ከፍተኛ ሊግ | የ17ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲጠናቀቁ የቀሪዎቹ ምድቦች ጨዋታዎች ዛሬ ተጀምረዋል።

በቴዎድሮስ ታከለ እና ጫላ አቤ

ምድብ ሀ

አሰላ ላይ እየተደረገ በሚገኘው የምድብ \’ሀ\’ ውድድር ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ተስተናግደዋል። በቀዳሚው የጠዋት ጨዋታ ባቱ ከተማ እና ሀላባ ከተማ ያለግብ ተለያይተዋል። በመቀጠል በተደረገው ጨዋታ ሰበታ ከተማ ባልተጠበቀ ሁኔታ ግዛው ሸንቁጤ ባስቆጠረው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ቤንች ማጂ ቡናን 1-0 ሊረታ ችሏል። ውጤቱ የመውረድ ስጋት ላለበት ሰበታ ከተማ ተስፋን የሰጠ ሲሆን ወደ አንደኛነት ከፍ የማለት ዕድል የነበረው ቤንች ማጂ ቡና አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ አቃቂ ቃሊቲ በሰለሞን ያለው ብቸኛ ግብ ሰንዳፋ በኬን 1-0 መርታት ችሏል።

ምድብ ለ

በምድብ ለ የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ሁለቱን የመዲናይቱን ክለቦች ያገናኘ መርሀግብር ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ ከመሪው ሻሸመኔ ከተማ ጋር ነጥቡን የሚያጠብበትን ዕድል በተጋጣሚው ቂርቆስ ተሸንፎ ሳያሳካ ቀርቷል።

\"\"

4፡00 ሲል የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ፈጠን ያሉ እንቅስቃሴዎችን ያስመለከተን ሲሆን ኳስን በመቆጣጠር ቂርቆሶች በርካታ የጎሉ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማዎች በቀዳሚው አርባ አምስት ተሽለው የታዩበት ነበር ማለት ይቻላል። ነገር ግን ኳስን በሚይዙበት ወቅት የአዲስ አበባን ተከላካዮች በቀላሉ ለማለፍ የማይቸገሩት ቂርቆሶች 10ኛው ደቂቃ ላይ በሔኖክ አወቀ ድንቅ ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ግብን ካርተናገዱ በኋላ በተደጋጋሚ ኤርሚያስ ሐይሉን ዋነኛ የማጥቂያ መንገዳቸው አድርገው አዲስ አበባዎች መጫወት ከጀመሩ በኋላ በርካታ አጋጣሚዎችን አግኝተው ከመረብ ጋር ማወሀድ ተስኗቸው ታይቷል። በተለይ ኤርሚያስ ከግብ ጠባቂው ቢኒያም ታከለ ጋር ሁለት ጊዜ አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው የመለሰበት የሚያስቆጩ የቡድኑ ግልፅ ዕድሎች ነበሩ።

\"\"

ከዕረፍት መልስም በተመሳሳይ አዲስ አበባ ከተማዎች የተጫዋች ቅያሪን በማድረግም ጭምር ጎል አስቆጥረው ወደ አቻነት ለመምጣት ብርቱን ትግል ውስጥ ገብተዋል። ቡድኑ ከተሻጋሪ እና በመስመር እንቅስቃሴዎች ወደ ግብ ክልል በማለፍ ግቦችን ለማስቆጠር በድግግሞሽ ከጎሉ ጋር የመገናኘት ዕድልን ፈጥረው የተገኙ ቢሆንም ከፊት መስመር ላይ ተሰልፈው የሚገኙ ተጫዋቾች ይታይባቸው በነበረው ያለ መረጋጋት ቡድኑን የኋላ ኋላ ዋጋ አስከፍሏል። የኋላ መስመራቸው በተለይ አዲሱ መገርሳ የዳኛን ውሳኔ በመቃወሙ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ከተወገደባቸው በኋላ በጥብቅ መከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ የነበሩት ቂርቆሶች ተሳክቶላቸው ጨዋታውን 1ለ0 አሸንፈው ወጥተዋል።

