ሪፖርት | የሁለቱ ቡናዎች ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

የሲዳማ ቡና እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ያለ ጎል 0ለ0 ተቋጭቷል።

ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ሲጋራ በተጠቀመው ስብስብ ላይ ለውጥ ያላደረገ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ከወልቂጤው ድል አንፃር በሁለት ተጫዋቾቹ ላይ ለውጥ አስፈልጎታል። በለውጡም ሬድዋን ናስር እና አንተነህ ተፈራ በአማኑኤል ዮሀንስን እና ብሩክ በየነ ተክተዋል።

\"\"

የሁለቱን ቡድኖች የጨዋታ ትግበራ ለመለየት ሀያ ደቂቃዎች ያህል ለመጠበቅ ተገደናል። ሲዳማ ቡናዎች ደቂቃዎችን ካጋመስን በኋላ የአማካይ ክፍል ተጫዋች ከሆኑት ፍሬው ሰለሞን እና ቴዎድሮስ ታፈሰ በሚነሱ እና ወደ ቀኝ የሜዳው ክፍል ወደ ተሰለፈው ጋናዊው አጥቂ ፍሊፕ አጃህ አማካኝነት በወጥነት የማጥቂያ ምንጫቸው አድርገው ወደ ተጋጣሚያቸው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ለመግባት ጥረቶች ሲያደርጉ አስተውለናል።

ከእንቅስቃሴዎች ውጪ በሙከራ ረገድ ያልደመቀው የቡድኖቹ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናዎች ከወትሮ የኳስ ቁጥጥር ግንኙነታቸው በተወሰነ መልኩ ራቅ ብለው በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሽግግር በተለይ ሦስቱን የፊት ተሰላፊ ተጫዋቾች ፍጥነታቸውን ለመጠቀም አልመው መንቀሳቀስ ቢችሉም ወጥነት የጎደለው አካሄዳቸው መስፍን ታፈሰ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ መቶ ጥራቷን የጠበቀች ኳስን ሞክሮ ፊሊፕ ኦቮኖ ከመለሰበት ውጪ የሲዳማን የተከላካይ ክፍልን ለማስከፈት ተቸግረዋል።


በአንፃሩ ሲዳማዎች የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ እና ከአማካይ ክፍላቸው ወደ አጥቂዎቻቸው መሬት ለመሬት በሚሾልኩ ኳሶች ሌላ የማጥቃት አማራጭን ለመጠቀም ቢዳዱም ኳስ እና መረብን ለማገናኘት አልታደሉም። አጋማሹ ሊገባደድ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ከማዕዘን ምት ከተሻሙ ኳሶች ኢትዮጵያ ቡናዎች ሁለት ጊዜ በመሐመድ እና መስፍን አማካኝነት ጥሩ ዕድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም ከፉክክር አንፃር የተቀዛቀዘ መልክን የተላበሰው አጋማሽ ጎልን ሳያስመለክተን ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በብዙ መልኩ ተሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ናቸው ፤ ኳስን ወደ ራሳቸው በማድረግ የቁጥጥር ድርሻ ብልጫውን ከወሰዱ በኋላ ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ጅምራቸው ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 48ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የአንድ ሁለት ቅብብል ከግራ ወደ ቀኝ ያቀበለውን መሐመድ ኑርናስር በፍጥነት ደርሶ አክርሮ የመታት ኳስ በላይኛው የግብ አግዳሚ ታካ ወጥታለች። በኢትዮጵያ ቡና በእንቅስቃሴ ይበለጡ እንጂ ሲዳማ ቡና ከተጋጣሚያቸው የሚነጠቁ ኳሶችን አሁንም በአጃህ አማካኝነት ለመጠቀም እና ግብን ለማግኘት ጥረት ከማድረግ ወደ ኋላ ባይሉም የሚያገኙትን ኳስ ግን በቀላሉ ያመክኗቸው ነበር።

\"\"

የሲዳማን የተከላካይ ክፍል በድግግሞሽ በጫላ ፣ መሐመድ ፣ መስፍን እና ብሩክ አማካኝነት ኢትዮጵያ ቡና በብርቱ ለማስከፈት ጥረት ማድረጋቸውን ቢያጠናክሩም በቀላሉ ወደ ሳጥን ሲደርሱ ደካሞች ነበሩ። ጫላ ነፃ ሆኖ ከቀኝ የሜዳው ክፍል የደረሰውን ኳስ ሞክሮ ከሳታት ከአምስት ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ 63ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የቅብብል ፍሰት መሐመድኑር ናስር ተቀይሮ ለገባው አብዱልሀፊዝ ቶፊክ አቀብሎት አማካዩ ከግቡ ትይዩ ካለው መስመር ጠርዝ ላይ በቀጥታ ወደ ጎል አክርሮ መቶ የላይኛው የግቡ ብረት መልሶበታል። በሲዳማ ቡና በኩል 87ኛው ደቂቃ ላይ ከራሳቸው የግብ ክልል በረጅሙ የተጣለን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ከግብ ጠባቂ ኢስቄል ሞራኬ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረው የምትጠቀሰዋ ሙከራ ነች። የጠሩ የግብ ሙከራዎችን እምብዛም ያላሳየን የሁለቱ ቡናማዎች ጨዋታም በስተመጨረሻም 0ለ0 ተቋጭቷል።


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ የመጀመሪያው አርባ አምስት ቡድናቸው በማጥቃቱ ረገድ የተሻለ እንደ ነበር ጠቁመው በሁለተኛው ግን የሰራነው ስራ ያን ያህል ባለ መሆኑ ከአማካይ እስከ አጥቂ ድረስ ተጋጣሚያቸው የተሻለ ሆኖ እንደ ተገኘ እና ቡድናቸውም የወረደ እንደ ነበር ከጠቁሙ በኋላ ለቀጣዩ የወልቂጤ ጨዋታ ተዘጋጅተን እንቀርባለንም ብለዋል። የኢትዮጵያ ቡና ጊዜያዊ አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በበኩላቸው በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ከተጋጣሚያቸው ያልጠበቁትን እንዳገኙ እና የመጫወቻ ሜዳ ነፍገዋቸው ሲጫወቱ እንደታዩ እንዲሁም ቡድናቸው ስህተትም ይሰራ እንደነበር ገልፀው በሁለተኛው አጋማሽ ግን የነበረባቸውን ስህተት አርመው ለመጫወት እንደሞከሩ እና በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ሲጫወቱ እንደቆዩ በንግግራቸው መግለፅ ችለዋል።