የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ19ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዛሬ ሲጠናቀቅ ቦሌ ክ/ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ተመሳሳይ የ1-0 ድል ቀንቷቸዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 ቦሌ ክ/ከተማ

04፡00 ሲል በጀመረው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ገና በ4ኛው ደቂቃ ግብ ሊቆጠርበት ነበር። የቅዱስ ጊዮርጊሷ ቃልኪዳን ወንድሙ በሳጥኑ  የግራ ክፍል ይዛው የገባችውን ኳስ ኳሱን ገፍታ በወሰደችበት ብቃት ልክ ታስቆጥረዋለች ተብሎ ሲጠበቅ የሞከረችው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል። ካለፉት ጨዋታዎች በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ማስኬድ የቀጠሉት ቦሌዎች በፈጠሩት የመጀመሪያ የጠራ የግብ ዕድል ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ንግስት በቀለ በጥሩ ቅልጥፍና ተከላካዮችን አታልላ በማለፍ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን በእግሯ ስትመልስባት ያንኑ ኳስ ያገኘቸው ጤናዬ ለታሞ መረቡ ላይ አሳርፋዋለች።

ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ውስጥ በጥሩ ቅብብል የታጀበ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው ለመግባት የተቸገሩት ጊዮርጊሶች 35ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። እየሩስ ወንድሙ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ቃልኪዳን ወንድሙ ያደረገችውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶባታል።

ከዕረፍት መልስ አጋማሹ ከተጀመረ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የቦሌዋ ስንታየሁ ኢርኮ ሳጥን ውስጥ ይዛው በገባችው ኳስ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን ስትመልስባት ያንኑ ኳስ ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ በጊዮርጊሶች በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ጤናዬ ለታሞ ስትመታ ግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን አስወጥታባታለች።

\"\"

ከዚህ አጋጣሚ በኋላ በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ አልተደረገበትም። ይሁንና በቦሌዎች በኩል 60ኛው ደቂቃ ላይ ንግሥት በቀለ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ሳትጠቀምበት ስትቀር በጊዮርጊሶች በኩል 71ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ትዕግሥት ወርቄ የግብጠባቂዋን መውጣት ተመልክታ ከሳጥን ውጪ ከፍ አድርጋ የሞከረችው ኳስ በግራው ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ጨዋታውም በቦሌ ክ/ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ 2-2 አዳማ ከተማ

ጥሩ ፉክክር በተደረገበት የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ከረጅም ርቀት በሚደረጉ ዒላማቸውን በጠበቁ ነገር ግን ፈታኝ ባልሆኑ ሙከራዎች ሲታጀብ 5ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማዋ ሳባ ኃይለሚካኤል ከግራ መስመር አክርራ መትታው ግብ ጠባቂዋ ብርሃን ብልቻ ያስወጣችባት ኳስ በአጋማሹ የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። ጨዋታው መኃል ሜዳው ላይ ብልጫ ለመውሰድ ማራኪ ፉክክር ማስመልከቱን ሲቀጥል 34ኛው ደቂቃ ላይ ሣራ ይርዳው እጅግ ድንቅ በሆነ ሩጫ እና አጨራረስ ግብ አስቆጥራ ድሬዳዋ ከተማ አጋማሹን መርቶ እንዲወጣ አስችላለች።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተሻሽሎ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል ረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ተደርጎበታል። በአጋማሹ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አስደናቂ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት አዳማዎችም 52ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ሣሮን ጎሳ ከረጅም ርቀት የመታችው ኳስ የግብ ጠባቂዋ ትኩረት ማጣት ተጨምሮበት ግብ ሆኗል። ኳስ ሲይዙ በእንቅስቃሴ ደረጃ የተሻሉ የሚመስሉት ከኳስ ውጪ ግን ደካማ የነበሩት ድሬዎችም 72ኛው ደቂቃ ላይ አምበሏ መስከረም ኢሳያስ ወርቅነሽ ሚልሜላ ከረጅም ርቀት የመታችውን እና  ግብ ጠባቂዋ ሳትቆጣጠረው የቀረችውን ኳስ በግንባሯ በመግጨት አስቆጥራው ድሬዳዋን በድጋሚ መሪ ስታደርግ 73ኛው ደቂቃ ላይ ግን በጨዋታው አስደናቂ እንቅስቃሴ በማድረግ ኮከብ የነበረችው የአዳማዋ ቅድስት ቦጋለ ከሳጥን ውጪ በድንቅ ሁኔታ የመታችው ኳስ መረቡ ላይ አርፏል። ጨዋታውም 2-2 ተጠናቋል።

ልደታ ክ/ከተማ 0-1 አርባምንጭ ከተማ

በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ልደታ እና አርባምንጭ ሲገናኙ ብዙም ፉክክር ባልነበረበት የመጀመሪያ አጋማሽ አርባምንጮች 14ኛው ደቂቃ ላይ መሠረት ወርቅነህ ከሳጥን ውጪ ባስቆጠረችው ድንቅ ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።

27ኛው ደቂቃ ላይ ሰርካለም ባሳ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርጋ የግቡ የግራ ቋሚ ገጭቶ የመለሰባት እና 42ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም ታምሩ ከቅጣት ምት በቀጥታ መትታው ግብ ጠባቂዋ አክሱማዊት ገ/ሚካኤል የመለሰችው ኳስ ሌሎች በአርባምንጮች በኩል የተደረጉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ልደታዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ከረጅም ርቀት በርካታ ሙከራዎች ቢያደርጉም ያን ያህል ግን ፈታኝ አልነበሩም።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል የአርባምንጯ ቤተልሔም ታምሩ 63ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሞክራው በቀኙ ቋሚ በኩል ለጥቂት የወጣባት እና 67ኛው ደቂቃ ላይ ደሞ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ መትታው የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰባት ኳስ በአጋማሹ የተሻሉት የግብ ዕድሎች ነበሩ። ሆኖም ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"