\”ካንቴ ይቀማልኛል\”

በኤልሻዳይ ቤኬማ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፐርፎርማንስ አናሊስት ኤልሻዳይ ቤኬማ ወቅታዊውን የሀገራችን የእግርኳስ ችግር አስመልክቶ ተከታዩን የግል አስተያየት እንደሚከተለው አቅርቧል።

አንድ የእግር ኳስ ጨዋታን ለማካሄድ መሰረታዊ ነገር ነው ተብሎ የመጀመሪያ ረድፍ ላይ የተቀመጠው ሜዳ ነው ፡፡ እግር ኳስን በወጥነት በዓለም ደረጃ ለመምራት ይረዳ ዘንድ ህጎችን የሚያወጣው እና የሚያሻሽለው አካል IFAB መጀመሪያ መሟላት አለበት ብሎ ህግ ቁጥር አንድ ሜዳ ብሎ የጀመረውም በምክንያት ነው። እስኪ የጨዋታ ሜዳ ሳይኖር እግርኳስን አስቡት…! በእርግጥ ኳስስ ሳይኖር ፤ ተጫዋችስ ሳይኖር የሚል ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ ለመግባት ሳይሆን ለሜዳ የሰጠነው ትኩረት ፣ የፈጠረብን ጉዳት ፣ በቶሎ ካልፈታነው የሚኖረው ተፅዕኖ እና ቢስተካከል ልናገኝው የምንችለውን ጥቅም እኔ በበኩሌ እቺን ልበል ብዬ ነው። ከዚህ በፊት በተለያየ ጊዜ ስፖርቱ አካባቢ ያሉ ሰዎች ያነሱት ጉዳይ ቢሆንም እስኪፈታ ባለመሰልቸት ጉዳዩ መነሳት አለበት ብዬ አምናለሁ ፡፡

ሀገር ሆኖ በመቆም ከሁሉም አፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ በሰፊ ልዩነት ትቀድማለች ፤ እንዲያውም ከብዙ የዓለም ሀገራት ቀዳሚ ናት። የአፍሪካ ኳስን በመመስረትም በግንባር ቀደምትነት አስደናቂ ሚና ተጫውታለች ፣ በፊፋ አባልነት ስማችን ከሰፈረ ዓመታቶችን አስቆጥረናል ፣ በየዓመቱ ከሁለት ቢልየን ብር በላይ በዚሁ ስፖርት ላይ ገንዘብ እናፈሳለን፡፡ ታዲያ ኢትዮጵያ \’አንድ ሜዳ የለሽም\’ ስትባል አይገርምም ? ይሄ ችግር ቢፈታ በቃ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግር ይፈታል የሚል አጉል ሀሳብ ይዤ ግን አይደለም ይሄን ጉዳይ ያነሳሁት።

\"\"

በዘመናዊ እግር ኳስ ከፍ ያለ ቦታ ላይ የደረሱት ሀገሮች መሰረታዊ ጉዳዮችን ቀድመው ስለፈቱ / The Devil is in the details / ብለው ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመስራት ታክቲካዊ ትንቅንቅ ላይ ናቸው፡፡ ጥቃቅን ጉዳዮች ቅንጦት የሆኑብን እኛ የሴጣኖቹ መፈልፈያ ካምፕ የሆነውን ስንፍናችንን ካላስወገድን በሁሉም አቅጣጫ ያለብን ድክመት አንድ ቀን ከስር እንዳይነቅለን እፈራለሁ፡፡ ያለውን እውነታ በመካድ መቀጠል የማንችልበት ደረጃ ላይም ደርሰናል፡፡ ለማነኛውም ከሜዳ ጥራት ጋር በተገናኘ ያልሰራነው ሥራ ያደረሰው ጉዳት በእኔ ዕይታ በመጠኑ ላንሳ።

