የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ21ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዛሬ ሲጀመር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ መቻል እና አዲስ አበባ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።

\"\"

ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ 0-6 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

04፡00 ሲል በደረጃ ሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ ላይ የሚገኙትን ክለቦች ያገናኘው የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፍጹም የበላይነት የታየበት ነበር። መሳይ ተመስገን 34ኛው እና 37ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረችው ግብ አጋማሹን 2-0 መርተው መጨረስ የቻሉት ንግድ ባንኮች ከዕረፍት መልስ ግን ሙሉውን ደቂቃ ከተጋጣሚ የግብ ክልል በማሳለፍ አራት ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል።

\"\"

በቅድሚያም 52ኛው ደቂቃ ላይ መዲና ዐወል በተረጋጋ አጨራረስ ስታስቆጥር በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም አክርራ በመምታት ያደረገቸውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶባታል። 62ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ተቀይራ የገባችው አረጋሽ ካልሳ አስቆጥራለች። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም መዲና ዐወል ካልተጠበቀ ቦታ በቀኙ ቋሚ በኩል ግብ ስታስቆጥር 75ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ግብ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችላለች። ንግድ ባንኮች የግቡን ብዛት ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉበት በርካታ የግብ ዕድል ሲያመክኑ በመጨረሻ ደቂቃዎች ግን በአርያት ኦዶንግ እና በአረጋሽ ካልሳ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለውም ነበር። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 6-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

መቻል 2-1 ቦሌ ክ/ከተማ

ከምሳ መልስ በተደረገው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጠንካራ እንቅስቃሴ ያልታየበት ነበር። የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ብልጫውን የወሰዱት መቻሎች 7ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ ነጻነት ፀጋዬ ከግራ መስመር እየገፋች በመውሰድ ያደረገችው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶባታል። ቦሌዎች በኳሱ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ጥሩ አጀማመር ቢያደርጉም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ተደራጅተው ለመግባት ሲቸገሩ 13ኛው ደቂቃ ላይም ባልተጠበቀ ሁኔታ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። እፀገነት ግርማ ከረጅም ርቀት ያደረገችው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል።  ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት እና በዕረፍት ያልተጠቀሙት መቻሎች 20ኛው ደቂቃ ላይ ግን ነጻነት ፀጋዬ በግራ መስመር ገፍታ በመውሰድ እና አክርራ በመምታት ባስቆጠረችው ግሩም ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በተሳካ የኳስ ቅብብል አይታጀቡ እንጂ በቀላሉ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት መቻሎች 41ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ምስር ኢብራሂም ከግብ ጠባቂዋ ያሳለፈችውን ኳስ የቦሌዋ  ቃልኪዳን ንቅበሸዋ በፍጥነት ደርሳ አስወጥታዋለች።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ የነበሩት ቦሌዎች 47ኛው ደቂቃ ላይ በንግሥት በቀለ አማካኝነት የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለው ነበር። ሆኖም ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የተመለሱት መቻሎች 59ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን በድጋሚ መምራት ጀምረዋል። ምርቃት ፈለቀ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በአስደናቂ ሁኔታ በመምታት መረቡ ላይ አሳርፋዋለች። ከግቧ መቆጠር በኋላም ቦሌዎች በጤናዬ ለታሞ መቻሎች በምርቃት ፈለቀ አማካኝነት የተሻለ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ጨዋታውም በመቻል 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ልደታ ክ/ከተማ 1-2 አዲስ አበባ ከተማ

10፡00 ላይ በተደረገው የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር ብርቱ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ በሁለቱም በኩል ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲደረግበት የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሁለቱም ተቸግረው አሳልፈዋል። የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራም 7ኛው ደቂቃ ላይ በልደታዎች ሲደረግ መዓዛ አብደላ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘቸው ረድዔት ዳንኤል ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ መልሳባታለች። ሆኖም ከአንድ ደቂቃ በኋላ ጥሩ ሙከራ አድርጋ በግብ ጠባቂዋ የተመለሰባት ህድዓት ኳሱ በሴኮንዶች ልዩነት ግብ አስቆጥራ ልደታን መሪ ስታደርግ የልደታዎች መሪነት ግን ከአራት ደቂቃዎች በላይ መሄድ አልቻለም። አዲስ አበባ ከተማዎች ኳስ ሳጥን ውስጥ በእጅ ተነክቷል በሚል ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት ቤተልሔም መንተሎ አስቆጥራዋለች።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 66ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም መንተሎ አመቻትታ ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘቸው ተቀይራ የገባችው አሥራት ዓለሙ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥራው አዲስ አበባ ከተማ ከመመራት ተነስቶ እንዲመራ አስችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት የቻሉት ልደታዎች ሁለት ፈታኝ የሆኑ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። በቅድሚያም 79ኛው ደቂቃ ወደግብ ያደረጉትን ሙከራ ኮከብ የነበረችው ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ በግሩም ቅልጥፍና ስታግድባቸው 85ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ኤልሳ መኮንን ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ሳትቆጣጠረው ቀርታ ያገኘችው ንጋት ጌታቸው ያደረገችውን ሙከራ ተከላካዮች በግሩም ፍጥነት አስወጥተውባታል። ይህም የጨዋታው የተሻለ የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በአዲስ አበባ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"