\”…ከራሴም፣ ከቀጣሪዎቼም፣ ከነፍሴም ጋር ተነጋግሬ ቆይታዬን ወደፊት የምመልሰው ይሆናል\” ውበቱ አባተ

አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ከጊኒው ጨዋታው መልስ በሀገር ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታውን ወደ ሞሮኮ በማምራት ከጊኒ አቻው ጋር አድርጎ ያለምንም ነጥብ መመለሱ ይታወቃል። ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰ ከቀናት በኋላ ደግሞ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለብዙሃን መገናኛ አባላት መግለጫ ሰጥተዋል።

አሠልጣኙ በቅድሚያ \”የምድብ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታችንን ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር አድርገን ተመልሰናል። ወደ ቦታው ስንሄድ በውድድሩ ላይ የሚያቆየንን ውጤት ለማስመዝገብ ነበር ፤ ነገርግን እንደተከታተላችሁት ያሰብነውን ማሳካት አልቻልንም። በተለይ የመጀመሪያው ጨዋታ መጥፎ ነበር። በሁለተኛው ጨዋታ የተሻለ አቀራረብ ነበረን። ነገርግን በነጥብ ደረጃ ያሰብነውን ማሳካት አልቻልንም።\” የሚል አጠር ያለ ገለፃ ካደረጉ በኋላ ተከታዮቹ አንኳር ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ቀርበዋል።

\"\"

ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ስኬታማ ነኝ ብለው ያስባሉ?

ስኬታማነት አንፃራዊ ነው። እኛ እየመራን ያለነው ብሔራዊ ቡድን ትክክለኛ መደላደል ላይ ያለ ቡድን አይደለም። ከመጀመሪያው የኒጀር ጨዋታ ጀምሮ ያሉት ነገሮችን ማየት አለብን። ነገርግን ያለፉትን ሁለት ዓመታት በአፍሪካ ዋንጫ እና በቻን ውድድር ማለፋችን ትልቅ ነገር ነው። እርግጥ በውድድሮቹ አልፈን ረጅም ርቀት መጓዝ አልተቻለም። ይህንን ለዋሉ ሰዎች ክሬዲቱን መስጠት አለብን። ብሔራዊ ቡድናችን እንደነግብፅ በየሁለት ዓመቱ በአህጉራዊ ውድድሮች ሲሳተፍ የነበረ አይደለም።

በብሔራዊ ቡድኑ ይቀጥላሉ?

ይሄ የብዙዎች ጥያቄ እንደሆነ አስባለው። ይህ በእኔ ብቻ የሚወሰንም አይደለም። ድንገት አሁን ተነስቶ ይሄ ነው ማለት ከባድ ነው። ምክንያቱም የሁለት ዓመት ውል ነው ያለኝ። ስለዚህ ከቀጣሪዎቼ ጋር ያለውን ነገር መነጋገር አለብን። ከራሴም፣ ከቀጣሪዎቼም፣ ከነፍሴም ጋር ተነጋግሬ ቆይታዬን ወደፊት የምመልሰው ይሆናል።

ከግብፁ ጨዋታ አንፃር ቡድኑ ወጥ ያልሆነበት መንገድ…?

ከግብፁ ጨዋታ አሁን አምስት ተጫዋቾች በጊኒው ጨዋታ አልተጫወቱም። ሌሎች ብሔራዊ ቡድኖች በዓመታት ውስጥ የሚኖራቸው የተጫዋች ለውጥ በጣም ጥቂት ነው። አሁን ከጉዳት እና ከሌሎች ነገሮች ጋር ተያይዞ እንዳልኩት ተጫዋቾችን አጥተናል።

ያሰቡትን ነጥብ ስላለማሳካታቸው…?

ወደየትኛውም ጦርነት እሸነፋለው ብለህ አትገባም። እኛም ጊኒም እናሸንፋለን ብለን ነበር። እኛ ተሸንፈናል። አዎ መሸነፍ አልነበረብንም። እንደየትኛውም አሠልጣኝ በውድድሩ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችል ነጥብ ማግኘት ነበረብን ፤ ግን አልሆነም። ከውድድሩ ወጥተን ሊሆን ይችላል። ግን ከዚህ ቀደም ተዋርደን የወጣንባቸው አጋጣሚዎች ነበሩን። አሁንም ቀጣይ የግብፅን ጨዋታ በጥሩ ዝግጅት ለመቅረብ እንጥራለን።

አሁን ያለንን ሊግ ማሳደር አለብን። በተለያየ አቅጣጫ ብሔራዊ ቡድኑን ለማሳደግ ስራዎች መሰራት አለባቸው። እየሰራን ያለነውም ነገር ፍፁም ነበር ማለት አልችልም።

ስለቀጣይ ጨዋታዎች…?