እንደሚታወቀው አሰልጣኝ የሚያምንበት የጨዋታ ፍልስፍና እና ያንን ፍልስፍና ወደ መሬት የሚያወርድበት ታክቲካዊ ጉዳዮችን የሚወስኑ ነገሮች ብዙ ቢሆንም ሜዳ አንደኛው ነው፡፡ የሜዳው ስፋት እና ጥበት ወይም የሜዳ ጥራት ደረጃ ታክቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተፅኖ አላቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ አሰልጣኝ \’ሜዳው አመቺ ስላልሆነ የግብ ክልላችን አካባቢ ስህተት መስራት ስለማንፈልግ ቀጥተኛ ኳሶችን በመጠቀም ከሜዳችን እንወጣለን\’ ካለ የሜዳው አለመመቸት ታክቲካዊ ጉዳዮችን ላይ ተፅኖ ፈጠሩ ማለት ነው፡፡ ታዲያ የሜዳ ጥራት ጉዳይ በቋሚነት ከዓመት እስከ ዓመት የሚኖር ከሆነ ክለቦቻችን ላይ ልናየው የምንፈልገውን የታክቲክ ትንቅንቅ ህልም ሆኖ ይቀር እና አሰልቺ አንድ ዓይነት ጨዋታ የምናይበት ዕድል ይሰፋል።

እግርኳስ የጊዜ እና ቦታ / Time and Space / አጠቃቀም ላይ የተመሰረተ ነው ፤ በእነዚህ ሁለት ነገሮች የሚወሰን ጨዋታ ነው፡፡ ጊዜ እና ቦታ የሚለውን ሀሳብ በሌላ ፅሁፍ በዝርዝር የማቀርብ ሲሆን ለአሁን ግን ባነሳነው ሀሳብ ላይ በጥቅሉ ጊዜ እና ስፍራ አጠቃቀም ላይ ያለውን ተፅዕኖ እንመልከት፡፡ ለምሳሌ አንድ ተጫዋች ለሌላ ጓደኛው ኳስ ለማቀበል በሚመታበት ጊዜ አቀባዩ ስለሚያቀብለው ኳስ በተመለከተ ለየትኛው እግሩ እንደሚሰጠው ፣ ተገቢውን የማቀበል ፍጥነት እና ጥራት ፣ ቀጣይ እንቅስቃሴን የሚያመቻች እንደሆነ እና መሰል ጉዳዮችን በአንድ ማቀበል ውስጥ አስቦ ሲሰጥ እንዲሁም ተቀባይ ከመቀበሉ በፊት በቀጣይ የሚወስነውን በዙሪያው ያሉ አማራጮችን ፣ አቋቋሙን እና መሰል ጉዳዮችን ኳስ ወደ እሱ እየመጣ የሚፈፅማቸው ነገሮች ናቸው፡፡ በሰጪ እና ተቀባይ አንድ ቅብብል መሀል ያነሳናቸው ውሳኔዎች ለዚያውም በሰከንዶች ጊዜ ውስጥ የሚደረጉ ናቸው፡፡ ታዲያ ተጫዋቾቻችን በሜዳ ጥራት ችግር ኳሷ እንደ ሰካራም እየተንገዳገደች እየመጣች የዘረዘርኳቸውን ጉዳዮች ያስቡ ወይስ በሰላም መድረሷን በጉጉት ይጠባበቁ ? እግርኳስ ላይ ደግሞ መቀባበል በዚህ ደረጃ አደጋ ውስጥ ገባ ማለት ትልቅ እንቅፋት ከመሆኑ ባሻገር አሰልቺ ይሆናል፡፡ አንድ ጓደኛዬ በቅርቡ \”አሁንስ ማየት ሰለቸኝ ልተው ነው\” ብሎኛል። ይሄ ሀሳብ የስንት ሰው ይሆን ? ሊያሳስበን ይገባል፡፡

በሊጋችን ላይ የሂደቶች መቆራረጥ በስፋት የሚታይ ነው፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት መነሳት ያለበት የጠራ የጨዋታ መንገድ ፣ በልምምድ የዳበረ ጥራት ያለው አተገባበር፣ የተጫዋች ጥራት እና ሌሎች ነገሮችን መጥቀስ ቢቻልም የሜዳ ጥራት ግን የችግሮቹ መሰረት ነው፡፡ አንድ ወዳጄ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከዚህ ቀደም ይጫወት የነበረን ልጅ ስም ጠርቶ የነገረኝን ላጫውታችሁ፡፡

ተጫዋቹ በጣም ድንቅ የአማካይ ክፍል ተጫዋች ሲሆን ስለሚያደርገው የጨዋታ ሂደቶች ሲያስረዳ \”እኔ ኳስ ሳገኝ ከአማካይ የሚጠበቁ ነገሮችን በጥንቃቄ ለመከወን እሞክራለው። ከመንጠቅ ጋር በተገናኝ ግን ኑጎሎ ካንቴ ስለሚነጥቅልኝ (ሜዳውን ማለቱ ነው) ብዙም አያሳስብም\” አለኝ ብሎ ነገረኝ። የሜዳ ጥራት መጓደል ከችሎታ አንፃር ውስን አቅም ያለውንም ፣ አስደናቂ ክህሎት ያለውንም ፣ በተለያየ ምክንያት ራሱን ለጨዋታ ዝግጁ ያላደረገውንም ፣ ታዳጊ ተጫዋቹንም ፣ ለብዙ ዓመታት ግልጋሎት የሰጠውንም ሁሉንም ተጫዋቾች በአንድ መድረክ ተከባብረው ያለ ልዩነት በጋራ እንዲቆሙ አድርጓቸዋል። በኢንተርናሽናል ጨዋታ ግን ይሄን ሜዳ ያመጣውን መከባበር አናገኝውም።

በእግር ኳስ የጨዋታ ሀሳብህን ወደ ተጫዋቾቹ የምታሰርፅበት የተለያዩ የሥልጠና ዘዴዎች አሉ፡፡ Differential Training Methodology የሚባለው አንዱ ሲሆን የዚህ የሥልጠና ዘዴ ሀሳቡ የተለያዩ ችግሮችን ሆን ብሎ በልምምዱ ውስጥ በማካተት ተጫዋቹ ለብዙ ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጥ በማድረግ በዋናነት የተጫዋቹን የአዕምሮ እና የውሳኔ ፍጥነት ላይ ዕድገት እንዲኖር የሚያደርግ የሥልጠና ዘዴ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የሜዳን ስፋት መጨመር ወይም መቀነስ ፣ ቅብብል የሚረብሽ ኮኖችን መጠቀም ፣ የቁጥር አለመመጣጠን ፣ የኳሶችን ብዛት ከአንድ በላይ ማድረግ ፣ አሽዋ ሜዳ ላይ ልምምዱን ማድረግ እና ሌሎችም ሊሆን ይችላል ፡፡ ነገር ግን ይሄ የሥልጠና መንገድ አንዱ የልምምድ ክፍል እንጂ ህይወታችን ሊሆን አይገባም፡፡

\"\"

