በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ \’ሐ\’ ዛሬ ድል ያደረገው ገላን ከተማ በግብ ልዩነት ምድቡን መምራት ጀምሯል።
ምድብ – ሐ
ኦሜድላ 1-1 ሀምበሪቾ ዱራሜ
ቀዳሚው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ፈጣን እንቅስቃሴ እና ያለመሸነፍ ስሜት የታየበት ሲሆን በጨዋታው ሁለቱም ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ያረጉበት አጋማሽ ነበር። ጨዋታው እንደተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ ልማደኛው ዳግም በቀለ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በጭንቅላቱ በማስቆጠር ሀምበሪቾ ዱራሜን መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን የግቧን መቆጠር ተከትሎ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በጥሩ ሞራል ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ታይተዋል። ኦሜድላዎች በአንፃሩ መከላከልን አማራጭ በማድረግ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም አጋማሹ በሀምበርቾ መሪነት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች የተጫዋች ቅያሬ በማድረግ የውጤት ለውጥ ለመፍጠር ሲጥሩ የተመለከትንበት አጋማሽ ሲሆን በኦሜድላ በኩል የፊት መስመር ተሰላፊው ተመስገን መንገሻ እንዲሁም ቻላቸው ቤዛ ጥሩ ጥሩ የሚባል ኳሶችን ወደ ግብ በመሞከር አቻ ለመሆን ጥረት አድርገዋል። ይህንንም ተከትሎ በ57ኛው ደቂቃ ኦሜድላዎች ያገኙትን ኳስ ከመስመር በማሻማት በታምራት እያሱ አማካኝነት አቻ የሆኑበትን ግብ በማስቆጠር በድናቸውን ከሽንፈት መታደግ ችሏል። በ74ኛው ደቂቃ ላይ በተፈጠረው የሜዳ ውስጥ ያልተገባ ባህሪይ በሀምበሪቾ ዱራሜ በኩል ዳግም በቀለ በኦሜድላ በኩል ተመስገን ታሪኩ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል። ጨዋታውም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ጅማ አባ ጅፋር 1-2 ነጌሌ አርሲ
በጨዋታው ፈጣን እና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በነጌሌ አርሲ በኩል የመሀል ሜዳውን በሰለሞን ገመቹ አማካኝነት እየተመራ በኳስ ቁጥጥር በመብለጥ ኳሶችን ወደ መስመር ለያሬድ መሀመድ እና ለምስጋናው መላኩ በተደጋጋሚ በማቅረብ ጅማ አባ ጅፋሮች ላይ ጫና ለመፍጠር ሲጥሩ ተመልክተናል። ጅማ አባ ጅፋሮች የኳስ ብልጫ ስለተወሰደባቸው በመስመርና ረጃጅም ኳሶች በመጠቀም ጫና ለመፍጠር ሲጥሩ ተመልክተናል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን ግን ሁለቱም ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ያደረጉበት አጋማሽ ነበር። ይህንንም ተከትሎ በ53ኛው ደቂቃ ነጌሌ አርሲዎች በጥሩ ቅብብል ያገኙትን ኳስ በምስጋና መላኩ አማካኝነት በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ አባ ጅፋሮች ወደ ፊት በመጫን ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተመልክተናል። ይህንንም ተከትሎ በ75ኛው ደቂቃ ያገኙትን የግብ ዕድል ሱራፌል ፍቃዱ ወደ ግብ በመቀየር ጅማ አባ ጅፋሮች አቻ መሆን ችለዋል። ብዙም ሳይቆይ በ82ኛው ደቂቃ ላይ ነጌሌ አርሲዎች በጥሩ የኳስ ቅብብል የተገኘውን የግብ ዕድል ተቀይሮ የገባው አብዱልሀኪም ሱልጣን በግሩም ሁኔታ ከረጅም ርቀት በማስቆጠር ነጌሌ አርሲዎች መሪ የሆን ችለው ጨዋታው በነጌሌ አርሲዎች አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቡራዩ ከተማ 0-1 ገላን ከተማ
ጨዋታው እንደተጀመረ በአንደኛው ደቂቃ ገላን ከተማዎች ጫና በመፍጠር የቡራዩ የተከላካይ ክፍል በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ኳስ በበየነ ባንጃው ግብ በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል። የግቧ መቆጠርን ተከትሎ ቡራዩ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ገላን ከተማዎች ተረጋግተው እና ኳስ በመያዝ የሚገኙ ዕድሎችን በመጠቀም ወደ ፊት በመሄድ የግብ ዕድል ፈጥረዋል። ይህንንም ተከትሎ በሱፈቃድ ነጋሽ ገላን ከተማዎች ያገኙትን ቅጣት ምት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ይጠቀሳል። መደበኛው አጋማሽ ተተናቆ በተጨማሪ ደቂቃ የቡራዩ ከተማ ተጫዋች መሐመድ ከድር በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ ቡራዩ ከተማዎች ተነቃቅተውና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ በፊት መስመራቸው አኗር ሙራድ እና ቅዱስ ተስፋዬ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። ሆኖም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በገላን ከተማ አሸናፊነት ተተናቋል። ገላን ከተማ ማሸነፉን ተከትሎ ከሀምበሪቾ ዱራሜ በነጥብ ዕኩል በመሆን በግብ ብልጫ የምድቡ መሪ መሆን ችሏል።