ዛሬ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ‘ሀ’ እና ‘ሐ’ ሰባት ጨዋታዎች ሲደረጉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ መሪነት ተመልሷል።
በጫላ አቤ
ምድብ ሀ
አሰላ ላይ በተደረጉ የዛሬ አራት ጨዋታዎች በድምሩ ዘጠኝ ግቦች ተቆጥረዋል። በቅድሚያ ረፋድ ላይ የተደረገው የቡታጅራ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል 0ለ0 ተጠናቋል። በመቀጠል የተደረገው የወልዲያ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻ ጨዋታ በበኩሉ አራት ግቦች ቢስተናገዱበትም ያለ አሸናፊ አቻ ተጠናቋል። ከመሪዎቹ ተርታ የሚገኘው ወልዲያ በቢኒያም ላንቃሞ እና በድሩ ኑርሁሴን አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥርም ለጨንቻ በፍቃዱ ሕዝቄል እና ገረሱ ገላዬ ያስቆጠሯቸው ግቦች በጊዜያዊነትም ቢሆን ሁለተኛ ደረጃን እንዳይዝ አድርጓል።
በዚሁ ምድብ ዱራሜ ከተማ በሰንዳፋ በኬ 2ለ1 ሲረታ በተጠባቂው የጅማ አባ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ደግሞ ባንክ 2ለ0 አሸንፏል። የንግድ ባንክን ግቦችም አቤል ማሙሽ እና አብዱለጢፍ ሙራድ አስቆጥረው ቡድኑ ዳግም መሪነቱን እንዲቆናጠጥ አስችለዋል።
ምድብ ሐ
የኮልፌ ክ/ከተማ እና ነጌሌ አርሲ ጨዋታ ድንቅ እንቅስቃሴ የተደረገበት እና አዝናኝ ጨዋታ የተመለከትንበት ሲሆን የነጌሌ አርሲ የመሀል ክፍል በዝነኛው ጋዲሳ እና በብሩክ ቦጋለ ጠንካራ ጥምረት ያለውና ኳሶችን ወደ ፊት የማሰራጨት እንቅስቃሴ ያለው ሲሆን በኮልፌ ክ/ከተማ በኩል ደግሞ በግብ ሙከራ እና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ነበሩ። በዚህ አጨዋወት በ10ኛው ደቂቃ ኮልፌ ክ/ከተማዎች ያገኙትን የግብ እድል ቃለጌታ ምትኩ በአስገራሚ ሁኔታ በማስቆጠር መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን ጨዋታውም ቀጥሎ በ42ተኛው ደቂቃ የነጌሌ አርሲው ግብ ጠባቂ አባቱ ጃርሶ ባልተገባ ቦታ ከፍተኛ ጥፋት በመስራቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። አጋማሹም ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል በነጌሌ አርሲ መሪነት አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ኮልፌ ክ/ከተማዎች ያገኙትን የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ተጠቅመው ግብ ለማስቆጠር ይበልጥ ተጭነው በማጥቃት የተጫወቱ ሲሆን በ50ኛው ደቂቃ ላይ ነጌሌ አርሲዎች ያሬድ መሐመድ ላይ በተሠራ ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ ቦጋለ በማስቆጠር አቻ መሆን ሲችሉ በ84ተኛው ደቂቃ ኮልፌ ክ/ከተማዎች ያገኙትን የግብ እድል የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ቃለጌታ ምትኩ ድጋሜ በማስቆጠር ኮልፌ ክ/ከተማን አሸናፊ ያደረገች ግብ አስቆጥሮ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው ተጠናቆ ኮልፌ ክ/ከተማዎች ጣፋጭ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።
በኦሜድላ እና ዳሞት ከተማ የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ፈጣን አጨዋወት እና ጥሩ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ ዳሞት ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ ፤ ኳስን ተቆጣጥረው በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክሩ በአንፃሩ ኦሜድላዎች በቻላቸው ቤዛ በመመራት በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ በ12ተኛው ደቂቃ ኦሜድላዎች ያገኙትን ኳስ ቢኒያም ጌታቸው ግብ በማስቆጠር ኦሜድላዎች መሪ መሆን ችለዋል። አጋማሹም በኦሜድላ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ዳሞት ከተማዎች ጫና ፈጥረው ግብ ለማስቆጠር ሲሞክሩ ኦሜድላዎች ሐይል ቀላቅለው ግብ እንዳይቆጠርባቸው በመከላከል በመልሶ ማጥቃት ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን ለመጨረስ ሲሞክሩ ነበር። ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ኦሜድላዎች ማሸነፋቸውን ያረጋገጡበትን ግብ በቻላቸው ቤዛ አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታውን አሸንፈው ጣፋጭ ሶስት ነጥብ አሳክተዋል።
የቡራዩ ከተማ እና የካ ክ/ከተማ የመጀመሪያው አጋማሽ ደግሞ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት አጋማሽ እና በኳስ ቁጥጥሩ የካ ክ/ከተማዎች ተሽለው የተገኙ ሲሆን በቡራዩ ከተማ በኩል ረጃጅም ኳሶች እና በመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ ተመልክተናል። ሆኖም ጥሩ ጥሩ የሚባል የግብ ሙከራዎችን የተደረጉ ቢሆንም ወደ ግብ ሳይቆጠር አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛ አጋማሽ የካ ክ/ከተማዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ተጭነው እና ግብ ለማስቆጠር በከፍተኛ ተነሳሽነት የተጫወቱ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በ68ተኛው ደቂቃ ላይ የየካ ክ/ከተማ የፊት መስመሩ ማቲያስ ሹመቴ ግብ በማስቆጠር የካ ክ/ከተማን መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን ከግቡ መቆጠር በኋላ ቡራዩ ከተማዎች ተነቃቅተው እና ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ ጨዋታውም በዚህ ሁኔታ በመቀጠል በ90ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ብስራት በቀለ ግብ አስቆጥሮ የየካ ክ/ከተማ አሸናፊነትን ያረጋገጠበት ሲሆን ጨዋታውንም የካ ክ/ከተማ ድል በማድረግ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።