ውድድሩ ውስጥ እስካለን ድረስ ቀጣይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ነው የምናስበው። እርግጥ ሁለት ቡድኖች ርቀውን 9 ነጥብ ይዘዋል። እነሱ ላይ መድረስ ከባድ እንደሆነ ይገባኛል።

ከተጫዋቾች ጋር ስላላቸው ግንኙነት…?

የማሰልፋቸው ተጫዋቾች ለእኔ ጥሩ ነገር አላቸው። የማስቀምጣቸው ግን ሊደብራቸው ይችላል ብዬ አስባለው። ይሄ ያለ ነው። 23 ተጫዋች ቢኖርም የሚጫወቱት 11 ብቻ ናቸው። ሁሉም ተጫዋቾች እንዲያድጉ ነው ፍላጎቴ። በግልም እደውላለው የማየውን እናገራለው። እንደእኔ ሁሉንም ተጫዋቾች አንድ ነገርላይ እኩል እንዲሆኑ እፈልጋለው። አንድ ነገርግን ሁሉም ዲሲፕሊን እንዲሆኑ እፈልጋለው። ከዚህ ውጪ የተለየ ግንኙነት የለንም።

ስለመጀመሪያው ጨዋታ…?

በመጀመሪያ ጨዋታ ላይ ከፍተኛ የሆነ የኳስ ብክነት ነበር። ዳር ላይ ሆኜ ለማስተካከል ስጥር ነበር። ጨዋታው ከቁጥጥራችን ውጪ ነው የነበረው። እረፍት ላይም ነግሬያቸው ነበር። ተጫዋቾቹ አዳምጠውኛል ፤ ነገርግን ተግብረውታል ማለት አልችልም። በአጠቃላይ የመጀመሪያው ጨዋታ ከቀለማችን ውጪ ነበር። ለዚህ ነው እንደዚህ ለመጫወት አሠልጣኝ አያስፈልጋችሁም ያልኳቸው። እንደ መጀመሪያው ጨዋታ ለመጫወት ስልጠናም እኔም አላስፈልጋቸውም።

\"\"

ከሚዲያ ጋር ስላላቸው ግንኙነት…?

ሁሉንም ሚዲያ አንድ ላይ መፈረጅ አልፈልግም። ሙያዊ ትችት የሚሰጡ፣ ያላየሁትን ነገር የሚጠቁሙ እና የሚያስተምሩኝ አሉ። አይደለም እነሱን የሚሰድቡኝንም አከብራለው። ስድብ የምለው ቃል በቃል ስድብ ስለሆነ ነው። የእኔንም የቤተሰቤንም ስም የሚየጠፉ እና አስተዳደጋቸውን በሚዲያቸው የሚያሳዩ አሉ። በእነሱ ደረጃ መባለግ አልፈልግም። ኳስ ያለ ሚዲያ ምንም ነው። ሁሉንም አከብራለው። ከማንም ጋር የተለየ ግንኙነት የለኝም። ሁሉንም አከብራለው። ከተቀጠርኩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በታሰበበት ሁኔታ ጥቃት ሲደርስብኝ ነበር። ግን ማለፍ ነው።

በመጨረሻ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና የሥራ-አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አጠር ያለ ገለፃ አድርገዋል። አቶ ባህሩ ለሞሮኮ መንግስት እና እግርኳስ ፌዴሬሽን ምስጋና አቅርበው ከአሠልጣኝ ቆይታ ጋር ተያይዞ \”አዲስ ውል ከተፈራረምን በኋላ የተመዘገቡት ውጤቶች መሰረታዊ ናቸው። በዚህ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ እግርኳስ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተዋዋልነውን ነገር የሚመለከት ይሆናል። በቀጣይ የሚኖረውንም ነገር የምትሰሙ ይሆናል። ከዚህ ውጪ ምንም ማለት አልፈልግም።\” በማለት ከአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቆይታ ጋር ተያይዞ የተነሳላቸውን ጥያቄ መልሰዋል።