የአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ይግባኝ ውድቅ ሆነ

ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ተለያይተው የነበሩት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ያቀረቡት አቤቱታ ዳግመኛ ፌዴሬሽኑ ሳይቀበለው ቀርቷል።
\"\"

ባሳለፍነው ዓመት ክረምት ወር ላይ ማለትም ከሐምሌ 01/2014 ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡናን ለማሰልጠን ተረክበው የነበሩት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ክለቡን በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥቂት ጨዋታዎች ላይ ከመሩ በኋላ \’ከክለቡ ጋር በገቡት ስምምነት መሠረት ውጤታማ ማድረግ አልቻሉም\’ በሚል ክለቡ እና አሰልጣኙ ረጅም ርቀትን ሳይጓዙ ነበር እህል ውሀቸው መቋጨት የቻለው። አሰልጣኝ ተመስገን ዳናም \’ውል እያለኝ ነው ልሰናበት የቻልኩት በውሌም መሠረትም ደመወዜ ይከፈለኝ\’ በማለት ከወራት በፊት ለፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ቅሬታቸውን አቅርበው ኮሚቴውም ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ ኢትዮጵያ ቡና የወሰነው ውሳኔ በውሉ መሠረት በአግባቡ የተፈፀመ ነው በሚል ለክለቡ ውሳኔውን ማፅናቱ ይታወሳል።

አሰልጣኝ ተመስገን ዳናም በድጋሚ ለፌዴሬሽኑ ደመወዝ ይገባኛል ውሳኔው ዳግመኛ ይጤንልኝ ሲሉ ከቀናቶች በፊት በድጋሚ በይግባኝ ደብዳቤ መልክ ቅሬታን ያቀረቡ ሲሆን የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ለሁለተኛ ጊዜ ጉዳዩን ካየ በኋላ በውሳኔው ክለቡ ህጉን ጠብቆ ነው ያሰናበተው ስለዚህ ክለቡ የክለቡ ውሳኔ አግባብ ነው በማለት ለይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አሰልጣኙ የከፈሉት ገንዘብ ገቢ መሆኑንም ጭምር በመግለፅ የአሰልጣኝ ተመስገን ዳናን አቤቱታ ውድቅ አድርጎታል።

\"\"