ሪፖርት | ብርቱካናማዎቹ ከመመራት ተነስተው ነብሮቹን ረተዋል

ድሬዳዋ ከተማ በቢኒያም ጌታቸው እና አቤል አሰበ ጎሎች ሀድያ ሆሳዕናን 2-1 አሸንፏል።

\"\"

ሀድያ ሆሳዕናዎች ባለፈው ሳምንት ካሸነፈው ስብስብ ያሬድ በቀለ ፣ ዳግም ንጉሴ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ ፣ ፀጋዬ ብርሀኑን ፤ በፔፔ ሰይዶ ፣ ብርሀኑ በቀለ ፣ መለስ ሚሻሞ እና ሬችሞንድ አዶንጎ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ድሬዳዋ ከተማዎችም ከለገጣፎው ሽንፈት እንየው ካሳሁን በቢንያም ጌታቸው በመቀየር ነበር ጨዋታቸውን የጀመሩት።

በተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የጀመረው የመጀመርያው አጋማሽ ምንም እንኳ ማራኪ እንቅስቃሴ ባያስመለክትም በጥራት ደረጃ የወረዱ ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች ተደርገውበታል። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቻቸው ያሬድ ታደሰ በጉዳት ያጡት ብርቱካናማዎቹ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በቻርለስ ሙሴንጌ እና ቢንያም ጌታቸው ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በተለይም ቢንያም በሀድያ ተጫዋቾች አለመናበብ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ ለግብ የቀረበች ነበረች።

በጨዋታው ዕድል በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩ ብርቱካናማዎቹ በቢንያም እና ኤልያስ አማካኝነትም ተጨማሪ ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ችግር ወደ ጎልነት መቀየር አልቻሉም። በአጋማሹ ሁለት ዒለማቸውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ ያደረጉት ሀድያዎች በአርባ ሥስተኛው ደቂቃ በሬችሞንድ አዶንጎ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል።

በውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ግብ ያስቆጠረው ይህ ጋናዊ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን መትቶት ግብ ጠባቂው የተፋውን ኳስ ነበር ወደ ግብነት የቀየረው።

ከዕረፍት መልስ መሐመድ ዓብዱለጢፍ በተሰለፈበት መስመር ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ብርቱካናማዎቹ በሀምሳኛው ደቂቃ በቢንያም ጌታቸው አማካኝነት ግብ አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል። አጥቂው ከመስመር የተሻማው ኳስ ተከላካዮች ከጨረፉት በኋላ በጥሩ መንገድ አብርዶ ነበር አስረኛ የሊግ ግቡ ያስቆጠረው።

ሀድያዎች ግን ከግቡ በኋላ ደግመው የጨዋታ ብልጫ ለመውሰድ ጊዜ አልፈጀባቸውም። ብልጫው ተከትሎም በባየ ገዛኸኝ እና ግርማ በቀለ አማካኝነት ግብ ያልሆኑ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል።

በዓብዱለለጢፍ የቆመ ኳስ አማካኝነት ሙከራ ካደረጉ በኋላ ተቀዛቅዘው የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በስልሣ ዘጠነኛው ደቂቃ በአቤል አሰበ ግሩም የረዥም ርቀት ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ግቧም የተጫዋቹ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ግቡ ሆና ተመዝግባለች።

ከግቧ በኋላም ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋቾች ቅያሬ አድርገው ጨዋታው ቢቀጥሉም ሀድያ ሆሳዕና ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጭ በብርቱካናማዎቹ በኩል ይህ ነው የሚባል የጠራ ዕድል አልተፈጠረም።

በሰማንያ አምስተኛው ደቂቃም ተመስገን ብርሀኑ በሁለት አጋጣሚዎች ቡድኑን አቻ ማድረግ ተቃርቦ ነበር። በተለይም ተጫዋቹ ከግብ ጠባቂው ፊትለፊት ተገናኝቶ ፍሬው በጥሩ ብቃት ያወጣው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ትልቁ የግብ ዕድል ነበር። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ባዬ ገዛኸኝ ሞክሮት ፍሬው እንደምንም ያወጣው እና ካሌብ በየነ ከርቀት አክርሮ መቶት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወሳኝ ሙከራዎች ያዳነው ፍሬው ያወጣው ኳስ ሀድያን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ዕድሎች ነበሩ።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ማራኪ እንቅስቃሴ ያስመለከው ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"