በ17ኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተደረጉ ጨዋታዎች ተከታዩን ምርጥ 11 እና አሰልጣኝ መርጠናል።
አሰላለፍ – 4-3-3
ግብ ጠባቂ
አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን
በቋሚነት ቡድኑ እያገለገለ የሚገኘው አቡበከር ኑሪ በጥሩ ብቃት ላይ እንደሚገኝ በጉልህ እያስመሰከረ የሚገኛል። ይህ ወጣት ግብ ጠባቂ ቡድኑ ተፈትኖ አርባምንጭ ከተማን በረታበት ጨዋታ ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያሳኩ ለጎል የቀረቡ ኳሶችን በማዳን ስኬታማ ጊዜ እያሳልፏል።
ተከላካዮች
ዓለምብርሀን ይግዛው – ፋሲል ከነማ
የአፄዎቹ የቀኝ መስመር ተከላካይ በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ላይ ያለው ድርሻ እያደገ ይገኛል። ወላይታ ድቻን ሲረቱ በተወሰኑ ደቂቃዎች የመስመር አማካይነት ሚናም ጭምር ተወጥቶ የነበረው ተጫዋቹ በጨዋታው የጎል አጋጣሚዎችን ከመፍጠር ባለፈ አንድ ግብ የሆነ ኳስም ለኦሴይ ማዉሊ አመቻችቷል።
በረከት ተሰማ – ለገጣፎ ለገዳዲ
በመከላከል አደረጃጀት ውስጥ ወጥ የሆነ ተከላካይ ማግኘት የተቸገሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች አሁን ሁነኛ የመሐል ተከላካይ ያገኙ ይመስላሉ። ድሬደዋ ከተማን ሲያሸንፉ የኋላ የሜዳ ክፍሉን በመቆጣጠር ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ባለ ብዙ ልምዱ በረከት ተሰማ በሶከር ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ምርጥ አስራ አንድ ውስጥ መካተት ችሏል።
ያሬድ ባየህ – ባህር ዳር ከተማ
የጣና ሞገዶቹ ወልቂጤ ከተማን 4-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፉ የመሃል ተከላካዩ ያሬድ ባዬህ ከራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ የሚያደርጉትን ቅብብል ወደፊት በማሳደግ እና በመከላከሉ ረገድም ለወልቂጤ አጥቂዎች ፈተና ሲሆን ቡድኑ የጨዋታ ብልጫ በተወሰደበት ሰዓት የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሮ የጨዋታውን ሚዛን ወደ ራሳቸው እንዲደፋ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ነበረው።
ካሌብ በየነ – ሀዲያ ሆሳዕና
በሀድያ ሆሳዕና የግራ መስመር የሜዳ ክፍል የሄኖክ አርፊጮን በተለያየ ሁኔታ አለመገኘትን ተከትሎ የመጫወት ዕድል እያገኘ የሚገኘው ወጣቱ የግራ መስመር ተከላካይ ካሌብ በየነ በሲዳማው ጨዋታ ቡድኑ በተሻጋሪ ኳሶች ምንም አይነት ላይ አደጋ እንዳይፈጠርበት በመከላከል ያሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ ለመመረጥ አብቅቶታል።
አማካዮች
ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ለገጣፎ ለገዳዲ
ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘውን ለገጣፎ በሁለተኛው ዙር የተቀላቀለው ሙሉጌታ ለቡድኑ አማካይ ክፍል ጥንካሬ የሆነ ይመስላል። ድሬዳዋ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ራሱን ነፃ አድርጎ ኳስ በመቀበል እና በማሰራጨት ቡድኑ አማካይ ክፍል ላይ ብልጫ እንዲወስድ የጎላ ድርሻ ነበረው።
አለልኝ አዘነ – ባህር ዳር ከተማ
