ከፍተኛ ሊግ | የ18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሀዋሳ እና ባቱ ከተሞች በሚደረጉት ሁለት ምድቦች ስድስት ጨዋታዎችን አስተናግዷል።

በቴዎድሮስ ታከለ እና ጫላ አቤ

ምድብ ለ

የሳምንቱ ቀዳሚ የነበረው እና ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን ጨዋታ 1ለ1 ተቋጭቷል።

\"\"

ንብ እና ነቀምት ከተማን ባገናኘው በዚህ መርሀግብር በመጀመሪያው አጋማሽ የተቆጠሩ ሁለት ጎሎች ናቸው ቡድኖቹን ነጥብ ያጋራው ውጤት የተመዘገበው። ኳስን በመቆጣጠሩ ረገድ 15 ያህል ደቂቃዎችን ተሽለው የታዩት ንቦች በፈጣን የሽግግር አጨዋወት በሚጫወቱበት ነቀምት ከተማዎች 19ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። ከጅምሩ ወደ ጎል ሲደርሱ የነበሩት ነቀምት ከተማዎች የንቡ ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት መዘያጋት ታክሎበት ገዛኸኝ ባልጉዳ ክለቡን መሪ አድርጓል። ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ምላሽ ለመስጠት ጊዜ ያልወሰደባቸው ንቦች በመልሶ ማጥቃት ናትናኤል ሰለሞን የግብ ጠባቂ እና የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ከአንድ ደቂቃ በኋላ አቻ አድርጓቸዋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር መቀዛቀዞች የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ንቦች በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ መስመር ተጥለው ወደ ሳጥን በሚደረጉ ተሻጋሪ ኳሶች ነቀምት ከተማዎች በበኩላቸው ረጃጅም ኳስን መሠረት በማድረግ ልዩነት ለመፍጠር የተንቀሳቀሱ ቢሆንም ተጨማሪ ጎልን ጨዋታው ሳያሳየን በአቻ ውጤት ተደምድሟል።

አምስት ሰዓት ላይ የጀመረው የካፋ ቡና እና አምቦ ከተማ ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተገባዶ በተሰጠ የጭማሪ ደቂቃ ሁለት ጎሎች ካፋ ቡናን ሦስት ነጥብን አሸማቶት ተጠናቋል።

\"\"

ጨዋታው ሲጀመር ካፋ ቡናዎች የተጫዋች ተገቢነት ክስን በአምቦ ተጫዋች ላይ ካስያዙ በኋላ ነበር ጨዋታው የጀመረው። አምቦ ከተማዎች በእንቅስቃሴ እና በሙከራ ረገድ በካፋ ቡና ላይ የበላይነትን ማሳየት ቢችሉም ከፊት የተሰለፉ አጥቂዎች የስልነት ችግሮች ጎልተው ስለሚታዩባቸው በቀላሉ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ተቸግረው ሰንብተዋል። ከአምቦ ከተማዎች ይቋረጡ የነበሩ የቅብብል ኳሶችን በብዛት ለመጠቀም ሲጥሩ ይታዩ የነበሩት ካፋ ቡናዎች በተመሳሳይ አጋጣሚዎችን አግኝተው ሊጠቀሙበት አልቻሉም።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ አምቦ ከተማዎች በይበልጥ ወደ ግብ የሚያቀርባቸውን እንቅስቃሴ አጠናክረው ሲቀጥሉ በአንፃሩ የአሰልጣኝ አምጣቸው ኃይሌው ቡድን ጥንቃቄ አዘልን ጨዋታ መርጠው ሲንቀሳቁ ታይቷል። አምቦዎች 60ኛው ደቂቃ ላይ የካፋ ቡና ተከላካይ በሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ኢብሳ ጥላሁን መቶ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሰግድ መልሶበታል። 

\"\"

ይሁን እና ጨዋታው ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ላይ ከድር ሲራጅ ብልጠቱን ተጠቅሞ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን ጎሎች 90+1 እና 90+4 ላይ ከመረብ አገናኝቶ ጨዋታው በመጨረሻም 2-0 የካፋ ቡና አሸናፊነት ፍፃሜን አግኝቷል።

ከቀትር በኋላ ጥሩ ፉክክርን በሜዳ ላይ ያሳየን የሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን እና እንጅባራ ከተማ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ ሀያ አምስት ደቂቃዎች ላይ በነበረው ፈጣን እንቀስቃሴ ደብረብርሃንን ባለ ድል አድርጎ የተጠናቀቀ ነበር።

በቀዳሚው አርባ አምስት ደቂቃ በእንቅስቃሴ ብቻ የታጀበው የሁለቱ ቡድኖች መርሀግብር መሀል ሜዳ ላይ በመከማቸት የሚደረጉ ቅብብሎች የበዙበት ሲሆን በፈጣን መሀል ለመሀል በሚላኩ ኳሶች እንጅባራዎች በተሻጋሪ ኳሶች ደግሞ ደብረብርሃን ለመጫወት ሞክረዋል አስቻለው ግርማ ለደብረብርሀን ካስቆጠራት እና ከጨዋታ ውጪ ከተባለችው አጋጣሚ ውጪ በአጋማሹ የጎሉ ሙከራዎችን መመልከት አልቻልንም።

\"\"

ሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ሲቀጥል አጀማመሩ ተመጣጣኝ መልክን የያዘ ቢመስልም በመስፍን ኪዳኔ ይመራ የነበረው ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታ በመግባት በመጨረሻው ሀያ አምስት ደቂቃ ጎልን አግኝተዋል። አስቀድሞ 75ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ከመስፍን ኪዳኔ ጋር ጥሩ ጥምረትን ያሳየው የተሻ ግዛው ለአሳልፈው ሰጥቶት የግራ መስመር በኩል የተሰለፈው ተጫዋቹ ወደ ውስጥ ያሻገራትን ኳስ ጥሩ ሆኖ የዋለው መስፍን ኪዳኔ ከመረብ ጋር ቀላቅሏታል። 82ኛው ደቂቃ ላይም በተመሳሳይ መልኩ መነሻውን ከግራ አድርጋ አስናቀ ሞገስ በአግባቡ የሰጠውን ሐይሌ እሸቱ ሁለተኛ ጎል ካደረገ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ የተሻ ግዛው ራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘችውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯት ጨዋታው 2ለ1 ተጠናቋል።

ከከባድ ዝናብ ጋር ተጣምሮ የምድቡ የመጀመሪያ ቀን የማሳረጊያ ጨዋታ የነበረው ጨዋታ በከምባታ ሹንሺቾ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በቂርቆስ እና ከምባታ ሺንሺቾ ጨዋታ በሁለቱም አጋማሾች ቂርቆሶች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫን ቢያሳዩም ወደ ተጋጣሚያቸው ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ገብቶ በማስቆጠሩ ረገድ ግን ውስንኖች ነበረባቸው። ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር የተሻሉ ፉክክሮችን ያስመለከተን ሁለተኛው አጋማሽ ሦስት ጎሎችን አሳይቶናል። 55ኛው ደቂቃ ላይ ጅብሪል ናስር ከቅጣት ምት ቆንጆ ጎልን አስቆጥሮ ቂርቆስን ቀዳሚ አድርጓል።

\"\"

ጎል ካስተናገዱ በኋላ ተጫዋቾችን ለውጠው በማስገባት ወደ ጨዋታ ቅኝት ውስጥ በይበልጥ የገቡት ሺንሺቾዎች
65ኛው ደቂቃ ላይ ድልነሳው ሽታ ወደ ጎል አክርሮ መቶ የቂርቆሱ ግብ ጠባቂ ግርማ ድንቁ የተፋትን ኳስ አምበሉ ውበት አብተው ክለቡን ወደ አቻነት መልሷል። 78ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋአብ ዮሴፍ በመልሶ ማጥቃት አስደናቂ ጎልን አክሎ ጨዋታው በከምባታ ሺንሺቾ 2ለ1 ተደምድሟል።

ምድብ ሐ

በሦስተኛው ምድብ ዛሬ ረፋድ ላይ ስልጢ ወራቤ እና ሮቤ ከተማ ተገናኝተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ስልጢ ወራቤዎች ብልጫ የታየበት እና በኳስ ቁጥጥሩም የበላይነቱን ወስደው ኳስን መሠረት በማድረግ ወደ ፊት ለመሄድ ሲሞክሩ የተመለከትንበት ነበር። የመሀል ክፍላቸውን በሙሀጅር መኪን በመመራት ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያስመለክቱን እና በመስመር በኩል አብዲ ረሀመቶ ድንቅ የሚባል እንቅስቃሴ ተመልክተናል። በሮቤ ከተማ በኩል የኋላ መሥመር ደጀን የሆነው ሶፊያን ገለቱ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያስመለከተን ሲሆን በአጋማሹም ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ሮቤ ከተማዎች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቀልበስ ያሰቡ ቢሆንም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ስልጢ ወራቤዎች ብልጫውን በመውሰድ ሮቤ ከተማዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ ታይቷል። ነገር ግን በሁለቱም በኩል ምንም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው ተጠናቆ ነጥብ ሊጋሩ ችለዋል።

የዕለቱ የምድቡ ሁለተኛ እና የመጨረሻ ጨዋታ 10:00 ላይ ደሴ ከተማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማን አገናኝቷል። የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ እና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። የመሀል ክፍሉን በአዲስ ህንፃ እና በተስሏች ሳይመን የሚመራው ደሴ ከተማ በኳስ ቁጥጥሩ እና በግብ ሙከራ ተሽለው የተገኙ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ደሴ ከተማዎች ያገኙትን ኳስ ከአብዱሠላም ዮሴፍ የተሻገረለትን ኳስ አዲስ ህንፃ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ደሴ ከተማዎች ጨዋታውን መርተው ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ አርጓል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ደሴ ከተማዎች ይበልጡኑ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በ47ኛው ደቂቃ ማናዬ ፋንቱ ከአዲስ ህንፃ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ በመቀየር የደሴ ከተማን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ኮልፌ ክ/ከተማዎች ጫና ፈጥረው ግብ ለማስቆጠር ሲጫወቱ በ59ኛው ደቂቃ ደሴ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት በመሄድ በጥሩ ቅብብል ተስሏች ሳይመን ከአዲስ ህንፃ የተሻገረለትን ኳስ በማስቆጠር የደሴ ከተማ በሰፊ ግብ ኮልፌ ክ/ከተማን በማሸነፍ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

\"\"