የ18ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ቃኝተናቸዋል።
አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ
በአንድ ነጥብ እና አንድ ደረጃ ተበላልጠው የተቀመጡት አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ 4ኛ ደረጃን ለመያዝ የሚያደርጉት ፍልሚያ ትልቅ ትግል ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች ተከታታይ ድል ያስመዘገበው አዳማ ከተማ በመቀመጫ ከተማው በሚያደርገው ሁለተኛ ፍልሚያ አውንታዊ ውጤት ማስመዝገብን እያሰበ ወደ ሜዳ ይገባል። በወጣቶች እና አንጋፎች የተገነባው አዳማ ከተማ በተለይ ለተስፈኛ ተጫዋቾች እየሰጠ ያለው ዕድል በጥሩ ሁኔታ ዋጋ እየከፈለው ይገኛል። በተለይ በአጥቂ መስመሩ ላይ የሚሰለፉት ዮሴፍ ታረቀኝ እና ቢኒያም አይተን የሚሰጣቸውን ዕድል ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት የሚያስገርም ነው። ይህንን ዕድል የፈጠረው አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ነገም በዚህ አስተሳሰቡ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ሲጠበቅ በተለይ ያለዳዋ ሁቴሳ ምርጥ የሆነው የአጥቂ መስመሩ ለሀዋሳዎች ፈተና እንደሚሆን ይታሰባል።
የአሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድን የሆነው ሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ተቆጥረዋል። እርግጥ በእነዚህ ሳምንታት ቡድኑ ሁለት ጊዜ ብቻ ያሸነፈ ቢሆንም ለተጋጣሚዎቹ እጅ አለመስጠቱ ይበል የሚያሰኝ ነው። ይህ ቢሆንም ግን በተለይ በማጥቃቱ ረገድ ያለው አፈፃፀም የተዳከመ ነው። ለተመዘገቡት የአቻ ውጤቶችም ይህ የአጥቂ መስመር ድክመት ዋነኛው ምክንያት ይመስላል። እርግጥ በቦታው ያሉት ተጫዋቾች መጥፎ የሚባሉ ባይሆኑም አሠልጣኙ አጠቃላይ የማጥቃት ውህደቱን ማስተካከል ይገባቸዋል። ነገም በመቀመጫ ከተማቸው የሚፋለሙትን አዳማ ከተማዎች ለመርታት ይህንን ክፍተታቸውን አርመው መምጣት ይገባቸዋል።
ሀዋሳ ከተማዎች ረጅም ጉዳት ላይ የሚገኙትን ብርሀኑ አሻሞ እና ወንድማገኝ ኃይሉን ግልጋሎት በነገው ጨዋታም አያገኙም።
ተጋጣሚዎቹ እስካሁን ድረስ በሊጉ 42 ጊዜ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች 93 ግቦች ሲመዘገቡ 48 በሀዋሳ ከተማ 45 ደግሞ በአዳማ ከተማ ስም ተቆጥረዋል። ሀዋሳ 18 አዳማ ደግሞ 12 ጊዜ ድል ሲቀናቸው በቀሩት 12 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል።
ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ቢኒያም ወርቅአገኘሁ እንዲሁም ካሳሁን ፍፁም እና አብዱ አሊ በረዳትነት በተጨማሪም ዳንኤል ግርማይ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ወላይታ ድቻ
በሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በተመሳሳይ ሽንፈት ያስተናገዱት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወላይታ ድቻ ነገ ምሽት በ18ኛ ሳምንት ጨዋታ ይገናኛሉ።
የለገጣፎን ማሸነፍ ተከትሎ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ራሳቸውን ያገኙት ኤላክትሪኮች በመጡበት ዓመት ተመልሰው ላለመውረድ ወደ ድል መመለስ ሁለተኛ ዕቅድ የሌለው ሀሳባቸው ነው። ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ራሱን በዝውውሮች ካጠናከረ በኋላ በእንቅስቃሴ መሻሻሎችን ቢያሳይም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ከመሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ጋር መገናኘቱ ጥሩ አጋጣሚ አይመስልም። ከድል ከራቀ 13 ጨዋታዎች ያለፉት ኤሌክትሪክ በተለይም በማጥቃት ወቅት ተነጥለው በሚታዩ ጥቂት ተጫዋቾች ብቻ የሚያደርገው ጥረት ለተጋጣሚዎች ምቹ ሆኖ ይታያል። በዚህ ረገድ አዲስ ፈራሚው ፍፁም ገብረማርያምን ለመጀመሪያ ጊዜ አካቶ በሚያደርገው የነጉው ጨዋታ ተሻሽሎ ሊቀርብ እንደሚችል ይገመታል።
10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወላይታ ድቻዎች ከተጋጣሚያቸው በብዙ ርቀት የተሻለ ሁኔታ ላይ ቢገኙም ወቅታዊ አቋማቸው ግን ጥሩ የሚባል አይደለም። ከመጨረሻው ድል በኋላ አምስት ጨዋታዎች ያሳለፈው ወላይታ ድቻ ሦስቱን ነጥብ በመጋራት ቢጨርስም ያስቆጠራቸው ግቦች ግን ሁለት ብቻ ናቸው። በተደራጀ ሁኔታ በመከላከል የማይታማው ቡድኑ ከዓምና በተሻለ ዘንድሮ ወደ ፊት ገፍቶ የማጥቃት ፍላጎት ኖሮት ቢታይም ጥረቱ የሚፈልገውን ውጤት አላመጣለትም። በዚህ ረገድ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በስብስባቸው ውስጥ ያሉ አጥቂዎችን በተለያዩ ጥምረቶች በመጠቀም ግቦችን ለማግኘት ሲጥሩ ይታያል። በነገውም ጨዋታ የቡድኑ ዋነኛ ትኩረት የፊት መስመሩ አፈፃፀም እንደሚሄን ዕሙን ነው።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 11ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ 3 ጊዜ ሲያሸንፍ ድቻ 2 አሸንፏል። በስድስቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ዕኩል ሰባት ጎሎችም አስቆጥረዋል።
ይህንን ጨዋታ አባይነህ ሙላት በመሀል ዳኝነት ፣ ለዓለም ዋሲሁን እና ሰብስቤ ጥላሁን በረዳት ዳኝነት ፣ ሶሬሳ ካሚል በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።