የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ 20ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ ሲጀመር ሀዋሳ ፣ አርባምንጭ እና አዲስ አበባ ተመሳሳይ የ1-0 ድል አሳክተዋል።

\"\"

ሀዋሳ ከተማ 1-0 ይርጋጨፌ ቡና

04፡00 ሲል በተጀመረው የሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ሲደረግበት የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሀዋሳዎች የተሻሉ ነበሩ። በተለይም 16ኛው ደቂቃ ላይ ፀሐይነሽ ጁላ  በግንባሯ ገጭታ የሞከረችው እና ግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ በግሩም ቅልጥፍና የመለሰችባት ኳስ አስቆጪ አጋጣሚያቸው ነበር። የጠራ የግብ ዕድል አይፍጠሩ እንጂ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ሀዋሳዎች 24ኛው ደቂቃ ላይም በሕይወት ረጉ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ከራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ ጠንካራ ይሁኑ እንጂ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የተቸገሩት ይርጋጨፌዎች በአጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ በተዘናጉበት ቅፅበትም ግብ አስተናግደዋል። ረድዔት አስረሳኸኝ ከሳጥን አጠገብ ባስቆጠረችው ድንቅ ግብም ሀዋሳ ከተማ አጋማሹን መርቶ ሊወጣ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ሀዋሳዎች በተጋጣሚ የግብ ክልል ውስጥ በቁጥር በዝተው በመገኘት ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ 62ኛው ደቂቃ ላይም ሲሣይ ገ/ዋህድ ከረጅም ርቀት ያደረገችውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ አግዳባታለች። 73ኛው ደቂቃ ላይ ከሰባት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ የተመለሰችው የሀዋሳ ከተማ ጥምር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቱሪስት ለማ ግብ ጠባቂዋን አታልላ ስታልፍ ኳሱ በመርዘሙ አቁማ ወደኋላ በመመለስ ለረድዔት አስረሳኸኝ ስታቀብል ረድዔትም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አርባምንጭ ከተማ 1-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከምሳ መልስ በተደረገው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በየጥቂት ደቂቃው በሚወስዱት የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ይታጀብ እንጂ የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። የጊዮርጊሷ ዓይናለም ዓለማየሁ በግል ክህሎቷ ታግዛ ለማጥቃት ከምታደርገው ጥረት ውጪም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳንመለከትበት አጋማሹ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጊዮርጊሶች በማራኪ የኳስ ቅብብል በተለይም አይናለም ዓለማየሁ በምታሳየው ክህሎት ለተመልካች አዝናኝ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል አርባምንጮች የበላይነቱን ወስደዋል። 57ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም ታምሩ በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ብትሞክረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የዋና ዳኛዋ ሲሣይ ራያ ፊሽካ ሲጠበቅ ግን ራሷ ቤተልሔም ታምሩ ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት በመምታት ባስቆጠረችው ድንቅ ግብ አርባምንጭ ከተማ የ 1-0 ጣፋጭ ድል ባለቤት ሆኗል።

አዲስ አበባ ከተማ 1-0 ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ

10፡00 ላይ በተደረገው የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ 6ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባዋ አሥራት ዓለሙ የያዘችውን ኳስ ወደ ሳጥን ልታስገባ በሞከረችው እና  ግብ ጠባቂዋ ላይላ ሸሪፍ ከሳጥን ወጥታ በእግሯ በመለሰችባት ኳስ የመጀመሪያውን የግብ ዕድል ሲያስመለክተን 21ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም መንተሎ ከቀኝ መስመር ከማዕዘን ባሻማችው እና የካቲት መንግሥቱ በግንባሯ ገጭታው በአግዳሚው በኩል ለጥቂት የወጣው ኳስም የአዲስ አበባ ከተማዎች በአጋማሹ የተደረገ የተሻለ የግብ ሙከራ ነበር።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት በሚያገኙት ኳስ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሞክሩት ንፋስ ስልኮችም 45ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። አልፍያ ጃርሶ ሳጥን ውስጥ አክርራ የመታችውን ኳስ ጥሩ ንቃት ላይ የነበረችው ግብጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ አግዳባታለች።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በአጋማሹ የተፈጠረው የተሻለ ብቸኛ የግብ ዕድል ግብ ሆኗል። 75ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም መንተሎ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከተገኘው የቅጣት ምት የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ላይላ ሸሪፍ በእጇ መቆጣጠር ባለመቻሏ መረቡ ላይ አርፏል።

ግብ በተቆጠረበት ቅፅበት የንፋስ ስልኩ አሰልጣኝ ድሪባ ጃንቦ ዳኞችን አፀያፊ ስድብ በመሳደቡ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል። ጨዋታውም በአዲስ አበባ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"