ዛሬ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ \’ለ\’ እና \’ሐ\’ ስድስት ጨዋታዎች ሲደረጉ ሀምበርቾ ዱራሜ ወደ መሪነት ተመልሷል።
በቴዎድሮስ ታከለ እና ጫላ አቤ
ምድብ ለ
ማለዳውን ቀዳሚ ሆኖ የተጀመረው የንብ እና ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ጨዋታ 4 ሰዓት ሲል ተጀምሯል። ብዙም ሙከራዎችን ለማየት ባልታደልንበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ አንፃር የተሻሉ ሙከራዎች ያየንበት ቢሆንም ከጎል ጋር የሚገናኙ አጋጣሚዎችን ግን ለማየት አልታደልንም በጨዋታው ከተደረጉ ሁለት ሙከራዎች ንቦች በናትናኤል ሰለሞን ደብረብርሃኖች በበኩላቸው ገናናው ረጋሳ ከመስመር አሻምቶ ኃይሌ እሸቱ ወደ ጎል አክርሮ መቶ ታሪክ ጌትነት ሲመልሰው መስፍን ኪዳኔ ለጥቂት ካመለጠችው ኳስ ውጪ ጨዋታው ከነበረው ደብዛዛ መልክ አንፃር 0-0 የተጠናቀቀ ሆኗል።
በቀጣዩ ጨዋታ በጎዶሎ ተጫዋቾች 89ኝ ደቂቃ ሙሉ የተጫወቱት ጉለሌ ክፍለ ከተማዎች አንድ ነጥብን ከቦዲቲ ይዘው ወጥተዋል። ጨዋታው በጀመረ በ56ኛው ሰከንድ የጉለሌው የግራ መስመር ተከላካይ ተረፈ ተሾመ በቦዲቲው አጥቂ ማሞ አየለ ላይ የሰራውን አደገኛ ጥፋት ተከትሎ በቀይ ካርድ ከሜዳ በመወገዱ ቡድኑ የቀሩት ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋቾች ለማጠናቀቅ ተገዷል። ጠንካራ የሜዳ ላይ ፉክክርን ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ ቦዲቲ ከተማዎች ከፊት በተሰለፉ አጥቂዎቻቸው ታግዘው ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉትን ሒደት ተመልክተናል። ቦዲቲዎች በመሳይ መለሰ እና ቢኒያም ታከለ አማካኝነት ሁለት ግልፅ የማግባት ዕድሎችን አግኝተው የተመለከትን ቢሆንም ግብ ጠባቂው ኮሰ ኩዊዝ መረቡን አላስደፍር ብሎ በአጋማሹ ውሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲቀጥል ተጫዋች በቀይ የወጣባቸው የማይመስሉት ጉለሌዎች ተደጋጋሚ ከጎል የሚያገናኛቸው ዕድሎች ያገኙት ቢሆንም ራስ ወዳድ በነበሩ አጥቂዎቻቸው ሲያመክኑ ውለዋል። ለዚህም ማሳያው ጨዋታው ሊጠናቀቅ አራት ያህል ደቂቃዎች እየቀሩ አትርሳው ተዘራ እና አምበሉ ጁንዴክስ አወቀ በቀላሉ ከመረብ የሚያገናኙትን ጨዋታ አለመጠቀማቸው ጨዋታው በመጨረሻም 0ለ0 ሊጠናቀቅ ግድ ብሏቸዋል።
የሳምንቱ የመጨረሻ የሆነው ጨዋታ ነቀምትን በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ላይ ያስቀመጠበትን ውጤት አስመዝግቦ ተጠናቋል። ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያስመለከተን ጨዋታው ጅምሩን ያደረገው ካፋ ቡናዎች ባስመዘገቡት የተጫዋች ተገቢነት ክስ የጀመረ ነበር። ካፋ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት ሽግግረሰ ለመጫወት በሞከሩበት እና ነቀምቶች በተሻጋሪ ኳሶች ጎሎችን ለማግኘት በጣሩበት ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በጭማሪው 45+1 ላይ ገዛኸኝ ባልጉዳ ከመስመር የተሻማለትን ኳስ አስቆጥሮ ነቀምትን ባለ ድል አድርጓል።
ምድብ ሐ
በቅድሚዬ ሶዶ ከተማ እና ገላን ከተማ ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ አጓጊ እና እልህ የቀላቀለ አጨዋወት የታየ ሲሆን በእንቅስቃሴ ረገድም ፈጣን እና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ አጋጣሚዎችን ተመልክተናል። ሶዶ ከተማዎች ኳስን ለገላን ከተማዎች ለቀው ወደ ኋላ በማፈግፈግ የተጫወቱ ሲሆን በአንፃሩ ገላን ከተማዎች ኳስን ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ለመድረስ ሲጥሩ ተስተውሏል። ይህን ተከትሎ በ11ኛው ደቂቃ ገላን ከተማዎች ከመስመር ያገኙትን ኳስ በማሻገር የኋላሸት ፈቃዱ ወደ ግብ በመቀየር መምራት የቻሉ ሲሆን በዚሁ ውጤት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የመለከትን ሲሆን በሁለቱም በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ተመልክተናል። በሶዶ ከተማ በኩል የሚያገኙትን ኳስ ግብ ለማስቆጠር