መረጃዎች | 75ኛ የጨዋታ ቀን

የ18ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች እንደሚከተለው ተቃኝተዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ድሬዳዋ ከተማ

24 ነጥቦች እና 21 ነጥቦችን በመያዝ 6ኛ እና 11ኛ ላይ የሚገኙትን ቡድኖች የሚያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር  ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።

ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ሲዳማ ቡናን 1-0 በመርታት ወደ ድል የተመለሱት ሆሣዕናዎች ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ሁለት ግብ ብቻ ማስቆጠራቸው ግን የአጥቂ መስመራቸውን በጥልቅ እንዲፈትሹ የሚያስገድድ ነው። ነገር ግን በአንጻራዊነት አራት ግቦች ብቻ ማስተናገዱ ደግሞ ቡድኑ ጠጣር የመከላከል አጨዋወቱን በጥቂቱም ቢሆን አጥብቆ እንደያዘ ያመላክታል።
\"\"
በመቀመጫ ከተማቸው አስደናቂ አጀማመር ማድረግ ችለው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች አሁን ያሉበት ወቅታዊ ብቃት ግን እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ተከታታይ አራት ጨዋታዎችን ተሸንፎ የነበረው ቡድኑ ሲዳማ ቡናን ሲያሸንፍ ያገግማል ተብሎ ቢጠበቅም በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ በሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ ግን ያልተጠበቀ ሽንፈት አጋጥሞታል። ክለቡ ባለበት ደረጃ ደስተኛ ያልሆኑት  አመራሮችም አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይን በማሰናበት በምትካቸው አሰልጣኝ አሥራት አባተን ለመቅጠር መስማማታቸው ተሰምቷል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ቤዛ መድህን በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ነው። በድሬዳዋ ከተማ በኩል ግን ምንም የጉዳት ዜና የለም።

ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና በሊጉ ሰባት ጊዜ ተገናኝተዋል። ሀዲያ ሆሳዕና ሦስቱን ሲረታ ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ሁለቱን አሸንፎ ቀሪውን ሁለት ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ሆሳዕና 11 ድሬዳዋ ደግሞ 8 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

በጨዋታው ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ሀብተወልድ ካሳ በረዳትነት እንዲሁም ባህሩ ተካ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ኢትዮጵያ መድን

የሣምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ባለፈው የጨዋታ ሣምንት ያልተጠበቀ ድል የተቀዳጀውን ለገጣፎ ለገዳዲን በደረጃ ሰንጠረዡ ከመሪዎቹ ተርታ ከሚገኘው ኢትዮጵያ መድን ጋር ሲያገናኝ ሁለቱም ካላቸው ወቅታዊ የጨዋታ ስሜት አንጻር ብርቱ ፉክክር እንደሚያደረጉበት ይጠበቃል።

በመጀመሪያው የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ከረቱ በኋላ ሦስት አቻዎችን አስመዝግበው በ 12ቱ የተሸነፉት ለገጣፎዎች ባለፈው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ግን ተጫዋቾቹ አዲስ የተዋቀሩ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ አብረው የቆዩ የሚያስመስል ድንቅ ቅንጅት ሲያሳዩ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የመረጡት የጨዋታ መንገድ ነገም ይጠበቃል። በተለይም አዲሱ ፈራሚያቸው አጥቂው ሱሌይማን ትራኦሬ ያሳየው ግሩም እንቅስቃሴ እና ክህሎቱን በሚያሳይ መልኩ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች በነገው ጨዋታም መነቃቃት እንደሚፈጥሩለት እና ለመድን ተከላካዮችም ፈተና ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
\"\"
በደረጃ ሰንጠረዡ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በስድስት ነጥቦች ዝቅ ብለው ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች ከመሪው ጋር ያላቸውን ነጥብ ለማጥበብ ብርቱ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም ለመጨረሻ ጊዜ በሰባተኛው እና በስምንተኛው የጨዋታ ሳምንት ብቻ ተከታታይ ድል ያስመዘገቡት ኢትዮጵያ መድኖች ከመጨረሻዎቹ ዘጠኝ ጨዋታዎች ግን አራቱን ብቻ ሲያሸንፉ በሦስቱ አቻ ወጥተው ሁለት ጊዜ ሽንፈት አጋጥሟቸዋል። አጥቂያቸው ሲሞን ፒተር ግብ ወደ ማስቆጠር መምጣቱ እንደ መልካም ዜና ቢቆጠርላቸውም በወራጅ ቀጠናው ለማንሠራራት ከሚገባው ለገዳዲ የሚጠብቃቸው ፈተና ግን ቀላል አይሆንም።

ለገጣፎ ለገዳዲ ዘነበ ከድር ከጉዳቱ ሲያገግምለት የግብ ዘቡ ኮፊ ሜንሳህ ግን በቅጣት ግልጋሎት አይሰጠውም።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት ፍልሚያ ኢትዮጵያ መድን 4ለ1 አሸንፏል።

ዳንኤል ግርማይ በመሀል ዳኝነት፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳትነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።