የዋልያዎቹ የሞሮኮ ጉዞ አስተዳደራዊ ዝግጅት…

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ሞሮኮ የሚያደርገውን ጉዞ አስመልክቶ የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን አስተዳደራዊ ጉዳዮችን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጊኒ አቻው ጋር ላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በዛሬው ዕለት ወደ ሞሮኮ የሚያመራ ሲሆን የቡድኑን ጉዞ አስመልክቶ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ሥራ-አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በአሁኑ ሰዓት ጋዜጣዊ መግለጨቀ እየሰጡ ይገኛሉ። በቅድሚያም አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ያስረዱት አቶ ባህሩ ጥላሁን ስለጉዞው ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

\"\"

\”ከጊኒ ጋር የምናደርገው ጨዋታ ቀኑ ከታወቀ በኋላ የመጫወቻ ስታዲየም እንድናሳውቅ ካፍ ጠይቆን ነበር። ሀገራችን ፍቃድ ያለው ስታዲየም እንደሌላት ይታወቃል። ከዚህ ቀደም ወደ ታንዛኒያ አምርተን ተጫውተን እንደነበር ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ታንዛኒያን መርጠን ነበር። ከዚህ ውጪ ግን ከሪከቨሪ እና ከፋይናንሳል ወጪ አንፃር ከጊኒ ፌዴሬሽን ጋር ውይይት አድርገን ነበር። በንንግሩም እነሱ ሰሜን አፍሪካ በተለይ ሞሮኮን እንደሚመርጡ ከነገሩን በኋላ የራሳችንን ጥቅም ለማሰብ ሞክረናል። ይህንን ተከትሎ ሞሮኮ ተጫውተን ወደ ታንዛኒያ መምጣቱ ምን ያህል ዋጋ ሊያስከፍለን እንደሚችል በማወቃችን እዛው ለመጫወት ወስነናል። በዚህ ውሳኔ አስተዳደራዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን ስፖርታዊ ነገሩንም ለማየት ሞክረናል። እንዳልኩት ከሪከቨሪ እና ከአየር ሁኔታ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ከአሠልጣኝ ቡድን አባላት ጋር ተወያይተናል።

\”የሜዳ አለመኖር ዋጋ እያስከፈለን ነው። እንደ ሀገር ደግሞ ዋጋ እየከፈለ ያለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ነው። ወጪ ብቻ ሳይሆን የደጋፊ ድጋፍም እያገኘን አይገኝም። የቻን ዝግጅት ጊዜ በክቡር ፕሬዝዳንታችን ንግግር የሞሮኮ ፌዴሬሽን ሙሉ ወጪያችንን ችሎን ነበር። አሁንም ያለው ወጪ ከፍተኛ ስለሆነ ፕሬዝዳንታችን አቶ ኢሳይያስ ጂራ ከሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር የአኮሜዴሽን ወጪያችን በሞሮኮ ተሸፍኗል። በዚህም የሞሮኮን እግርኳስ ፌዴሬሽን እናመሰግናለን። በአጠቃላይ 70 ሺ ዶላር የሞሮኮ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይሸፍንልናል።\”

\"\"

ከዚህ ውጪ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከ1x ቤቲንግ ጋር ውል ተፈራርሞ የፒች ብራንድ ማስታወቂያ እንደሚታይና ፌዴሬሽኑ 8 ሺ ዶላር እንዳገኘ ጠቁመዋል።