በትግራይ ክልል የሚገኙ ተጫዋቾች ስላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ከቀድሞው የመቐለ 70 እንደርታ የመስመር ተከላካይ አንተነህ ገብረክርስቶስ ጋር ቆይታ አድርገናል።
ላለፉት ሦስት ዓመታት በተካሄደው የእርሰ በርስ ጦርነት ምክንያት በሁሉም የሊግ እርከኖች የሚገኙ የትግራይ ክለቦች ከውድድር ውጪ መሆናቸው ይታወሳል። በጦርነቱ ሰለባ ከሆኑት ዘርፎች አንዱ እግርኳስ መሆኑም ግልፅ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ የትግራይ ስቴድየምን ወቅታዊ ሁኔታ ከቀናት በፊት ያስቃኘናችሁ ሲሆን አሁን ደግሞ በክልሉ ስለሚገኙ ተጫዋቾች ከቀድሞው የመቐለ 70 እንደርታ የመስመር ተከላካይ አንተነህ ገብረክርስቶስ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።
የትግራይ ክልል ተጫዋቾች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ?
\”ተጫዋቾቹ እና በክለቦቹ ዙርያ የሚገኙ ባለሞያዎች ያሉበት ሁኔታ ትንሽ ከባድ ነው። አሁን አጀንዳችን በስፖርቱ ዙርያ ሆነ እንጂ የትግራይ ህዝብ በሙሉ ችግር ውስጥ ነው ያለው። አብዛኛው ስፖርተኛ ሥራ አጥ ሆኖ ችግር ውስጥ ነው ያለው ፤ ዕድሉን አግኝቶ ከክለቦች ጋር መነጋገር የቻለ ደግሞ ይህን ያህል ጊዜ ከስፖርቱ ርቀህ ስለ ቆየህ አናስገባህም የሚል ነው እየተሰጠው የሚገኘው ምላሽ። ተጫዋቾቻችን በችግር ውስጥ ነው ያሉት ፤ ድጋፍ ይሻሉ።\”
ችግሩን ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ትላለህ ?
\”ቅድም እንዳልኩህ ነው ፤ የስፖርት ዘርፍ በቀላሉ መታየት የለበትም። የኮትዲቯር ልምድ መጥቀስ እንችላለን። እነ ድሮግባ እግርኳሱን ተጠቅመው ሀገሪቱን እንዴት ወደ ሰላም እንደመለሷት ይታወቃል።
እዚህም በስፖርቱ ዙርያ ከተሰራ ብዙ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለው። ሙሉ ለሙሉ ባይመለስም ብያንስ የተወሰነ እንቅስቃሴ መኖር ነበረበት። ተጫዋቾቹ ፣ ክለቦች እና ሜዳዎች በምን ሁኔታ ይገኛሉ ብለው እንኳን ጉብኝት ማድረግ ነበረባቸው። ደራርቱ ቱሉ ወደ ትግራይ መጥታ ያደረገችው ዓይነት ጉብኝት ማለት ነው። በትላልቅ ክለቦች ደረጃም ባይሆን እግርኳስ ቢጀመር ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው ፤ ስፖርት ትውልድ በመቅረፅ ያለውን ድርሻ ትልቅ ነው። ትግራይ ላይ ምን ዓይነት የእግር ኳስ እንቅስቃሴ እንደነበር ይታወሳል ፤ ይሄ ሜዳ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው አውሮፓ እንኪባል የስታዲየሙ ድባብ ብዙዎች አስገርሞ ነበር።\”
ችግሩን ለመቅረፍ በማህበር ደረጃ ተደራጅታቹህ ጥያቄ ለማቅረብ አልሞከራችሁም ?
\”እኛ በኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋቾች ማሕበር ውስጥ እንጂ የትግራይ ማህበር የሚባል አልነበረንም። ከኢትዮጵያ ተጫዋቾች ማህበር \’በትግራይ የሚገኙ አባሎቻችን በምን ሁኔታ ይገኛሉ ?\’ ብሎ የጠየቀም የለም። ማህበሩ በችግራችን ወቅት ከጎናችን አልቆመም። የሰላም ስምምነቱ ከተፈፀመ ብዙ ጊዜ ሆኖታል ፤ ግን ምንም የተደረገ ነገር የለም።
በዚህ ተግባርም እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎች አዝነዋል።\”
አሀን ላይ በትግራይ ክልል የስፖርት አስፈላጊነት እስከምን ድረስ ነው ?
\”በቁጥር ቀላል የማይባል ወጣት አልባሌ ቦታ ላይ ነው የሚውለው። ለዚህ ዋነኛ መፍትሄው ደግሞ ስፖርት ነው። ትግራይ ውስጥ ከስፖርቱ የበለጠ ብዙ አንገብጋቢ ችግሮች እንዳሉ እረዳለሁ ፤ የስፖርት አስፈላጊነት ግን ቀላል አይደለም።
ወጣቱ ቅድም ካልኩህ ችግሮች እንዲላቀቅ የስፖርት አስፈላጊነት ወሳኝ ነው።\”
ስታድየሙ ዖና ሆኖ ስታየው ምን ተሰማህ ?
\”ሀገሪቱ ውስጥ በጥራትም በድምቀትም ግንባር ቀደም ከሆኑ ስቴድየሞች አንዱ ነበር። እንዲህ ሆኖ ሳየው በጣም ነው ያዘንኩት። ለመጀመርያ ጊዜ ስቴድየሙን ያየሁት በ2009 የትግራይ ደርቢ ሲካሄድ ነበር። ሁሌም የስታዲየሙ ድባብ አስደናቂ ነበር ፤ ከዓመታት በኋላ እንዲህ ሆኖ ካየሁት በኋላ ደግሞ በጣም ነው ያዘንኩት።\”
በስተመጨረሻ…
\”ሁሉም ባለድርሻ አካላት የእግርኳስ እንቅስቃሴ ለማስጀመር ጥረት ማድረግ አለባቸው ፤ ይህንን የምለው አምራች ዜጋውን ለማዳን ከማሰብ አንፃር ነው። ከሱስ የፀዳ ትውልድ ለመፍጠር ስፖርት ወሳኝ ነው።\”