ሪፖርት| የጣና ሞገዶቹ በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ አፄዎቹን አሸንፈዋል

ተጠባቂው በነበረው ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ከመመራት ተነስቶ ፋሲል ከነማን 2-1 በማሸነፍ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሦስት አጥብቧል።

\"\"

ዐፄዎቹ ወላይታ ድቻን ካሸነፈው ስብስባቸው መናፍ ዐወልን በአስቻለው ታመነ ለውጠው ጨዋታውን ሲጀምሩ የጣና ሞገዶችም በበኩላቸው አራት ለአንድ ካሸነፈው ስብስባቸው በአደም አባስን ቦታ ዱሬሳ ሹቢሳን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

እንደተገመተው በፈጣን እንቅስቃሴዎች ታጅቦ በተካሄደው ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከፍተኛ የመሸናነፍ ፍላጎት የታየበት ነበር። ሽመክት ጉግሳ ከኦሴይ ማውሊ የተላከለት ኳስ ተጠቅሞ ባደረገው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩት ዐፄዎቹ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ምንም እንኳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስዱም ሙከራ በማድረግ ረገድ ግን የጣና ሞገዶቹ የተሻሉ ነበሩ። ባህር ዳሮች ካደረጓቸው ሙከራዎችም ዱሬሳ ሹቢሳ በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል የሄደው ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ ፣ ፍፁም ጥላሁን በግንባሩ ገጭቶት ናትናኤል ጨርፎት ወደ ውጪ የወጣው ኳስ እና ፉዓድ ከቆመ ኳስ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

\"\"

በ40ኛው ደቂቃ ግን በቁጥር ጥቂት የጠሩ ሙከራዎች ያደረጉት ዐፄዎቹ በታፈሰ ሰለሞን አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። ጎሏም ኦሰይ ማውሊ ተጋጣሚያቸው በኳስ አመሰራረት ሂደት በፈጠረው ስህተት ተጠቅሞ ለታፈሰ አመቻችቶለት አማካዩ በጥሩ እርጋታ ዕድሉን ወደ ጎልነት የቀየረበት ነበር። በሂደቱ ሽመክት የመጀመርያን ኳስ በማሸነፍ ጥሩ አበርክቶ አድርጓል። የጣና ሞገዶቹ ከግቧ በኋላ በፍራኦል መንግሥቱ አማካኝነት ከቆመ ኳስ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ከግቡ አግዳሚ በላይ ለጥቂት ወጥታለች።

ከዕረፍት መልስ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በዐፄዎቹ ሳጥን ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ያሬድ ባየህ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

\"\"

ከግቧ በኋላም ዐፄዎቹ በናትናኤል ጥሩ የሳጥን ውጭ ሙከራ በኩል አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በ54ኛው ደቂቃ በፋሲል ከነማ በኩል ዓለምብርሀን ይግዛው በፉዓድ ፈረጃ ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

የቁጥር ብልጫ ከወሰዱ በኋላ የእንቅስቃሴ ብልጫ የወሰዱት የጣና ሞገዶቹ በፍፁም ፣ ያሬድ እና አለልኝ ለግብ የቀረበ ሙከራ ቢያደርጉም ሁሉም ሙከራዎች በዐፄዎቹ ጥረት ግብ ከመሆን ተርፈዋል። በተለይም ፉዐድ በነፃ አቋቋም ሆኖ ያደረጋት ሙከራ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። 80ኛው ደቂቃ ላይ ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርገው ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት የጣና ሞገዶቹ ጥረታቸው ሰምሮ ግብ አስቆጥረዋል ፤ ጎሏም በአለልኝ አማካኝነት ከረዥም ርቀት የተቆጠረች ግሩም ግብ ነበረች።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ በተለይም ከቀይ ካርዱ በኋላ ተዳክመው የታዩት ፋሲሎች በአጋማሹ ጥቂት ሙከራዎች ብቻ ነበር ያደረጉት። ከነዚህም በግብ አስቆጣሪው ታፈሰ የተደረገች ሙከራ ትጠቀሳለች።

85ኛው ደቂቃ ላይ ዐፄዎቹ በጨዋታው ሁለተኛ ተጫዋቻቸውን በቀይ ካርድ አጥተዋል። የግራ መስመር ተከላካዩ አምሳሉ ጥላሁን በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ሁለተኛው ተጫዋች ነው። ሁለት ቀይ ካርድ እና ሦስት ግቦች ጨምሮ ሳቢ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታ በጣና ሞገዶቹ አሸናፊነት መጠናቀቁ ተከትሎ ቡድኑ ከመሪው ቅዱስ ግዮርጊስ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሦስት ጠቧል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ የነበሩ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ስህተቶች እና ቀይ ካርዶች ዋጋ እንዳስከፈሏቸው በማንሳት በቀጣይ ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል። አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው የተሻሉ በነበሩበት ሰዓት ጎል ቢያስተናግዱም ተጫዋቾቻቸው የነበራቸውን ተነሳሽነት ሲያደንቁ ከቀይ ካርዱ በኋላ ያደረጓቸው ቅያሪዎች ያሰቡትን ለውጥ እንዳላመጣላቸው አብራርተው ውጤቱ ለቀጣይ ጉዟቸው ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። አሰልጣኙ በተጨማሪ አለልኝ አዘነን ከጎል ማስቆጠር በተጨማሪ ለቡድኑ የሚሰጠውን አገልግሎት በማስረዳት አሞካሽተውታል።

\"\"