ሪፖርት | አዞዎቹ ከመመራት ተነስተው ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

አርባምንጭ ከተማ ከመመራት ተነስቶ መቻልን በማሸነፍ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ከሦስት ነጥብ ጋር ተገናኝቷል።

አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ መድኑ ሽንፈት አንፃር የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርጓል። በማሟሟቅ ላይ ሳለ ጉዳት የገጠመው ግብ ጠባቂው መኮንን መርዶኪዮስ በይስሀቅ ተገኝ ሲተካ አሸናፊ ፊዳ ፣ ዮሐንስ ተስፋዬ ፣ ሙና በቀለ ፣ ሱራፌል ዳንኤል እና አህመድ ሁሴን ከአሰላለፍ ውጪ ሆነው በምትካቸው መላኩ ኤልያስ ፣ በርናንድ ኢቼንግ ፣ አካሉ አትሞ ፣ እንዳልካቸው መስፍን እና አላዛር መምሩ ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

መቻሎች በበኩላቸው ከአዳማ ከተማው ሽንፈት ጋር ሲተያይ ውብሸት ጭላሎን በተክለማሪያም ሻንቆ ፣ ዮዳሄ ዳዊትን በኢብራሁም ሁሴን ፣ ደሳለኝ ከተማን በተስፋዬ አለባቸው እንዲሁም ሳሙኤል ሳሊሶን እስከ ውድድሩ መጨረሻ በጉዳት በማይኖረው ፍፁም ዓለሙ ቦታ ተጠቅመዋል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊትም የመቻል ተጫዋቾች የቡድን ፎቶ ሲነሱ ባሳለፍነው ሳምንት ከበድ ያለ ጉዳት አስተናግዶ ከቀሪ የሊጉ ጨዋታዎችን ውጪ የሆነውን አጋራቸው ፍፁም ዓለሙን አስበዋል።

እንደ ስታዲየሙ ድባብ ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 33ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም የሰላ ሙከራ ማስመልከት አልቻለም። ቡድኖቹም በተመሳሳይ ጥንቃቄን መርጠው ለመንቀሳቀስ ሲሞክሩ ያስተዋልን ሲሆን በአንፃራዊነት አርባምንጭ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ሲንቀሳቀሱ ነበር። መቻሎች በተቃራኒ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች በርከት አድርገው ወደ ሜዳ ቢገቡም ከራሳቸው ሜዳ ለመውጣት ሲቸገሩ ተስተውሏል።

ጨዋታው 33ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን በመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ ተቆጥሯል። በዚህም ሳሙኤል ሳሊሶ ከደሳለኝ ከተማ የደረሰውን ተጫዋች ሰንጣቂ ኳስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮት መቻሎች መሪ ሆነዋል። መመራት የጀመሩት አርባምንጭ ከተማዎች ለተቆጠረባቸው ጎል ወዲያው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሞክረው እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም በመቻል ግራ ሳጥን አላዛር መምሩ ተገኝቶ የላከውን ኳስ በቅድሚያ ኤሪክ ካፓይሮ ከዛም ተመስገን ደረሰ በተከታታይ ሞክረውት በተከላካዮች ተመልሷል። አጋማሹም ሌላ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያሳይ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ገና አንደተጀመረ በሰከንዶች ውስጥ የግቡ ባለቤት ሳሙኤል ከግራ መስመር በቀጥታ ጥብቅ ኳስ መትቶ የቡድኑን መሪነት ለማሳደግ ሞክሯል። በ56ኛው ደቂቃ ደግሞ ከነዓን ማርክነህ ጥሩ የኳስ አገፋፍ በማድረግ ተከላካዮችን ቀንሶ የሞከረው ኳስ ሌላ ቡድኑ ሁለተኛ ጎል እንዲያገኝ የሚያስችል ዕድል ነበር። አርባምንጮች በበኩላቸው በ52ኛው ደቂቃ የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ በራሳቸው በኩል አድርገው ዒላማ ስቶባቸዋል።

አሠልጣኝ መሳይ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረው በ70ኛው ደቂቃ ተሳክቶላቸዋል። በዚህም ከቆመ ኳስ የተነሳን አጋጣሚ የመቻል ተከላካዮች በሚገባ ማፅዳር ተስኗቸው ያገኘው ተመስገን ደረሰ በግንባሩ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጭራሽ ግብ ሲያስተናግዱ የወረዱት መቻሎች ከ7 ደቂቃዎች በኋላ ሁለተኛ ግብ አስተናግደው መመራት ጀምረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ኤሪክ ካፓይቶ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በተጨመሩት ደቂቃዎች ላይ የመቻልን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው ሳሙኤል ከቅጣት ምት የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሞክሮ አልተሳካለትም። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በአዞዎቹ አሸናፊነት ተገባዷል።

\"\"