳዕናም ቆይታ የነበረው ፈጣኑ የመስመር አጥቂ አስቻለው ግርማ አራተኛው አዲስ ፈራሚ መሆኑ ዕርግጥ ሲሆን በተከላካይ ስፍራ ላይ ለስሑል ሽረ ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና በወላይታ ድቻ ተጫውቶ ያሳለፈው እና በሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት ችግር ካለ ክለብ ቆይቶ የነበረው ዮናስ ግርማይ እና በጅማ አባጅፋር ቆይታ ማድረግ የቻለው ልደቱ ጌታቸው ፊርማቸውን አኑረዋል።