ባህር ዳር ከተማ ወልቂጤን በሰፊ የግብ ልዩነት ሲረታ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ እና በተከላካዮች እና አጥቂዎች መካከል ድንቅ የሆነ መግባባት በመፍጠር ቡድኑ መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ እንዲወስድ ወሳኝ ሚና የነበረው አማካዩ ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታትም ለቡድኑ ግብ ማስቆጠርም ችሏል።
ታፈሰ ሰለሞን – ፋሲል ከነማ
ፋሲል ከነማ ወላይታ ድቻን ባሸነፈበት ጨዋታ የመሀል ሜዳ የበላይነትን ማግኘት ብቻ በቂ አልነበረም። ይልቁኑም በተጋጣሚ ሜዳ ክፍተት ለማግኘት በታታሪነት የታጀበ የታፈሰ የማጥቃት ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነበር። ተጫዋቹ ይህንን በማድረግ አደገኛ ዞኖች ላይ እየተገኘ የማጥቃት ሂደቱን ሲያሳልጥ ተስተውሏል።
አጥቂዎች
ኦሴይ ማውሊ – ፋሲል ከነማ>
በኢትዮጵያ ያለፉትን አምስት ዓመታት በተለያዩ ክለቦች ሲጫወት የምናውቀው አጥቂው ማውሊ ዐፄዎችን በሁለተኛው አጋማሽ ነበር የተቀላቀለው። ፋሲሎች ወላይታ ድቻን ከመመራት ተነስተው ድል ባደረጉበት ጨዋታ ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያገኙ ሁለቱንም ጎሎች በማስቆጠር ቡድኑን ታድጓል።
ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ
የብዙዎችን ትኩረት የሳበው አዲሱ የአዳማ ፈርጥ በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የተጣለበትን ኃላፊነት በከፍተኛ ሁኔታ እየፈፀመ ይገኛል። ቡድኑ መቻልን 3-2 ሲረታም ሁለት ግቦችን በስሙ ማስመዝገብ ሲችል ከውጤታማነቱ ባሻገር ሜዳ ውስጥ ያሳየው ጠንካራ እንቅስቃሴም ለመመረጡ ምክንያት ሆኗል።
ሱሌይማን ትራኦሬ – ለገጣፎ ለገዳዲ
ለገጣፎ ለገዳዲ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛውን ድል ድሬዳዋ ከተማን 2-1 በመርታት ሲያሳካ የአዲሱ ፈራሚያቸው ትራኦሬ ብቃት ድንቅ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ጥሩ ሙከራዎቹን የግቡ ብረት ሲመልስበት ከዕረፍት መልስ ግን ድንቅ በሆነ ክህሎት ቡድኑ አሸናፊ የሆነባቸውን ሁለት ግቦች በማስቆጠሩ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ ሆኗል።
አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ – ለገጣፎ ለገዳዲ
ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባደገበት ዓመት ነጥቦችን መስብሰብ የከበደው ለገጣፎ ለገዳዲ የውድድር ዓመቱን ሁለተኛ ድል አሳክቷል። የክለቡ አዲስ አሰልጣኝ የሆኑት ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ በአመዛኙ ከሹመታቸው በኋላ ወደ ቡድኑ ስብስብ የቀላቀሏቸውን ተጫዋቾች በማቀናጀት በድሬዳዋው ጨዋታ ይዘውት የገቡት የጨዋታ ዕቅድ ተፈላጊውን ውጤት ያስገኘላቸው በመሆኑ የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ አድርገን መርጠናቸዋል።
ተጠባባቂዎች
ሰዒድ ሀብታሙ – አዳማ ከተማ
መሳይ አገኘሁ – ባህር ዳር ከተማ
ፍራኦል መንግሥቱ – ባህር ዳር ከተማ
ግርማ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
ጋቶች ፓኖም – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሐብታሙ ሸዋለም – ኢትዮጵያ መድን
ባዬ ገዛህኝ – ሀዲያ ሆሳዕና
ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