ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ18ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ18ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአንፃራዊነት የተሻለ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው በምርጥ ቡድናችን አካተናል።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ : 4-3-3

ግብ ጠባቂ


ፍሬው ጌታሁን – ድሬዳዋ ከተማ

በዚህ ሳምንት ምርጥ ብቃት አሳይተው ቡድናቸው ተሸክመው ከወጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ፍሬው ጌታሁን ነው። ብርቱካናማዎቹ ከመመራት ተነስተው ባሸነፉበት ጨዋታ በርካታ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎችን ያከሸፈው ይህ ተጫዋች ምርጥ ሳምንት አሳልፏል። ተጫዋቹ በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያከሸፋቸው ሙከራዎች የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

ተከላካዮች


መድሀኔ ብርሃኔ – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ድል በተቀናጀበት ጨዋታ ዕረፍት አልባው የመስመር ተመላላሽ ለውጤቱ አስተዋጽኦ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል የጎላ ተሳትፎ ነበረው። በመስመር በኩል የአዳማን ፈጣን የሽግግር አጨዋወት ከማቋረጥ በዘለለ ክለቡ ለማጥቃት በሚዳዳበት ሰዓት ወደ ፊት እየተሳበ ሲጫወት የተመለከትን ሲሆን ሁለተኛዋን ጎል ክለቡ ሲያስቆጥር ለቅጣት ምቱ መገኘት ዋነኛ ምክንያት መሆን በመቻሉ በሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ አካተነዋል።

\"\"

ያሬድ ባዬህ – ባህር ዳር ከተማ

የጣና ሞገዶቹ ዐፄዎቹ ላይ በፕሪሚየር ሊጉ ግንኙነታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ድል ሲቀዳጁ ከቡድኑ አምበል ያሬድ ባዬህ የሚነሱ ኳሶች በቡድኑ የጨዋታ ዕድገት ላይ የነበራቸው አስተዋጽኦ ወሳኝ ነበር። የመሀል ተከላካዩ ቡድኑ ወደ አቻ እንዲመጣም በተረጋጋ ሁኔታ የፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠርም ችሏል። ከውጤታማነቱ ባሻገር ቡድኑን በመራበት መንገድ በተከታታይ ሳምንት ምርጥ ቡድናችን ውስጥ ሊካተት ችሏል።

እያሱ ለገሰ – ድሬዳዋ ከተማ

ብርቱካናማዎቹ ከረዥም ጊዜ በኋላ ሙሉ ሦስት ነጥብ ሲያገኙ የተከላካይ ክፍሉ እና ግብ ጠባቂው ያደረጉት ተጋድሎ ቀላል አልነበረም። በነበረው ድርሻ ከተከላካዮቹ ጎልቶ የወጣው ደግሞ እያሱ ለገሰ ነው ፤ በተለይም ተጋጣምያቸው ብልጫ በወሰደባቸው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያቋረጣቸው ወሳኝ ኳሶች እና የነበረው የጨዋታ ፍላጎት በቦታው ተመራጭ አድርጎታል።

ደስታ ደሙ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ ጥሩ ብቃት ካሳዩት አንዱ ደስታ ደሙ ነው። በጨዋታው አንድ ለግብ የሆነ ኳስ ያቀበለው ይህ ተጫዋች የፈረሰኞቹን የመስመር አጨዋወት ለማክሸፍ ያሳየው ትጋት እና ጥሩ እንቅስቃሴ ካመቻቸው ግብ የሆነ ኳስ ጋር ተዳምሮ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

አማካዮች


አለልኝ አዘነ – ባህር ዳር ከተማ

ሊጉ ላይ ካሉ ድንቅ የተከላካይ አማካዮች አንዱ መሆኑን እያስመሰከረ የመጣው አለልኝ አዘነ እጅግ ስኬታማ በሆኑ ቅብብሎቹ እና ዙሪያውን አጥርቶ በማየት የሚፈጥራቸው የግንኙነት መስመሮች አድናቆት እያስተረፉለት ይገኛሉ። ከረጅም ርቀት በሊጉ ከታዩ ድንቅ ግቦች ውስጥ አንዱ የሆነ ግብ በማስቆጠርም ባህርዳር ከተማን ለድል ማብቃቱ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ ያደርገዋል።