ወደ ፊት ቶሎ ቶሎ ሲሄዱ በ66ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አላዛር ፋሲካ አስገራሚ ግብ አግብቶ ሶዶ ከተማን አቻ ማድረግ የቻለ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ገላን ከተማዎች በ68ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን የግብ ዕድል የኋላሸት ፍቃዱ ሁለተኛ ግቡን በማስቆጠር ዳግም ገላን ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በኋላ በ80ኛው ደቂቃ የሶዶ ከተማ የመስመር ተጫዋች የሆነው አማኑኤል ተስፋዬ የገላን ከተማ ግብ ጠባቂ መውጣት ተመልክቶ ከርቀት መቶ ግብ በማስቆጠር ሶዶ ከተማን አቻ ማድረግ ችሎ ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል።
በምድቡ በቀጣይነትየተደረገው የደሴ ከተማ እና ስልጢ ወራቤ ጨዋታ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ የስልጢ ወራቤ የበላይነት ታይቶበታል። በመሀል ክፍላቸው ጃፋር ሙደሲን እና ጥላሁን በቀለ ባሳዩት ፍሰት ባለው መልኩ የበላይነቱን በመውሰድ የተጫወቱ ሲሆን በተከላካይ ክፍሉም አልፎ አልፎ የሚመጣውን የደሴ ከተማ የግብ ሙከራ በብቃት በመከላከል ግብ እንዳይቆጠር ሲያደርጉ ተስተውሏል። በደሴ ከተማ በኩል ተስሏች ሳይመን እና የተከላካይ ክፍሉ የተሻለ የተንቀሳቀሱ ሲሆን ያገኙትን አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ታይቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ ስልጢ ወራቤዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ደሴ ከተማዎች ላይ ጫና ፈጥረው ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የተመለከትን ሲሆን ይህንን ተከትሎ በ50ኛው ደቂቃ ላይ ብሩክ ሰማ አክርሮ የመታት ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የወጣበት አስቆጪ አጋጣሚን ተመልክተናል። ብዙም ሳይቆይ በ52ኛው ደቂቃ ስልጢ ወራቤዎች ከመስመር ያገኙትን ኳስ በማሻገር ማታያስ ኤሊያስ በአስገራሚ ሁኔታ በጭንቅላቱ በመግጨት ወደ ግብ ቀይሮ ስልጢ ወራቤን መሪ ማድረግ ሲችል ከግቧ መቆጠር በኋላ ደሴ ከተማዎች የተወሰነ የመነቃቃት እና ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ የተመለከትን ቢሆንም ስልጢ ወራቤዎች ተቋቁመው ግብ ሳያስተናግዱ ጨዋታው ተጠናቆ ስልጢ ወራቤ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።
የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋርን ከሀምበሪቾ ዱራሜ አገናኝቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በሀምበሪቾ ዱራሜ በኩል የኋላ ደጀን የሆኑት እንዳለ ዮሐንስ እና ትእግስቱ አስፋው ጠንካራ የሆነ ጥምረት ግብ እንዳይቆጠርባቸው ያደረጉት ጥረት ተስተውሏል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል አሚር አብዲ እና ሙሉዓለም በየነ ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ኳሶችን ወደ ፊት መስመር ሲያደርሱ ተመልክተናል። ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ እና በግብ ሙከራ በኩል ሀምበሪቾ ዱራሜ ተሽለው የታዩ ቢሆንም በጅማ አባ ጅፋር ግብ ጠባቂ ድንቅ ብቃት ግብ ሳይቆጠር አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ተነቃቅተው የገቡ ሲሆን ሀምበሪቾ ዱራሜዎች የመሀል ሜዳውን የበለጡ እና በመሀል ሜዳ አቤል ዘውዱ እና ስንታየው አሸብር ድንቅ እንቅስቃሴ አድርገዋል። በ75ኛው ደቂቃ ሀምበሪቾ ዱራሜ በአንድ ሁለት ቅብብል ያገኙትን ኳስ በረከት ወንድሜ በድንቅ ሁኔታ በማስቆጠር ሀምበሪቾ ዱራሜ መሪ የሆነ ሲሆን ከግቧ መቆጠር በኋላ ጅማ አባ ጅፋሮች ግብ ለማስቆጠር የሞከሩ ቢሆንም ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው ተጠናቆ ሀምበሪቾ ዱራሜ ሶስት ነጥብ አሳክተዋል። ውጤቱን ተከትሎ ሀምበርቾ ዱራሜ የምድቡን መሪነት ነጥብ ከጣለው ገላን ከተማ መረከብ ችሏል።