በመቀጠል ሁለቱን በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ክለቦችን ያገናኘው ጨዋታ በጉለሌ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክርን ተመሳሳይ የሆነ የአጨዋወት ቅርፅን ማየት በቻልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ የሚገኙ ዕድሎችን በአግባቡ ለመጠቀም ይጥሩ የነበሩት ጉለሌዎች አጋማሹ ሊገባደድ ሰከንዶች እየቀሩ ከማዕዘን ምት ሔኖክ ሞላ ያሻማትን ኳስ ልማደኛው የቡድኑ አጥቂ ጁንዴክስ አወቀ ጎል አድርጓት ክለቡን መሪ አድርጓል።

\"\"

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ተመልሶ ሲቀጥል ከምባታ ሺንሺቾዎች ሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን ጉለሌዎች ተጨማሪ ጎል ከመረብ ለማዋሀድ ብርቱ ትግል ውስጥ የገቡበት ነበር። ጉለሌዎች ሦስት ግቦችን በዚህኛው አጋማሽ ያስቆጠሩ ቢሆንም ከጨዋታ ውጪ ተብለው ጎሎቹ ተሽረዋል ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ 1ለ0 በጉለሌ ድል አድራጊነት ተጠናቋል።

ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን የጂንካ ከተማ እና ይርጋጨፌ ቡና ጨዋታ በሽርፍራፊ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ጂንካን ሦስት ነጥብ አሸምቷል።

በደጋፊዎቻቸው ታግዘው ጨዋታቸውን ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው የጨዋታ አርባ አምስት ተመጣጣኝ እና ለተመልካቹ ማራኪ የሆነን የጨዋታ መንገድ ሲከተሉ ታዝበናል። ጨዋታው እንደተጀመረ መልኤል ብርሀኑ ከቅጣት ምት አክርሮ መቶ አበበ በላይ በመለሰበት ሙከራ ወደ ማድረጉ የተሸጋገሩት ይርጋጨፌዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ ዮሐንስ ኪሮስ ወደ ጎል አክርሮ ሲመታ የጂንካው ተከላካይ ናኩዌር በቀለ በራሱ ላይ አስቆጥሯታል። መደበኛው ቀዳሚ አርባ አምስት ሊገባደድ 45+1 ላይ ከቆመ ኳስ ሀቁምንይሁን ገዛኸኝ ቆንጆ ጎል አስቆጥሮ ጂንካን አቻ አድርጓል።

\"\"

በተሻለ ንቃት ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ጂንካዎች በርካታ ዕድሎችን አግኝተው በተጋጣሚያቸው ላይ ልዩነት መፍጠር የቻሉበትን ሒደት ተመልክተናል። ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የዋሉት ጂንካ ከተማዎች 90+2 ላይ ተቀይሮ የገባው ጎሳዬ ብርሀኑ ሦስት ተጫዋቾች አልፎ ሀምዲ ቶፊቅ መረብ ላይ ቡድኑን አሸናፊ ያደረገች ግብን በማስቆጠር ጨዋታው 2-1 ተጠናቋል።

ምድብ ሐ

በምድብ ሐ በቅድሚያ ሮቤ ከተማ እና ዳሞት ከተማ ተገናኝተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና ፈጣን እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ ሲሆን በኳስ ቁጥጥር እና የመሀል ሜዳውን በመብለጥ ጫና ሲፈጥሩ የነበሩት ሮቤ ከተማዎች ነበሩ። ዳሞት ከተማዎች ኳስን በመልቀቅ የሚገኙትን አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ይህንን ተከትሎ ጨዋታው በተጀመረ በ7ኛው ደቂቃ ዳሞት ከተማዎች ያገኙትን ኳስ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በሱልጣን አቢዩ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሮቤ ከተማዎች ኳስን መስርተው በማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ከተፍተኛ ጫና የፈጠሩ ቢሆንም ዳሞት ከተማዎች የተከላካይ ስፍራቸውን በማጠናከር ምንም ግብ ሳይቆጠርባቸው አጋማሹ ተጠናቋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የሮቤ ከተማዎች የበላይነት የተስተዋለበት ነበር። ሮቤ ከተማዎች ጫናዎችን በመፍጠር ግብ ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በ59ኛው ደቂቃ ላይ የዳሞት ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ሮቤ ከተማ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሶፊያን ገለቱ ወደ ግብ በመቀየር ሮቤ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል። ይህንንም ተከትሎ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ የተስተዋለ ሲሆን በ82ኛ ደቂቃ ላይ ዳሞት ከተማዎች ያገኙትን ግልፅ የግብ ዕድል በተደጋጋሚ ግብ ሲያስቆጥር የነበረው ሱልጣን አቢዩ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

