የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ16ኛ ሣምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሣምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲጀመር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል ከመመራት ተነስተው ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።

ይርጋጨፌ ቡና 1-2 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ለተመልካች እጅግ አዝናኝ በነበረው የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ ፉክክር ሲደረግበት የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ግን ይርጋጨፌዎች የተሻሉ ነበሩ። 33ኛው ደቂቃ ላይም በዳግማዊት ሰለሞን የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ለጥቂት የወጣ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም መስታወት አመሎ ባስቆጠረችው ግብ አጋማሹን መርተው ጨርሰዋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችሉ በአጋማሹ የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ዕድልም አስቆጥረውት ወደ ጨዋታው መመለስ ችለዋል። አይናለም ዓለማየሁ ከቀኝ መስመር ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረችውን ኳስ ግብጠባቂዋ ምሕረት ተሰማ መቆጣጠር ተስኗት መረቡ ላይ አርፏል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ግን ይርጋጨፌዎች በድጋሚ ጨዋታውን ለመምራት ተቃርበው ነበር። ፍሬሕይወት ተስፋዬ ከሳጥን አጠገብ ያደረገችው ሙከራ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል።

በማራኪ የኳስ ቅብብል የመጨረሻ ኳሳቸውን አጥቂዋ ኢየሩስ ወንድሙ ላይ በማድረግ ተደጋጋሚ ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ የነበሩት እንስት ፈረሰኞች በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ግን የተሳካ ጊዜ አሳልፈዋል። 74ኛው ደቂቃ ላይም ተቀይራ ከገባች አምስት ደቂቃ ያልቆየችው ትዕግስት ወርቄ ያገኘችውን ኳስ ከረጅም ርቀት በዓየር ላይ እንዳለ በመምታት በውድድሩ ከታዩ ድንቅ ጎሎች ውስጥ አንዱ አድርጋዋለች። ቀሪዎቹ ደቂቃዎችም ለተመልካች ሳቢ ፉክክር ተደርጎባቸው ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ 0-0 ልደታ ክ/ከተማ

08፡00 ሲል በጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ልደታዎች የተሻሉ ቢመስሉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሀዋሳዎች ብልጫውን ወስደዋል። 8ኛው ደቂቃ ላይም ረድዔት አስረሳኸኝ ከሳጥን ውጪ ያደረገችውን ሙከራ የግቡ የላይ አግዳሚ ገጭቶ ሲመልስባት 25ኛው ደቂቃ ላይም ራሷ ረድዔት ከግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ የልደታዋ ግብጠባቂ አክሱማዊ ገ/ሚካኤል መልሳባታለች። ልደታዎች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ይቸገሩ እንጂ በተረጋጋ መንፈስ በጨዋታው ብልጫ እየወሰዱ ቢመጡም ከወትሮው በተለየ የአማካይ እና የአጥቂዎቻቸው አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በተዳከሙባቸው ሀዋሳዎች 41ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። በአጋማሹ ልዩነት ፈጣሪ የነበረችው ረድዔት አስረሳኸኝ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘቸው እሙሽ ዳንኤል ያደረገችው ሙከራ በግራው ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶባት ትልቅ የግብ ዕድል አባክናለች።

ሁለት ዓይነት መልኮች በነበሩት ሁለተኛ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ይህ ነው የሚባል የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልታየበት ነበር። ሆኖም በቀሪዎቹ ደቂቃዎች የጨዋታው ግለት እየጨመረ ሲሄድ ሀዋሳዎች ቀይረው ወደ ሜዳ ካስገቧት ቁምነገር ካሣ በሚነሱ ኳሶች በርካታ የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ ራሷ ቁምነገር 79ኛው እና 86ኛው ደቂቃ ላይ በላዩ አግዳሚ በኩል ለጥቂት የወጡ ሙከራዎች ማድረግ ችላ ነበር። በኳስ ቁጥጥሩ መኃል ሜዳው ላይ ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ልደታዎች ፈታኝ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ግብ ከማስተናገድ ለጥቂት ተርፈዋል። ሀዋሳዎች በሴኮንዶች ልዩነት ሳጥን ውስጥ ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርጉ በተለይም እሙሽ ዳንኤል እና ታሪኳ ጴጥሮስ ያደረጉት ፈታኝ ሙከራ በዕለቱ ኮከብ በነበረችው ግብጠባቂዋ አክሱማዊ ገ/ሚካኤል እና በተከላካዮች ርብርብ መክኖባቸዋል። ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።

መቻል 3-2 ድሬዳዋ ከተማ

በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ የተደረገው የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር መቻልን ከድሬዳዋ ከተማ ሲያገናኝ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ሲሆን አንድ ብቻ ለግብ የቀረበ ሙከራ ተደርጎበታል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ የዳኛ ፊሽካ ሲጠበቅ የመቻሏ ነጻነት ፀጋዬ ከግራ መስመር ያደረገችው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተሻሽሎ ሲቀርብ አምስት ግቦችም ተቆጥሮበታል። በቅድሚያም የድሬዳዋ የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻ የሆነችው ሜላት ደመቀ 61ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረችው ግብ ቡድኗን መሪ ብታደርግም መቻሎች 67ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ ባስቆጠረችው ግብ ወደ ጨዋታ መመለስ ችለዋል። በሴኮንዶች ልዩነትም ማዕድን ሳህሉ የግብ ጠባቂዋን መውጣት ተመልክታ ከፍ አድርጋ ባስቆጠረችው ግሩም ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።

\"\"

በተዘናጉበት ቅፅበት በአንድ ደቂቃ ሁለት ግብ ያስናተገዱት ድሬዳዋዎች በተረጋጋ የጨዋታ መንፈስ በመቀጥል በቀኙ የሜዳ ክፍላቸው የወሰዱትን ኳስ ቃልኪዳን ተስፋዬ በግንባሯ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፋው አቻ መሆን ችለዋል። ባልተጠበቁ ክስተቶች ተቃራኒ ስሜት ለማስተናገድ የተገደዱት ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን በአቻ ያጠናቅቃሉ ተብሎ ሲጠበቅ 89ኛው ደቂቃ ላይ ግን ፀጋ ንጉሤ ግብ አስቆጥራ መቻልን የ 3-2 ጣፋጭ ድል ባለቤት አድርጋለች።