የቃልኪዳን ዘላለም እና ልደቱ ለማ ጎሎች የምሽቱ ጨዋታ በ1-1 ውጤት እንዲቋጭ አድርገዋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ኢብራሂም ከድር እና ልደቱ ለማን ከቅጣት በተመለሰው አብነት ደምሴ እና አብዱርሀማን ሙባረክ ተክቶ ሲቀርብ በአንፃሩ ወላይታ ድቻ በፋሲል ከነማው ሽንፈት የተጠቀመበትን አሰላለፍ ሳይለውጥ ወደ ሜዳ ገብቷል።
ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል በሚሰነዘሩ ደካማ የማጥቃት ሙከራዎች እና በሚቆራረጡ ቅብብሎች የጀመረ ነበር። አስሩ ደቂቃ ካለፈ በኋላ ግን ወላይታ ድቻዎች የተጋጣሚን ቅብብሎች በማቋረጥ እና በቶሎ ወደ ግብ በመድረስ በኩል ተሽለው ታይተዋል። ሆኖም ቡድኑ በኤሌክትሪክ ሳጥን ውስጥ ተፈላጊውን ውሳኔ ባለማሳለፉ በቃልኪዳን ዘላለም ፣ ቢኒያም ፍቅሬ እና ዘላለም አባቴ አማካይነት የተደረጉት መከራዎቹ ፈታኝ የሚባሉ አልሆኑም። የኢትዮ ኤሌክትሪኮች ቅብብል በቀላሉ የሚበላሽ እና ለወላይታ ድቻዎች ጥቃት ሁነኛ መነሻ ሆኖ እየታየ በቀጠለው ጨዋታ 29ኛው ደቂቃ ላይ ብልጫቸውን ማስቀጠል የቻሉት ድቻዎች ጎል አስቆጥረዋል።
ቃልኪዳን ዘላለም ኳስ እየገፋ ያስጀመረው ጥቃት ለአይን ማራኪ በሆነ መልኩ በቢኒያም ፍቅሬ ቀጥሎም በአበባየሁ አጂሶ ንክኪዎች ውስጥ አልፎ ራሱ ቃልኪዳን በድንቅ አጨራረስ ጎል አድርጎታል። ከግቡ በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከመጀመሪያው በተሻለ ወደ ወላይታ ድቻ የሜዳ ክፍል በቅብብሎቻቸው መድረስ ቢችሉም የረባ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ተጋምሷል።
ዘላለም አባቴ ከቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መትቶ ለጥቂት በግቡ አናት በወጣበት ኳስ ጠንከር ያለ የሁለተኛ አጋማሽ አጀማመር ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች ብዙም ሳይቆይ የኋላ መስመራቸው በተዘናጋበት ቅፅበት ጎል አስተናግደዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር በረጅሙ የተላከውን ኳስ ስንታየሁ ዋለጬ ነፃ ሆኖ ሲያመቻች ተቀይሮ የገባው ልደቱ ለማ ከአምስት ከሀምሳ ውስጥ አስቆጥሮ ኢትዮ ኤሌትሪክን አቻ አድርጓል።
በቀጣይ ደቂቃዎች ድቻዎች ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ቃልኪዳን አማካይነት የግብ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ኤሌትሪኮችም ከመጀመሪያው በተሻለ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲሞክሩ ታይቷል። የተጋጋለ ይመስል የነበረው ፉክክር ግን በሂደት በሁለቱም አቅጣጫዎች ዕድሎችን ለመፍጠር ከሚደረጉ ጥረቶች ውጪ የተለየ ለጎል የቀረበ ሙከራን ሊያሳየን አልቻለም። በጨዋታ ውጪ ውሳኔዎችም ጭምር ሲቋረጡ ከነበሩ የማጥቃት ሂደቶች ባለፈ ቡድኖቹ ከቆሙ ኳሶችም ጭምር ደካማ አፈፃፀም አሳይተዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት ግን ተቀየሮ የገባው የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ተካልኝ አሰፋ ከረጅም ቅጣት ምት በተገኘ አጋጣሚ ከቅርብ ርቀት ያለቀለት አጋጣሚ ቢያገኝም ለቡድኑ እጅግ ወሳኝ የነበረውን ዕድል በማይታመን መልኩ አባክኗል። ጨዋታውም በ1-1 ውጤት ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ቡድናቸው በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ለተጋጣሚው መጫወቻ ቦታ ከመተው ይልቅ ተጭኖ መጫወት እንዲጀምር ማድረጋቸውን አብራርተው ልደቱ ለማ ተቀይሮ በመግባት ጥሩ መንቀሳቀሱን አንስተዋል። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ በሁሉም ረገድ የተሻሉ እንደነበሩ አንስተው በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው መመጣጠኑን በማስረዳት የተጋጣሚያቸውንም አቀራረብ አድንቀዋል። ጨምረውም ፊት መስመር ላይ የሰሯቸው ጥቃቅን ስህተቶች ሙሉ ውጤት ይዘው እንዳይወጡ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል።