ጎፈሬ እና ወልቂጤ ከተማ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ፈፅመዋል


👉\”…የትጥቅ ችግሮችን ለመቅረፍ ከጎፈሬ ጋር አብረን በመስራታችን ደስተኞች ነን\” አቶ ጌቱ ደጉ

👉\”ስምምነቱን በመፈፀማችን የተሰማንን ታላቅ ደስታ ለመግለፅ እንወዳለን\” አቶ አቤል ወንድወሰን

👉\”…አሁን ግን በሚፈለገው የትጥቅ አይነት ተደራሽ ለመሆን ከጎፈሬ ጋር የፈጠርነው ስምምነት ትልቅ ጥቅም ይሰጠናል\” አቶ ካሚል ጀማል

ከተመሰረተ ገና አምስት አመታት ያስቆጠረው ኢትዮጵያዊው የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ በዋናው የሀገራችን የሊግ እርከን ከሚሳተፉ 16 ክለቦች መካከል ከ15ቱ ጋር አብሮ እንደሚሰራ ይታወቃል። ተቋሙ የቀጣይ ዓመታት ስራዎችን ከወዲሁ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን ከሰሞኑን ከበርካታ ክለቦች ጋርም ስምምነቱን እያደሰ ይገኛል። በዛሬው ዕለት ደግሞ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት አብሮ ለመስራት የአጋርነት የፊርማ ሥነ-ስርዓት አከናውኗል።

\"\"

አዲሱ ገበያ አካባቢ በሚገኘው የጎፈሬ ማምረቻ እና ዋና ሾሩ ሩም በተከናወነው የፊርማ ሥነ-ስርዓት ላይ ጎፈሬን ወክለው ምክትል ሥራ-አስኪያጁ አቶ አቤል ወንድወሰን እንዲሁም በወልቂጤ በኩል የክለቡ የቦርድ ፀሐፊ ረዳት ፕሮፌሰር ጌቱ ደጉ፣ የከንቲባው ቢሮ ተወካይ አቶ ታፈሰ ዳምጠው እና የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ካሚል ጀማል ተገኝተዋል። ፊርማው ከመከናወኑ በፊትም ስለስምምነቱ ገለፃ የተደረገ ሲሆን በቅድሚያም አቶ ጌቱ ተከታዩን ሀሳብ አንስተዋል።

\”እንደዚህ አይነት ስምምነቶች በተለይ ለክለቦቻችን ትልቅ ጥቅም አላቸው ብዬ አስባለው። አብዛኞቹ የሀገራችን ክለቦች ካሉባቸው የተለያዩ ችግሮች አንፃር የአጋርነት ስምምነቶችን ማድረግ አስፈላጊ ነው። እኛም የትጥቅ ችግሮችን ለመቅረፍ ከጎፈሬ ጋር አብረን በመስራታችን ደስተኞች ነን። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ክለቡን በፋይናንስ ለመደገፍ ከደጋፊ ማኅበሩ ጋር ጠንከር ያለ ስራ ሰርተን ደጋፊዎቻችንን በደንብ የምናገኝበት ስምምነት ይሆናል። ከእግርኳስ የራቀውን ደጋፊ ለማምጣትም ጥሩ ስምምነት ነው ብዬ አስባለው። በአጠቃላይ በክለቡ ስም ጎፈሬን ማመስገን እፈልጋለው።\” በማለት በስፍራው ለተገኙ እንግዶች ንግግራቸውን አሰምተዋል። አቶ ጌቱ ጨምረው ባለፉት ሁለት ዓመታት ጎፈሬ ለወልቂጤ ከተማ ያደረገውን ድጋፍ አድንቀው በክለቡ ማሊያ ላይ የሚደረገው አካባቢን እና ሀገርን የሚያስተዋውቅ ቀለም አሁንም በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

በስምምነቱ ጎፈሬ ለዋናው የወንዶች፣ ታዳጊዎች እንዲሁም የሁለቱም ፆታ ቅርጫት ኳስ ቡድኖች 13 አይነት ትጥቆችን የሚያቀርብ ሲሆን በሦስቱ ዓመትም በወጥነት የደጋፊዎች መለያም የሚያስረክብ ይሆናል።

የክለቡ ደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ካሚል ጀማል በበኩላቸው \”ክለባችን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከገባ በኋላ በሚፈለገው ልክ ደጋፊዎቻችንን በደንብ ተደራሽ መሆን አልቻልንም። አሁን ግን በሚፈለገው የትጥቅ አይነት ተደራሽ ለመሆን ከጎፈሬ ጋር የፈጠርነው ስምምነት ትልቅ ጥቅም ይሰጠናል። የደጋፊውንም ፍላጎት ለማሟላት ይህ ስምምነት የተሻለ ዕድል ይፈጥራል ብዬ አስባለው።\” ብለዋል።

ስምምነቱ በፊርማ ከመፅደቁ በፊት መድረኩን የተረከቡት የጎፈሬ ምክትል ሥራ-አስኪያጅ አቶ አቤል ስምምነቱን በተመለከተ ተከታዩን ሀሳብ አጋርተዋል። \”ከወልቂጤ ከተማ ጋር ባለፉት ሁለት ዓመታት አብረን ስንሰራ ነበር ፤ እርግጥ በሁለቱ ዓመታት ከክለቡ ጋር በተደራጀ እና በውል በታሰረ መልኩ አልነበረን ስንሰራ የነበረው። በእነዚህ ጊዜያት የነበሩትን ችግሮች በተለይ ከደጋፊዎች ማሊያ እና አጠቃላይ የክለቡን የትጥቅ ችግር ለመቅረፍ ይህንን ትልቅ ስምምነት ፈፅመናል። በዚህም እንደ ጎፈሬ የተሰማንን ታላቅ ደስታ መግለፅ እፈልጋለው። ደጋፊ ማኅበሩም ሆነ ክለቡ ከትጥቅ እና ከፋይናንስ ጋር ተያይዞ ሲቸገሩ የነበረበት መንገድ ነበር። አሁን ግን የነበሩ ችግሮችን ለማስተካከል ይህንን ስምምነት አድርገናል።\” በማለት አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም ክለቡ ራሱን በገቢ የሚያጠናክርባቸው መንገዶችን በጋራ የመቀየስ ስራ በሦስቱ ዓመት እንደሚሰራ ተጠቁሞ የፊርማ እና የፎቶ መነሳት መርሐ-ግብር ተከናውኗል።

\"\"