መረጃዎች | 78ኛ የጨዋታ ቀን

ነገ በሚከናወኑት ሁለት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በሊጉ ሰንጠረዥ ግርጌ የሚገኙትን ቡድኖች ያገናኛል።

ዘንድሮ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊጉ አብረው ቢያድጉም በተመሳሳይ ሁኔታ የውድድር ዓመቱ የከበዳቸው ለገጣፎ ለገዳዲ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለተኛው ዙር መልካቸውን ቀይረው ለመምጣት ሞክረዋል። ሆኖም ግን መጠነኛ መሻሻል ያሳዩ እንጂ በፈለጉት ወጤታማነት ላይ አይገኙም። የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥር በመፈፀም የበርካታ አዳዲስ ፈራሚዎችን ወደ ስብስቡ ያመጣው ለገጣፎ ለገዳዲ በተለይም ድሬዳዋን በረታበት ጨዋታ ሦስት ነጥቦች እና ድንቅ ብቃት ቢያሳይም በቀጣዩ ጨዋታ አስደንጋጭ የሆነ የ7-1 ሽንፈት አስተናግዷል። ኢትዮ ኤሌክትሪክም በበኩሉ ባደረጋቸው ለውጦች ከቀደመው የተሻለ ተፎካካሪነትን ያሳይ እንጂ ከወላይታ ድቻው የአቻ ውጤት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አልቻለም።

\"\"

ለገጣፎ ለገዳዲ ሰፊ ሽንፈት ያስተናግድ እንጂ በመድኑ ጨዋታ የፈጠራቸው የግብ ዕድሎች ብዛት ትልቁ ጠንካራ ጎኖቹ ናቸው። የአዲሱ አጥቂው ሱለይማን ትራኦሬን የአጨራረስ ብቃት መልሶ ማግኘትም በእጅጉ ያስፈልገዋል። በኤሌክትሪክ በኩል ቡድኑ ለመተግበር የሚሞክረው የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን የማግኘት አኳኋን ፍጥነቱን መጨመር እና ተጋጣሚ ሜዳ ላይ በተሻለ ጊዜ እና ብልጫ ባለው ቁጥር መገኘት ትኩረቶቹ እንደሚሆኑ ይገመታል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከኮፊ ሜንሳህ ቅጣት በተጨማሪ የተስፋዬ ነጋሽ እና ዘነበ ከድርን ግልጋሎት ማግኘቱ አጠራጣሪ ሲሆን በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩልም የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት አብነት ደምሴ እና ጌቱ ኃይለማሪያም ከጨዋታው ውጪ ሆነዋል።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኛኙቡት ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-0 አሸናፊነት መጠናቃቁ ይታወሳል።

ጨዋታውን ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሀል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ዳዊት ገብሬ በረዳትነት ፣ ሙሉቀን ያረጋል በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አዳማ ከተማ

ምሽት ላይ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀመጫ ከተማው እየተጫወተ የሚገኘው አዳማ ከተማን የሚገጥምበት ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል።

ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅርብ ጨዋታዎች ድሎችን በቀላሉ እያገኘ አይደለም። በመጨረሻው ጨዋታ በሲዳማ ቡና ነጥብ መጣሉ ብቻ ሳይሆን ኢትዮ ኤሌትሪክን ሲያሸንፍ የገጠመው ፈተና ከዛ ቀደም የነበሩ ተከታታይ ጨዋታዎችንም በአንድ ግብ ልዩነት ብቻ ማሸነፉ ማሳያ ነው። እርግጥ ነው ተቸግሮም ቢሆን ማሸነፍ ከሊግ መሪ የሚጠበቅ ቢሆንም በተከታታይ መፈተኑ ጥሩ ምልክት ላይሆን ይችላል። በተመሳሳይ ተከታዮቹ እየቀረቡት መምጣታቸው እና በተለይም ባህር ዳር ከተማ ዛሬ አሸንፎ በነጥብ ዕኩያው መሆኑ ጊዮርጊስ የነገውን ጨዋታ በትኩረት እንዲመለከተው ያደርገዋል። በሜዳው የሚጫወት ቡድንንን እንደመግጠሙ መጠንም ብዙ ሳይቸገር መርታት ከቻለ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ጥሩ ትርጉም ያለው ድል ይሆንለታል።

አዳማ ከተማ ለወጣት ተጫዋቾቹ በሰፊቅ ዕድል እየሰጣ ባሳየባቸው ጨዋታዎች ጥሩ ውጤታማነት ታይቶበታል። ምንም እንኳን የሦስት ጨዋታዎች ተከታታይ አሸናፊነቱ በሀዋሳ ከተማ ቢገታም ቡድኑ ቀደም ብሎ ሲያሳይ የከረመው አቋም ለነገው ጨዋታ ስንቅ የሚሆነው ነው። በሀዋሳው ጨዋታ ጅማሮ አዳማ ይታይበት የነበረው ከፍ ያለ በራስ መተማመንም እንዲሁ ጠንካራ ጎን ተብሎ የሚወሰድ ቢሆንም ዕድሎቹን መጠቀም አለመቻሉ በሂደት ጨዋታውን አክብዶበት ለሽንፈት ተዳርጓል። ከነገ ተጋጣሚው ጥንካሬ አንፃርም ይህ ድክመት ከተደገመ ውጤት ሊያሳጣው እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

በጨዋታው የአዳማ ከተማ ወጣት አጥቂዎች በቀኝ ባመዘነው የቡድኑ ጥቃት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል። በተቃራኒው የቅዱስ ጊዮርጊስ ከፍ ባለ ጫና ጨዋታዎችን ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የመሰንዘር ልምድ እንዲሁም የእስማኤል ኦሮ አጎሮ የአጨራረስ ብቃት በተጠባቂው ፍልሚያ ከሊጉ መሪዎች የሚጠበቁ ነጥቦች ናቸው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት ሰፊ የበላይነት አለው። ከዚህ ቀደም 41 ጊዜያት የተገኛኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ 22 ጊዜ ሲያሸንፍ አዳማ ከተማ በአንፃሩ ሰባት ጊዜ ረቷል። አስራ ሁለቱ ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ናቸው።

በዚህ ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በዋና ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ለዓለም ዋሲሁን በረዳትነት ፣ ሶሬሳ ካሚል በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

\"\"