የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማኅበር በቀጣይ ከ18ኛው ሳምንት ጀምሮ የሚካሄዱ ሜዳዎችን ለመምረጥ ከዛሬ ጀምሮ እንቅስቃሴ ያደርገል።
የ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመኑን ጅማሬ በባህርዳር ከተማ አድርጎ ለአምስት ያህል ሳምንታት ከቆዬ በኋላ ወደ ቀጣዩ አስተናጋጅ ድሬዳዋ ከተማ ማምራቱ ይታወሳል። ድሬዳዋ ከተማም ለስምንት ሳምንታት ያህል ውድድሩን ካስተናደች በኋላ ቀጣይ ተረኛ አዘጋጅ አዳማ ከተማ እንዲሆን መርሐግብር ተይዞለት የመክፈቻ ፕሮግራም እና የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ ሊደረግ በዝግጅት ላይ እንዳለ ከበላይ አካል በመጣ ትዕዛዝ ምክንያት የአዳማ ቆይታ እውን ሳይሆን መቅረቱ ይታወቃል።
ሆኖም የአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ አስቸኳይ ባደረገው ስብሰባ ኮሚቴዎችን በማዋቀር በድሬዳዋ እና በባህር ዳር የመገምገም ሥራ ሲሠራ ቆይቶ በድጋሚ ሊጉን ወደ ድሬዳዋ ሊመልሰውም ችሏል። ነገርግን ሁለተኛው የድሬዳዋ ቆይታ ሊጉን በመልካም ጎን የሚያስጠራ ሳይሆን ይልቁንም በወቅቱ ባለው ዝናብ ምክንያት የመጫወቻ ሜዳዎቹ ምቹ ባለመሆናቸው በርካታ ጨዋታዎች በይደር እየተያዙ ሲራዘሙ ሰንብተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎችን የሚያደርግ በመሆኑ ሊጉ ለሦስት ሳምንታት ከተቋረጠ በኋላ በቀጣይ የሚካሄድባቸው ሦስት ከተማዎች በዕጩነት ቀርበዋል።
ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ የ18ኛው ሳምንት የሚጀመርበትን ቦታ ለመምረጥ በሊግ ካምፓኒው አክስዮን ማኅበር ኮሚቴ ተዋቅሯል። ይህ ኮሚቴ በተመረጡ ሦስት ሜዳዎች ማለትም በሀዋሳ ፣ በአዳማ እና በባህርዳርን ከዛሬ ጀምሮ የመገምገም ሥራ በማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግሮችን ያደርጋሉ።
ከግምገማው መልስ ሐሙስ ኮሚቴዎቹ የደረሱበትን ደረጃ ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ አክሲዮን ማኅበሩ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ መልስ ሊጉ የት ይካሄዳል የሚለውን ቦታ ይፋ የሚያደርግ መሆኑ ታውቋል።