በከፍተኛ ዝናብ ምክንያት ከአንድ ቀን ዕረፍት በኋላ በሚመለሰው ሊጉ ነገ እንደሚደረጉ በሚጠበቁ ሁለት የ17ኛ ሳምንት መርሃግብሮች ዙርያ ተከታዩቹን መረጃዎች አሰባስበናል።
ድሬዳዋ ከተማ ከለገጣፎ ለገዳዲ
የቀትሩ መርሃግብር ከሳምንታት በኃላ ከድል የታረቁትን ድሬዳዋ ከተማዎችን በሊጉ ግሮጌ ከሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ያገናኛል።
ከአራት ተከታታይ ሽንፈቶች በኃላ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ላይ ባገኙት የፎርፌ ውጤት ወደ ድል የተመለሱት ድሬዳዋ ከተማዎች አሁን ላይ በ21 ነጥብ በሰንጠረዡ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ይህ ውጤት በክለቡ ዙርያ ያለውን የውጥረት ስሜት በማለዘብ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ ከውጤት ማጣት እንዲሁም የቡድኑን ስብስብ እያስተዳደረበት ባለው መንገድ ዙርያ በብዙሃኑ የክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ትችቶች እያስተናገደ የሚገኝ ሲሆን ሊጉ ወደ ቀጣይ ከተማ ከማምራቱ በፊት ነገ ከለገጣፎ እንዲሁም በቀጣይ ሀዲያ ሆሳዕናን በሚገጥሙባቸው ጨዋታዎች አውንታዊ ውጤቶች በመያዝ የክለቡን ደጋፊ ልብ መልሰው ለማግኘት እንደሚጠቀሙበት ይታመናል።
አሁንም በ6 ነጥቦች በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በስብስብ ረገድ በሁለተኛው ዙር ተለውጠው ቢቀርቡም ሁለተኛው ዙርን በሀዋሳ ከተማ 1-0 ሽንፈትን በማስተናገድ ነበር የጀመሩት።
በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ያስፈረሟቸውን ሰባት አዳዲስ ተጫዋቾችን በሙሉ ሀዋሳ ከተማን በገጠሙበት ጨዋታ የተጠቀሙት አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ቡድናቸው በሜዳ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ፍፁም ያልተቀናጀ ነበር። ከወዲሁ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሲዳማ ቡና ጋር በ13 ነጥብ አንሰው የተጠቀመጡት ለገጣፎዎች ሳይረፍድ ከወዲሁ በፍጥነት ነጥብ ወደ መሰብሰብ መመለስ ይገባቸዋል።
በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል በነገው ጨዋታ በሙሉ ስብስብ የሚቀርቡ ሲሆን በአንፃሩ በለገጣፎ ለገዳዲዎች በኩል አጥቂው መሐመድ አበራ የነገው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት የሚያልፈው ይሆናል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2ኛ የጨዋታ ሳምንት ያደረጉት መርሃግብር በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች አንድ አቻ በሆነ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።
የቀትሩን መርሃግብር ሔኖክ አክሊሉ በዋና ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ሸዋንግዛው ይልማ በረዳትነት እንዲሁም ኤፍሬም ደበሌ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ይመሩታል።
ፋሲል ከነማ ከወላይታ ድቻ
የምሽቱ መርሃግብር በአንድ ነጥብ ልዮነት 7ኛ እና 8ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ወላይታ ድቻዎችን ከፋሲል ከነማ ጋር ያገናኛል።
በሰንጠረዡ ወገብ ላይ በ21 ነጥቦች የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ በአዳማ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠሩባቸው ሁለት ግቦች በሽንፈት ለመጀመር የተገደዱ ሲሆን በነገው የወላይታ ድቻ ጨዋታ ግን ወደ ድል ለመመለስ ጠንክረው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።
ከጨዋታ ጨዋታ ወጥ የሆነ የሜዳ ላይ ብቃትን ለማሳየት እየተቸገሩ የሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በሊጉ የተሻለ ስፍራን ይዘው ለመፈፀም በየጨዋታው ወጥ የሆነ ብቃትን ወደ ማሳየት መምጣት ይኖርባቸዋል።
ፋሲሎች በነገው ጨዋታ ላይ ከአዳማ ጋር ሲጫወቱ በቀይ ካርድ የተሰናበተውን ሱራፌል ዳኛቸውን የማያገኙ ሲሆን የከፍተኛ አስቆጣሪያቸው ፍቃዱ ዓለሙም ለጨዋታው የመድረሱ ነገር ሲያጠራጥር
ተከላካዮ መናፍ ዐወል ግን ከቅጣት የሚመለስ ይሆናል።
ከተጋጣሚያቸው ፋሲል ከነማ በአንድ ነጥብ እና ደረጃ ከፍ ብለው የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ሁለተኛውን ዙር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለ ግብ ነጥብ በመጋራት ነበር የጀመሩት።
በሊጉ ከለገጣፎ ለገዳዲ ቀጥሎ 12 ግቦችን ብቻ በማስቆጠር 2ኛው ደካማ የማጥቃት መስመር ባለቤት የሆነው ቡድኑ በመጨረሻ ባደረጓቸው ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ምንም ዓይነት ግብ ማስቆጠር ያልቻሉ ሲሆን ዕድሎችን በመፍጠር ረገድም ያለባቸው ውስንነት እጅግ አሳሳቢ ነው ለአብነትም በመጨረሻው የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ በሙሉ ዘጠና ደቂቃ ያደረጉት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ መጠን አንድ ብቻ መሆኑ በጣም አስገራሚ ነው።
ወላይታ ድቻዎች ለነገው ጨዋታ ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ ከሚገኙት ደጉ ደበበ ፣ አንተነህ ጉግሳ እና በሀይሉ ተሻገር ውጭ አዲስ የተሰማ የጉዳት ሆነ የቅጣት ዜና የለም።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር በተገናኙበት ጨዋታ ወላይታ ድቻ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በድምሩ በሊጉ ካደረጓቸው አስራ አንድ ግንኙነቶች ፋሲል ከነማዎች ስድስት እንዲሁም ወላይታ ድቻዎች ደግሞ አራት ጊዜ በድል መወጣት ሲችሉ ቀሪዋ አንድ ጨዋታ ደግሞ ነጥብ በመጋራት የተፈፀመ ነበር።
ይህን የምሽት መርሃግብር ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በመሀል ዳኝነት፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ አበራ አብርደው በረዳትነት እንዲሁም ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው በአራተኛ ዳኝነት እንዲመሩት ተመድበዋል።