ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከአምስት ተከታታይ አቻዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቋል

የብሩክ በየነ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ኢትዮጵያ ቡና ወልቂጤ ከተማን 1-0 እንዲያሸንፍ አድርጋለች።

\"\"

ኢትዮጵያ ቡና ያለግብ ከተጠናቀቀው የሀዋሳው ጨዋታ አንፃር ቅጣት ላይ የሚገኘው አማኑኤል ዮሐንስ እና ብሩክ በየነን በሬድዋን ናስር እና ከጉዳት በተመለሰው መስፍን ታፈሰ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል። ከጥቂት ቀናት በፊት በባህር ዳር የተሸነፉት ሰራተኞቹ ደግሞ ፋሪስ አለዊን በጀማል ጣሰው ፣ አዲስዓለም ተስፋዬን በፍፁም ግርማ እንዲሁም ተመስገን በጅሮንድን በፍፁም ግርማ ቦታ ተክተዋል።

በተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና በፈጣን ጥቃት ጨዋታውን የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች ከሬድዋን ናስር ፣ ሮቤል ተክለሚካኤል እና ጫላ ተሺታ በተነሱ መካከለኛ ርቀት ያላቸው ኳሶች ለግብ ሙከራነት የቀረቡ አደጋዎችን መፍጠር ችለዋል። ሮቤል 13ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት ያደረገው ሙከራ ግን የቡድኑ ቀዳሚ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣ ሙከራ ነበር።
\"\"

ከሮቤል ሙከራ አንድ ደቂቃ በኋላ ተመስገን በጅሮንድ ከሳጥን ውጪ በህዝቄል ሞራኬ የተመለሰ ከባድ ሙከራ ሲያደርግ ወደ ግብ መድረስ የጀመሩት ወልቂጤዎች በቀጣይ ደቂቃዎች ይበልጥ አስፈሪ ሆነዋል። የቡናን ቅብብሎች መሀል ሜዳ ላይ በማቋረጥ በተሻለ የቁጥር ብልጫ ሳጥን ውስጥ ተገኝተው ሙከራዎችን ሲያደርጉም ታይቷል። በዚህም 19ኛው ደቂቃ ላይ የኋላሸት ሰለሞን ጌታነህ ከበደ ያመቻቸለትን ኳስ በቀኝ አቅጣጫ ገብቶ በመምታት ሌላ የኢትዮጵያ ቡናን ግብ ጠባቂ የፈተነ ሙከራ አድርጓል። ተጫዋቹ 21ኛው ደቂቃ ላይ የኩዌኩ ዱሀ ስህተት የተጨመረበት ያለቀለት የግብ አጋጣሚ ከአቤል ነጋሽ ቢደርሰውም ከቅርብ ርቀት አምክኖታል።

የቀዳሚው አጋማሽ ቀሪ ደቂቃዎች በሁለቱ ሳጥኖች መካከል ፈጠን ባሉ ሽግግሮች የታጀበ እንቅስቃሴን አስመልክቶን ወደ ማብቂያው ላይ በሁለቱም በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ተደርገዋል።42ኛ ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከርቀት ኢላማውን የጠበቀ ጠንካራ ሙከራ ሲያደርግ በምላሹ ጫላ ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ ከፋሪስ ጀርባ አምርቶ በግቡ አግዳሚ ሲመለስ መሐመድ ኑርናስር በግንባር ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።
\"\"

ብሩክ በየነን በአንተነህ ተፈራ ቦታ በመተካት ሁለተኛውን አጋማሸን የጀመሩት ቡናዎች ከፍተኛ የማጥቃት ጫና ፈጥረዋል። ቡድኑ ወልቂጤ ከተማዎች ከሜዳቸው እንዳይወጡ በማድረግ በተደጋጋሚ በሰነዘራቸው ጥቃቶች ግብ ለማስቆጠር ቀርቦ ነበር። ከዚህ መካከል 50ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት በጀመረ እንቅስቃሴ በግንባር የተጨረፈ ኳስ ያገኘው ብሩክ በየነ ወደ ግብ መትቶ ፋሪስ አለዊ አምክኖታል። እንዲሁም 55ኛ ደቂቃ ላይ ኃይለሚካኤል አደፍርስ በግራ ሳጥን ውስጥ ተገኝቶ አክርሮ የመታውም ኳስ በፋሪስ ጥርት ድኗል።

በቀጣይ ደቂቃዎች ሰራተኞቹ የተጋጣሚያቸውን ጥቃቶች ቀስ በቀስ በማርገብ ከሜዳቸው መውጣት ጀምረዋል። ሆኖም የቡድኑ የማጥቃት ሽግግር መዳከም የመጨረሻ ዕድሎችን ለመፍጠር እንዳይችል አድርጎታል። ይልቁኑም ደቂቃው ሰባን ሲሻገር የቡናዎች ተደጋጋሚ ሙከራ ተመልሶ መጥቷል። በዚህም 73ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከሳጥን ውስጥ በተከላካዮች አናት ላይ ያደረሰውን ኳስ ነፃ የነበረው ሮቤል ከቅርብ ርቀት ሲስት ከሁለት ደቂቃ በኋላ ፋሪስ አለዊ በተሳሳተ የጊዜ አጠባበቅ ያሳለፈውን ኳስ መሐመድ ኑር ናስር ከግቡ አፋፍ ላይ በግንባር ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት በዉሀቡ አዳማስ መክኗል።
\"\"

ጫን ብለው እስከፍፃሜው የቀጠሉት ቡናዎች በመጨረሻም 87ኛ ደቂቃ ላይ በለስ ቀንቷቸዋል።
ተቀይሮ የገባው አማኑኤል አድማሱ የወልቂጤን የኳስ ምስረታ አቋርጦ ያስጀመረው ጥቃት በኃይለሚካኤል አመቻችነት በብሩክ በየነ አማካይነት ከመረብ ተገናኝቷል። ጨዋታውም በዚሁ በቡና 1-0 አሸናፊነት ተደምድሟል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ ከዕረፍት መልስ የአጨራረስ ችግራቸውን አሻሽለው ለመግባት እንደሞከሩ ጠቅሰው ብሩክ እንቅስቃሴውን አይቶ እንዲገባ በማሰብ ተጠባባቂ እንዳደረጉት ሲስረዱ በቡድኑ ውጤት ቢደሰቱም በእንቅስቃሴው እንዳልረኩ ጠቁመዋል። የወልቂጤው ምክትል አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ዕድሎችን ማምከናቸውን እና በሁለተኛው አጋማሽ መድከማቸውን አስረድተዋል። ጨምረውም ተከታታይ ሽንፈት ቢያገኛቸውም ድክመታቸውን አርመው እንደሚመጡ ተናግረዋል።

\"\"</a