ልዩ ዘገባ ከሞሮኮ | ጊኒ በነገው ጨዋታ ልታጣቸው የምትችላቸው ተጫዋቾች እነማን ናቸው?

በነገው ወሳኝ ጨዋታ በኢትዮጵያ በኩል ምኞት ደበበ በቅጣት ምክንያት የማይኖር ሲሆን በጊኒ በኩል ደግሞ ሦስት ተጫዋቾች የመግባታቸው ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በ2023ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዋልያዎቹ በነገው ዕለት ከጊኒ አቻቸው ጋር ወሳኝ የምድብ 3ኛ ፍልሚያቸውን የሚያከናውኑ ሲሆን ከጨዋታው በፊትም በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተሰጠውን አስተያየት አከታትለን አቅርበናል። በቡድን ዜና ረገድ በኢትዮጵያ በኩል ተከላካዩ ምኞት ደበበ በሁለት ቢጫ ካርዶች ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ሲሆን በተጋጣሚያችን ጊኒ በኩል ደግሞ ሁለት የአጥቂ መስመር ተጫዋቾች እንዲሁም አንድ ተከላካይ ነገ የመግባታቸው ነገር አጠራጣሪ እንደሆነ ተሰምቷል።

\"\"

የመጀመሪያው ተጫዋች በጀርመኑ በስቱትጋርት የሚጫወተው ጉይራሲ ሰርሁ ነው። በቡንደስሊጋው በ13 ጨዋታዎች 6 ጎሎች በስሙ ያሉት አጥቂው በክለብ እያለ ተጎድቶ ስብስቡን የተቀላቀለ ሲሆን ከሰኞ ጀምሮም ከአጋሮቹ ጋር ልምምድ እንዳልሰራ ተጠቁሟል። ይልቁንም ለብቻው ተነጥሎ ልምምድ ሲሰራ እንደነበር ከጊኒ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚዲያ ኦፊሰር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ምናልባትም ተጫዋቹ የነገው ጨዋታ አምልጦት ሁለተኛው ጨዋታ ላይ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚችል ተገምቷል።

ሁለተኛው ተጫዋች ደግሞ በፈረንሳይ የሚጫወተው የ24 ዓመቱ ሞርጋን ቦኖ ነው። አጥቂው በቡድኑ ሁለት የልምምድ መርሐ-ግብሮች የተሳተፈ ቢሆንም በትናትናው ዕለት ተጎድቶ ከሜዳ ወጥቷል። የተጫዋቹ የጉዳት አይነት ምን እንደሆነ ባይገለፅም ለክፉ እንደማይሰጠውና ምናልባት በነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር ማለዳ ላይ እንደሚለይ ተመላክቷል።

ኮንቴ ኢብራሂማ ሶሪ ደግሞ ሌላኛው በጨዋታው የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ የሆነ ተጫዋች ነው። እንደ አብዛኞቹ የብድን አጋሮቹ በፈረንሳይ ሊግ የሚጫወተው ተከላካዩ ከትናንት በስትያ በነበረው የቡድኑ ልምምድ ላይ ብሽሽቱ አካባቢ ህመም አጋጥሞት ልምምድ ያልሰራ ሲሆን እንደ ሞርጋን ቦኖ ጠዋት ያለበት ሁኔታ ታይቶ ምናልባት ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ ጨዋታውን ሊከውን እንደሚችል ተገልጿል።

\"\"