ከፍተኛ ሊግ | ሻሸመኔ ከተማ ወደ መሪነት መጥቷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ16ኛ ሳምንት የምድብ ለ ጨዋታ የአንድ ቀን ሽግሽግ ተደርጎበት ዛሬ መደረግ ሲጀመር ሻሸመኔ ከተማ  ከነገ ጨዋታዎች በፊት መሪነቱን የያዘበትን እንጅባራ ተከታታይ ድልን ያሳካበትን ውጤት ሲያስመዘግቡ ቀሪ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
\"\"

3፡00 ሰዓት ሲል አሰልጣኝ መኮንን ገላናህን አሰናብቶ በረዳት አሰልጣኙ የተመራው ሺንሺቾ ከተማ እና ጂንካ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የጂንካ ከተማ ፈጣን ተሻጋሪ ኳሶች በርከተው መታየት በቻለበት የመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ በርካታ አጋጣሚን አግኝቶ በጥብቅ መከላከል ውስጥ የተጠመዱትን የሺንሺቾን የኋላ አጥር ለማለፍ ሲቸገሩ አስተውለናል። በርካታ ጊዜያቸውን በመከላከሉ ውስጥ ያሳለፉት ሺንሺቾዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር በኩል በፈጣን መልሶ ማጥቃት ያገኙትን ተቀይሮ የገባው መልካሙ ፉንዱሬ ጂንካን ቀዳሚ አድርጎ አጋማሹ ተገባዷል።
\"\"

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ሺንሺቾዎች በእጅጉ ተሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱበት እንደሆነ ያስቆጠሩት ግብ ምስክር ነው። ከመልበሻ ክፍል መልስ መሀል ክፍላቸውን በሚገባ አደራጅተው ጥቃትን የጀመረው ቡድኑ 56ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ወደ ቀኝ መስመር አድልታ የተገኘችን ኳስ አማካዩ ቴዲ ታደሠ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ግሩም ጎልን አስቆጥሯል። 61ኛው ደቂቃ ላይ የሺንሺቾው ድልነሳው ሽታው ከዕለቱ ዳኛ ጋር በፈጠረው የቃላት ልውውጥ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል ጨዋታውም ተጨማሪ ግብን ሳያስመለክተን 1-1 ተጠናቋል።

በተደራጀ እና ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተዋቀሩት ሻሸመኔ ከተማ እና ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃንን ያገናኘው ጠንካራ ጨዋታ 5 ሰዓት ሲል በዕለቱ ሁለተኛ መርሀግብር ቀጥሏል። ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብን ይዘው ጨዋታቸውን የጀመሩት ሁለቱ ክለቦች የግብ ሙከራን ገና በጊዜ ነበር ያስመለከቱን። 3ኛው ደቂቃ ላይ የተሻ ግዛው ከኤልያስ ማሞ የደረሰውን በቀላሉ ያመከነበት እና ጌትነት ተስፋዬ እና ፉአድ መሐመድ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ለሻሸመኔ ከተማ ያደረጓቸው ሁለት ሙከራዎች ተጠቃሾቹ ናቸው።
\"\"

አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙን በቅጣት ያጡት እና በበርካታ ደጋፊዎች ፊት ጨዋታቸውን ማድረግን የቀጠሉት ሻሸመኔ ከተማዎች በሁለተኛው አጋማሽ በተደራጀ የአንድ ሁለት አጨዋወት ቀጥለው 62ኛው ደቂቃ ላይ ፉአድ መሐመድ ከመረብ ባገናኛት ብቸኛ ጎል 1ለ0 በማሸነፍ መሪነታቸውን ተቆጣጥረውታል።

ሦስተኛ የዕለቱ ጨዋታ እንጅባራ ከተማን ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ አገናኝቶ በእንጅባራ ድል አድራጊነት ተጠናቋል። ኳስን በመቆጣጠሩ ረገድ የማይታሙት ቂርቆሶች ዛሬም ይህኑን አጨዋወት መሠረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ የተስተዋለ ቢሆንም የቂርቆስን የቅብብል ስህተት በአግባቡ ለመጠቀም ተደጋጋሚ ዕድልን በማግኘቱ የተዋጣላቸው እንጅባራዎች በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ 15ኛው ደቂቃ ላይ በወጣቱ አጥቂ ዳዊት ታደለ ብቸኛ ግብ ተከታታይ ሁለተኛ ድላቸውን አሳክተዋል።
\"\"

የማሳረጊያ ጨዋታ የነበረው ሁለቱን የኦሮሚያ ክለቦች አምቦ ከተማ እና ነቀምት ከተማን ያገናኘው ጨዋታ ጠንከር ባለ ዝናብ ታጅቦ 1ለ1 ተጠናቋል። ረጃጅም ኳሶች በበዙበት በዚህ ጨዋታ 23ኛው ደቂቃ ላይ የነቀምት ከተማ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂን ስህተት ተጠቅሞ ሚልኪ ዘለቀ ወደ ጎል አክርሮ ሲመታ የነቀምቱ የመስመር አጥቂ ቦና ቦካን ጨርፋ ኳሷ ከመረብ አርፋለች። ከመስመር በሚሻገሩ ተለምዷዊ አጨዋወታቸው ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ለመጫወት የተጉት ነቀምቶች ወደ አቻነት መጥተዋል።

በዚህም በሁለተኛው አጋማሽ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊገባደድ ሁለት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩት ተመስገን ዱባ ቡድኑን አቻ በማድረግ 1ለ1 ጨዋታው ሊቋጭ ችሏል።

\"\"