ባሲሩ ዑመር – ኢትዮጵያ መድን

ኢትዮጵያ መድን በጎሎች በተንበሸበሸበት ጨዋታ ባሲሩ ለጎሎቹ መገኘት ሁነኛ የመነሻ ምንጭ ሆኖ አገልግሏል። መድኖች አብዛኛውን የጥቃት ምንጫቸው ከመሐል ክፍሉ አድርገው ሲንቀሳቀሱ አማካዩ ከጎኑ ከተሰለፉ ተጫዋቾች ጋር የፈጠው ተግባቦት እና ከመስመር አጥቂዎች ኳስን ያገናኝ የነበረበት ሒደት እጅግ ድንቅ ከመሆኑ ባሻገር ከተቆጠሩ ሰባት ጎሎች የሁለቱ ቀጥተኛ መነሻ መሆን በመቻሉ የሳምንቱ የምርጥ ስብስብ አካል አድርገነዋል።

ሀብታሙ ንጉሴ – ወላይታ ድቻ

የጦና ንቦቹ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ሲጋሩ በተለይ በመጀመሪያው አጋማች የተሻለ ሲንቀሳቀሱ አማካዩ ሀብታሙ ንጉሴ ያሳየው ብቃት መልካም የሚባል ነው። አማካዩ በዋናነት ከአጋሩ ንጋቱ ጋር በመሆን የተጋጣሚን የኳስ ቅብብል እያቋረጠ ለመልሶ ማጥቃት መነሻ የሆኑ ዕድሎችን ሲያስጀምር የተስተዋለው ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ጫናዎች በበረከቱ ጊዜም በጥሩ መታተር ለኋላ ክፍሉ ደጀን ሲሆን ነበር።

አጥቂዎች


ዓሊ ሱለይማን – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን በሜዳው ሲረታ የኤርትራዊው አጥቂ የጎላ እንቅስቃሴ ለክለቡ የውጤት መገኘት አስተዋጽኦው የጎላ ነበር። ከተሰለፈበት የቀኝ መስመር በኩል በተለይ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከተከላካይ ጀርባ እየሮጠ ቡድኑ ሦስት ነጥብን ይዞ እንዲወጣ በብርቱ የታገለው የመስመር አጥቂው አብዱልባሲጥ በጨዋታ አቤኔዘር ከቆመ ኳሶች የድል ግቦችን ሲያስቆጥሩ ሁለቱንም ኳሶች አመቻችቶ በመስጠት ሚናው ላቅ ያለ በመሆኑ በምርጥነት ተካቷል።

ቢንያም ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ

ብርቱካናማዎቹን የረዱ አስር ግቦች በማስቆጠር በግሉ ጥሩ ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ቢኒያም ጥሩ የጨዋታ ሳምንት አሳልፏል። አጥቂው ከሀድያ ጋር በነበረው ጨዋታ ቡድኑን ወደ ፉክክር የመለሰች ቀዳሚ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ከጎልም ባለፈ በፈጣን እንቅስቃሴ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች ሲረብሽ የነበረበት መንገድ የሚደነቅ ነበር።

ሲሞን ፒተር – ኢትዮጵያ መድን

መድኖች ሰባት ጎሎች ባስቆጠሩበት የለገጣፎው ጨዋታ ላይ በተለይ ከዕረፍት በኋላ ላደረጓቸው የሰሉ ጥቃቶቻቸው የዩጋንዳዊው አጥቂ ሲሞን ፒተር ሚና ጠጠር ያለ ነበር። ከዕረፍት በፊት ሁለተኛ ግብን ብሩክ ሲያስቆጥር አመቻችቶ የሰጠው እና ከዕረፍት መልስ ሁለት ግቦችን ከመረብ ያገናኘው አጥቂው ጎል ከማስቆጠሩ በዘለለ ለለገጣፎ ተከላካዮች ራስ ምታት ሆኖ በማሳለፉ በምርጫችን ተካቷል።

አሠልጣኝ


ደግ አረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ድንቅ የሆነ መሻሻል እያሳየ የመጣው ባህርዳር ከተማ ላለበት የተፎካካሪነት ደረጃ የአሰልጣኙ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ከሜዳ ውጪ ላለው የቡድን መንፈስ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የሚታወቁት አሰልጣኙ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ቡድናቸው ፋሲል ከነማን ከመመራት ተነስቶ 2-1 በማሸነፍ ከመሪው ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሦስት ሲያጠብ የተጫዋቾቹን በራስ መተማመን በማሳደግ የመረጡት የጨዋታ እንቅስቃሴ የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ተመራጭ አሰልጣኝ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

\"\"

ተጠባባቂዎች

መሐመድ ሙንታሪ
ጊት ጋትኩት
ጀሚል ያቆብ
አብዱልባሲጥ ከማል
ሮቤል ተክለሚካኤል
ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን
መሐመድኑር ናስር
ፍሊፕ አጃህ