የምድቡ ሁለተኛ በነበረው የኮልፌ ክ/ከተማ እና ስልጢ ወራቤ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በአንፃራዊ ሁኔታ ስልጢ ወራቤዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት በሙሀጂረ መኪ እና እንዲሁም በመስመር በኩል አብዲ ረሀመቶ ያሳዩት ድንቅ ብቃት ትተጠቃሽ ነበር። እንዲሁም የአጥቂ ክፍላቸው በብሩክ ሰማ ጥሩ እንቅስቃሴ የተመራ ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን የስመለከትን ሲሆን በኮልፌ ክ/ከተማ በኩል በቅርቡ ወደ ክለቡ የተቀላቀለው ዮሐንስ ሲማሙ ከፊልሞን ገ/ፃዲቅ ጋር በመጣመር ተስፋ ሰጪ እና ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከቱን አስመልክተውናል።

\"\"

በተከላካይ ስፍራ ውብሸት አለማየሁ የስልጢ ወራቤን የማጥቃት ሙከራ በብቃት ሲቋቋም ተመልክተናል። የአጥቂ ስፍራውን ቃልጌታ ምትኩ ሲመራውና አደገኛ የማጥቃት ሙከራ ሲፈጥሩ የተስተዋለ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በ42ኛው ደቂቃ ኮልፌ ክ/ከተማዎች ያገኙትን ጥሩ የግብ ዕድል በቃለጌታ ምትኩ አማካኝነት በማስቆጠር መሪ ሆነው ወደ ዕረፍት አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ስልጢ ወራቤዎች መመራታቸውን ተከትለው ግብ ለማስቆጠር ይበልጡኑ ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን ከቆይታ በኋላም የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ እና የፊት ክፍሉን በማጠናከር ግብ ለማስቆጠር ሲጥር ተመልክተናል። ሆኖም አንድም የግብ ዕድል ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ጨዋታውን በሽንፈት አጠናቀዋል።

የምድቡ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በሶዶ ከተማ እና ደሴ ከተማ መካከል የተደረገ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ሶዶ ከተማ ኃይልን የቀላቀለ አጨዋወት አና ፍጥነት የቀላቀለ አጨዋወት የተጫወቱ ሲሆን ደሴ ከተማ ደግሞ ተቀዛቅዘው ኳስን በመያዝ ተጫውተዋል።

\"\"

የመሀል ሜዳቸው በተስሏች ሳይመን እየተመራ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ወደ ፊት በመላክ የግብ ዕድል ሲፈጥር አዲስ ህንፃ ኳስን አረጋግቶ በድንቅ ችሎታ ሲያሰራጭ ተመልክተናል። እንዲሁም በሶዶ በኩል አሸናፊ ነጋሽ ኳስን ወደ ፊት ለማፍጠን ሲጥር ተስተውሏል። በ42ኛው ደቂቃ ደሴ ከተማዎች በግሩም ሁኔታ ያገኙትን ኳስ በአዲስ ህንፃ አማካኝነት በማስቆጠር ደሴ ከተማን መሪ በማድረግ አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሶዶ ከተማዎች ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን ግብም ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ደሴ ከተማዎች ግብ ላለማስተናገድ ኳስን በመያዝ ከኳስ ጋር ብዙ ሰዓት በማሳለፍ ምንም ግብ ሳያስተናግዱ ማሸነፍ ችለዋል።

\"\"