ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን በፉክክሩ ገፍቶበታል

ኢትዮጵያ መድኖች መድኖች ከመሪው ቅዱስ ግዮርጊስ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት የመለሱበትን ድል አርባምንጭ ከተማ ላይ አሳክተዋል።

\"\"

በተደጋጋሚ ጊዜ በሚሰሩ ጥፋቶች ታጅቦ የጀመረው ጨዋታው መድኖች የተሻለ የተንቀሳቀሱበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የአካል ንክኪዎች እና ጥፋቶች የነበሩት ጨዋታው ጥፋቶቹን ተከትለው በሚሰጡ የቅጣት ምቶች ሙከራዎች ተደርገውብታል።
በ9ኛው ደቂቃም በተጠቀሰው መንገድ ከቅጣት ምት የተገኘው ዕድል የግብ ጠባቂው ስህተት ታክሎበት ብሩክ ሙሉጌታ ግብ በማስቆጠር መድንን መሪ ማድረግ ችሏል።

\"\"

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት አዞዎቹ ፤ ሙከራ በማድረግ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። አሸናፊ ፊዳ በግንባር ያደረገው ሙከራ ፤ መሪሁን መስቀለ ከረጅም ርቀት ያደረገው ሙከራ እና አሕመድ ሁሴን ከግቡ ግራ ጠርዝ አከባቢ ያደረገው የተሻለ ለግብ የቀረበ ሙከራ በዚህ ረገድ ይጠቀሳሉ።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በተወሰነ መንገድ አፈግፍገው ለመጫወት የሞከሩት መድኖችም በጨዋታው ጥሩ ተንቀሳቅሶ ግብ ባስቆጠረው ብሩክ ሙሉጌታ አማካኝነት ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ሆኖም ሁለቱም ሙከራዎች በተመሳሳይ በመኮንን መርኮድዮስ ድንቅ ብቃት መክነዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ቅያሪ አድርገው ወደ ሜዳ የተመለሱት አርባምንጮች ከቅያሪዎቹ በኋላ ብልጫ ወስደዋል። በ50ኛው ደቂቃም ኤሪካ ካፓይቶ ተቀይሮ የገባው መላኩ ኤልያስ በጥሩ መንገድ ያሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

\"\"

ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ይሳዩት አዞዎቹ በ69ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር ፤ ሆኖም አቡበከር ኑሪ ተከላካዮቹ የካፓይቶ እና አሕመድ ሁሴን ሙከራዎች ተረባርበው ማክሸፍ ችለዋል። ከሰባት ደቂቃዎች በኋላም ኢትዮጵያ መድኖች በሲሞን ፒተር አማካኝነት ግብ አስቆጥረው በድጋሚ ጨዋታውን መምራት ችለዋል ፤ ግቧም በጨዋታው በርካታ ጥፋቶች የተሰሩበት ባሲሩ ዑመር በጥሩ መንገድ ያመቻቻት ነበረች።

\"\"

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል በርካታ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በአርባምንጮች በኩል በካፓይቶ በመድኖችም በሀቢብ አማካኝነት የተደሩጉ ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ ነበሩ።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ
\”በመጀመርያው አጋማሽ እነሱ ኳስ በመቆጣጠር የተሻሉ ነበሩ። ብዙ አጋጣሚዎች ፈጥረናል ብዙ ማስቆጠር ነበረብን \” ብለዋል። አሰልጣኙ አክለውም በሁለተኛው አጋማሽ ያደረጓቸው ቅያሬዎች በጨዋታው ለውጥ እንዳመጡ ገልፀዋል። አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቀጥለው \”ስለ ነጥብ ልዩነት ብዙም አናስብም ፤ አጨዋወቱ እና ቡድኑን ማላመድ ላይ ነው ዋናው ስራችን። ጨዋታው ጥፋቶች የበዙበት ነበር። ይህም አጨዋወታችን ላይ አሉታዊ አስተዋፅዖ አድርጓል\” ካሉ በኋላ በመከላከሉ ረገድ በተለይም በትኩረት ማነስ እና በቦታ አያያዝ በተለይም ክፍተት እንዳለባቸው አብራርተዋል።

\"\"