የለገጣፎ ግብ ጠባቂ ቅጣት ተላለፈበት

በአዳማ ከተማ በተካሄዱ የ17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መነሻነት በሊጉ አስተዳዳሪ በተወሰዱ የዲስፕሊን እርምጃዎች ሁለት ተጫዋቾች እና አንድ ክለብ ተቀጥተዋል።

በድሬዳዋ አንድ ጨዋታ ብቻ የተደረገበት የፕሪምየር ሊጉ 17ኛ ሳምንት በአዳማ ቀጥለው በተደረጉ ጨዋታዎች መጠናቀቁ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም በሰባቱ ጨዋታዎች ላይ የታዩ የዲሲፕሊን ጥሰቶችን ከዳኞች እና ኮሚሽነሮች የደረሰውን ሪፖርት ተከትሎ የሊጉ የውድድር እና ሥነስርዓት ኮሚቴ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

\"\"

ለገጣፎ ለገዳዲ የዓመቱ ሁለተኛ ድሉን በድሬዳዋ ላይ ሲያስመዘግብ ለቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ጋናዊው ግብ ጠባቂ ኮፊ ሜንሳህ የዕለቱ ዳኛ ተከተል ተሾመን በመሳደቡ በጨዋታው መገባደጃ ላይ በቀይ በመውጣቱ የሦስት ጨዋታ ቅጣት እና 3 ሺህ ብር እንዲከፍል ተወስኖበታል። ተጫዋቹ ወደ መልበሻ ክፍል ሲያመራም ተጨማሪ ስድቦችን በዳኞች ላይ በመሰንዘሩ ሦስት ተጨማሪ ጨዋታ እና 3 ሺህ ብር ቅጣት ሲጣልበት በድምሩ ስድስት ጨዋታ እና የስድስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖበታል።

የሲዳማ ቡና ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ አዱኛ ፀጋዬ ሲዳማ ቡና በሀድያ ሆሳዕና 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ በቴክኒክ ክፍል ውስጥ ያለን መስታወት በመስበሩ የአስር ሺህ ብር ቅጣት እና የሰበረውን መስታወት እንዲያሰራ ተወስኖበታል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መድን ደጋፊዎች ከአርባምንጭ ጋር በነበራቸው ጨዋታ ዳኛን በመሳደባቸው ክለቡ የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ሲወሰንበት አማኑኤል ዮሐንስ ኢትዮጵያ ቡና በሁለት በቀይ በመውጣቱ እንዲሁም የኢትዮጵያ መድኑ አጥቂ ሀቢብ ከማል አምስተኛ ቢጫ ካርድ በማየቱ ሁለቱም የአንድ ጨዋታ እና የ1500 ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

\"\"