እግር ኳስ በአትዮጵያ በብዙ ሰው እንደመወደዱ ፣ በርካታ ችሎታ ያላቸው ታዳጊዎች እንደመኖራቸው ፣ ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር እንደመሆናችን እና ቀላል የማይባል የፋይናንስ እገዛ በዚሁ ስፖርት ላይ ወጪ እንደመውጣቱ ፍሬ እያየን አይደለም። መንግሥት ጥራት ያላቸው ሜዳዎችን በትኩረት መስራትን ሊያየው የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ፣ ደራርቱ ቱሉ እና የሙያ አጋሮቻቸው በሀገር ላይ ያላቸውን የኢንቨስትመንት እና የማህበራዊ ጉዳዮች አውንታዊ ተፅዕኖ በተመሳሳይ በእግርኳሱ ማግኝት የሚችልበት ዕድል እንዳለ በማሰብ ኢንቨስት መደረግ አለበት። ሰይዶ ማኔ ለሀገሩ ሴኔጋል እየሰራ ያለው ሆስፒታል (በኮቪድ ወቅት ሀገሩን እንዴት እንደረዳ ምን ዓይነት ኢንቨስትመንት እያደረገ እንደሆነ ማየት) ፣ ኤቶ ፣ ድሮግባ ፣ ዊሀ ፣ ሳላሀ ዝርዝሩ ብዙ ነው ፤ ተመሳሳይ ነገር በሀገራችን መፍጠር ግን ይቻላል፡፡ የመጀመሪያ እርምጃ ግን ሜዳ መስራት ነው።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን \’ሁሉም ክለቦች በካፍ ወይም ደግሞ በፊፋ የክለብ ላይሰንሲግ መስፈርት መሰረት እያንዳንዱ ነገር ተሟልተው ሲገኙ ነው ክለብ የምላቸው\’ የሚል አስገዳጅ ነገር መደንገግ ከባድ እና ወደ መሬት ማውረድ የሚቻል ባይሆንም ደረጃ በደረጃ ግን አስገዳጅ ነገሮችን መጀመር አለበት ብዬ አምናለሁ ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ከሜዳ ጋር በተገናኘ በሀገር ደረጃ ለውጥ የማምጣት አቅሙም ልምዱም ባይኖረውም ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች አንፃር ከፌዴሬሽን ጋር በጋራ የክለብ ላይሰንሲግ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይችላል። ሊግ ካምፓኒውን የመሰረተው የክለቦች ጥምረት እንደመሆኑ ለራሳቸው መልካም እና ምቹ ከባቢ ለመፍጠር ዋነኛ መሳሪያ የሆነውን የክለብ ላይሰንሲግ መስፈርት የሟሟላት እንቅስቃሴን ከፌዴሬሽኑ ጋር ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። እንዴት አንድ የክለብ ላይሰንሲንግ መስፈርቶችን የሚያሟላ ክለብ እናጣለን ?

የኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ እየተደረገበት ያለው ሜዳ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ይገባኛል አሁን የሚደረገውም ውድድር በሆኑ ሰዎች ጥረት ነው እንጂ እንደ ቸልተኛነታችን ከዚህም የከፋ ሜዳ ላይ ልንጫወት በቻልን፡፡ እኔ ግን የማወራው እንደ ሀገር እጅግ እጅግ የሚያሳዝን ሜዳ ላይ ሊጋችን እየተካሄደ መሆኑን ነው። እውነት ለመነጋገር አሁን ፕርሚየር ሊጉ እየተካሄደበት ያለው ፎርማት ማለትም አንድ ሜዳ ላይ በቀን ሁለቴ በሳምንት አራት ቀን ጨዋታን ማድረግ በሌሎች ሀገራት ካለው ተሞክሮ ጋር ሲነፃፀር የድሬደዋ ስታዲየም \’ወንጀል ተፈፅሞብኛል! \’ ብሎ ክስ በከፈተብን ነበር ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሜዳ ውጪ በመጫወት ያጣችውን የተለያዩ ጉዳዮችን ማንሳት ዘንግቼ ሳይሆን ጉዳዩን እንደምንም ብሎ አንድ ሜዳ ከማዘጋጀት ያለፈ እንደሆነ እና በርካታ ሜዳዎች እንደሚያስፈልጉ ለመጠቆም ነው። ያው ምክር ለሰጪው ቀላል አይደል ?

በቲክቶክ ዘመን ከሁለት መስመር በላይ መፃፍ አስፈላጊ ባይሆንም የሚመለከታቸው አካላት ካነበቡት ብዬ ያነሳሁት ሀሳብ ይህንን መሳይ ነበር።

ይህ አስተያየት የፀሀፊው የግል ምልከታ መሆኑ ልብ ይሏል።