ጎፈሬ ከሲዳማ ቡና ጋር ያለውን ስምምነት ለሦስት ዓመታት አራዘመ

👉 \”ጎፈሬ አብሮን እንዲሰራ ጥሪ ስናቀርብ በጎ ምላሽ መልሰው አብረውን ለመስራት ስለመጡ በጣም እናመሰግናለን\” አቶ አቡሽ

👉 \”ሲዳማ ቡና እና ጎፈሬ ትስስራቸውና አካሄዳቸው ቤተሰባዊ ነው\” አቶ ሳሙኤል

ከተቋቋመ ገና በጣት የሚቆጠሩ ዓመታት የሆነው ጎፈሬ ከበርካታ የሀገር ውስጥ ክለቦች ጋር በትጥቅ ጉዳዮች መጠነ ሰፊ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ከሀገር አልፎም በምስራቅ አፍሪካ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እና ክለቦች ጋር ስምምነቶችን እየፈፀመ ምህዳሩን እያስፋፋ ይገኛል። ከሀገር ውስጥ ክለቦች መካከል ደግሞ ሲዳማ ቡና የሚገኝ ሲሆን ሁለቱ አካላት ያለፉትን ጊዜያት በጥትቅ አቅርቦት ስራዎች አብረው ሲሰሩ ቆይተው ግንኙነቱን ለማራዘም በዛሬው ዕለት የፊርማ ሥነ-ስርዓት አከናውነዋል።

\"\"

በሐምሌ ወር 2013 በይፋዊ የፊርማ ስነ-ስርዓት አብረው መስራት ጀምረው የነበረው ሲዳማ እና ጎፈሬ ውላቸው ከወራት በኋላ ይጠናቀቃል። ይህንን ተከትሎ ሁለቱ አካላት በዛሬው ዕለት አመሻሽ ላይ እስከ 2018 ድረስ የሚቆይ ስምምነታቸውን አራዝመዋል።

በሥነ-ስርዓቱ ላይ የጎፈሬ መስራች እና ባለቤት አቶ ሳሙኤል፣ ምክትል ሥራ-አስኪያጁ አቶ አቤል እንዲሁም የማርኬቲንግ ዲፓርትመንት ሀላፊው አቶ ፍፁም ሲገኙ በሲዳማ በኩል ደግሞ ሥራ-አስኪያጁ አቶ አቡሽ፣ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ስራ-አስፈፃሚ አባላት እና የደጋፊዎች ማኅበር አመራሮች ተገኝተዋል። አቶ አቡሽ እና አቶ ሳሙኤል ስምምነቱን በፊርማ ከማፅናታቸው በፊት ተከታዩን መጠነኛ ገለፃ አድርገዋል።

በቅድሚያም አቶ አቡሽ \” እንደሚታወቀው ሲዳማ ቡና ጠንካራ እና አንጋፋ ክለብ ነው። ጎፈሬ አብሮን እንዲሰራ ጥሪ ስናቀርብ በጎ ምላሽ መልሰው አብረውን ለመስራት ስለመጡ በጣም እናመሰግናለን። ከዚህ ቀደም ክለባችን ከጎፈሬ ጋር በትጥቅ አቅርቦት ጉዳዮች አብሮ ሲሰራ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ስምምነቱ አልቆ በአዲስ መልክ እና መንፈስ የተለያዩ ተጨማሪ ነገሮች በሁለታችንም በኩል ተጨምረውበት ነው ውል እያሰርን የምንገኘው። ይህን ስምምነት ለሦስት ዓመታት የሚዘልቅ ነው። በእነዚህ ዓመታት ሲዳማ ቡና እግርኳስ ክለብ በስሩ የሚያስተዳድራቸው ከ20 ዓመት በታች፣ የሴቶች እና የወንዶች ቡድኖች ከጎፈሬ የሚያስፈልጉ የስፖርት ትጥቆችን በስፖንሰርሺፕ የሚቀርብላቸው ይሆናል።\” የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል። አቶ አቡሽ ጨምረው ሲዳማ በሦስቱም ክለቦቹ ጎፈሬን እንደአምባሳደርነት የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራም አመላክተዋል።

መድረኩን በቀጣይነት የተረከቡት አቶ ሳሙኤልም በስፍራው የተገኙ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው ተቋማቸው ከሲዳማ ቡና ጋር ለሁለተኛ ጊዜ እያደረገ ያለውን ስምምነት በተመለከተ ይህንን ብለዋል። \”ሲዳማን ክልል ጎፈሬን እንደማንቂያው ነው የምናየው። ከዚህ ቀደም የነበረው ነገር በተለያዩ መልኩ እድገት አሳይቶ ነው በተመሳሳይ ሁኔታ ይህንን ስምምነት እየፈረመ ያለው። እንደተባለው ስምምነቱ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ ነው። ጎፈሬ በአሁኑ ሰዓት ማምረት እስከቻለበት ደረጃ ድረስ ያሉ ነገሮችን በጠቅላላ በስፖንሰርሺፕ ያቀርባል። በተጨማሪም ክለቡን የማዘመን እና የማርኬቲንግ ስትራቴጂዎችንም ከክለቡ እና ከደጋፊ ማኅበሩ ጋር የሚሰራ ይሆናል። ወደ ውጪም ተደራሽ የሚሆኑ ስራዎችን ለመከወን ዕቅድ ተዟል። እኛም እንደ ጎፈሬ ይህንን ስምምነት በማድረጋችን በጣም ደስተኞች ነን።\”ካሉ በኋላ በቀጣዩ ዓመት ትልቅ ስራ እንደሚጠብቃቸው አመላክተዋል።

አቶ ሳሙኤል በንግግራቸው ማብቂያ \”ሲዳማ ቡና እና ጎፈሬ ትስስራቸው እና አካሄዳቸው ቤተሰባዊ ነው። ጎፈሬ የመጀመሪያ የማርኬቲንግ ስራ የሰራው ከሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ነው። ከዛ ጊዜ አንስቶ አሁንም አብረን እየሰራን ነው። ነገሮች መዘመን ስላለባቸው ውሉን ለማደስ ተነጋግረን ነው አሁን ውሉን እያደስን የምንገኘው።\” ብለዋል።

\"\"


በመጨረሻም ስምምነቱ በፊርማ ከፀና በኋላ የፎቶ መነሳት መርሐ-ግብር ተከናውኖ የዕለቱ ሥነ-ስርዓት ተገባዷል።