መረጃዎች | 71ኛ የጨዋታ ቀን

ነገ በብቸኝነት የሚደረገውን የ17ኛ ሳምንት የመዝጊያ መርሐ-ግብር በተመለከተ ተከታዮቹን መረጃዎች አዘጋጅተናል።

ከክፍያ ጋር በተያያዘ ለረጅም ጊዜ ልምምድ ያልሰሩት ወልቂጤ ከተማዎች እጅግ ዘግይተው ከትናንት በስትያ እና ትናንት ተጫዋቾቻቸው ተሰባስበው ከነገው ጨዋታ በፊት ሁለት ልምምዎችን ብቻ አድርገዋል። እርግጥ ቡድኑ የውድድር ዓመቱን ዘለግ ያለ ጊዜ ከደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋር ተያይዞ አሉታዊ ዜናዎች እየተሰሙበት የከረመ ቢሆንም አሁን የቡድኑ አባላት ጥያቄ አውንታዊ ምላሽ ያገኘ ይመስላል። የሆነው ሆኖ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው ቡድኑ እንደዚህ አይነት ችግሮችን እየተፋለመ እስካሁን ያስመዘገበው ውጤት ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህ ቢሆንም ግን አሁንም የወራጅ ቀጠናው ስጋት በመጠኑ አለባቸው። ስለሆነም በተሟላ ሁኔታ ዝግጅት ባያደርጉም እስከ አምስተኛ ደረጃ ድረስ ከፍ ሊያደርጋቸው የሚችለውን ሦስት ነጥብ ላለማጣት እንደሚጥሩ ይታመናል።

\"\"

ከብሔራዊ ቡድኑ እረፍት በፊት በሁለት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ተስኗቸው በኢትዮ ኤሌክትሪኩ ፍልሚያ ወደ ድል የተመለሱት ባህር ዳር ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው በተቃራኒ የተሟላ ዝግጅት በመዲናችን አዲስ አበባ አድርገው በዛሬው ዕለት አዳማ ገብተዋል። የሊጉ ቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ የሆነው ባህር ዳር ከተማ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች የጣላቸው 11 ነጥቦች ዋጋ እያስከፈለው ከመሪው ጋር ያለው ልዩነት በመጠኑ ሰፋ ብሏል። እርግጥ በመጨረሻው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ቢያሸንፍም በብሔራዊ ቡድን ምክንያት ሊጉ መቋረጡ ረዘም ያለ የዝግጅት ጊዜ ስለሚቸረው ክፍተቶቹን በሚገባ ሊያይ ይችላል። ነገም ከበላዮቹ ከሚገኙት ክለቦች ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እንደሚጫወት ይገመታል።

ወልቂጤ ከተማ አሁንም የግብ ዘቡ ሮበርት ኦዶንካራን በግልፅ ባልተነገረ ምክንያት ያላገኘ ሲሆን ከአንዋር ዱላ ውጪ ግን ሁሉንም ጉዳት ላይ የነበሩ ተጫዋቾች አግኝቷል። በባህር ዳር ከተማ በኩም ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን በውድድር አጋማሽ የዝውውር መስኮት የፈረመው ማማዱ ሲዲቤም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ወልቂጤ እና ባህር ዳር ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ ተገናኝተዋል። በግንኙነታቸውም ባህር ዳር አንድ ጊዜ ሲረታ ወልቂጤ በበኩሉ ሁለቱን አሸንፏል ፤ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በአምስቱ ጨዋታዎች ሁለቱም ቡድኖች እኩል አምስት አምስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ጨዋታውን ዳንኤል ግርማይ በመሀል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ሰብስቤ ጥላሁን በረዳትነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በአራተኛ ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል።

\"\"