የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ – የሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጦች
የ2007 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ከተጀመረ 1 ወር እና የ4 ሳምንት ጨዋታዎች እድሜ አስቆጥሯል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም በአንዱ ወር ውስጥ (ከጥቅምት 16 እስከ ህዳር 16) ድንቅ ብቃታቸውን ያሳዩ ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ መርጣለች፡፡


ግብ ጠባቂ – ወንድወሰን አሸናፊ ( ሙገር ሲሚንቶ )


ወንድወሰን አሰግድ አክሊሉ ጥሎት የሄደውን ቦታ በሚገባ ሸፍኗል፡፡ የማይታመኑ ኳሶችን የማዳን ብቃቱ የአሰላውን ቡድን ከንግድ ባንክ እና ወልድያ ጋር ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አስችሎታል፡፡ በተለይም ከንግድ ባንክ ጋር ያሳየው ብቃት ብቻውን ከአመቱ ምርጥ አቋሞች አንዱ ያደርገዋል፡፡

ቀኝ ተከላካይ – ታከለ አለማየሁ (አዳማ ከነማ)

ታከለ ድንቅ የመስመር ተጫዋች ብቻ ሳይሆን ግብ አስቆጣሪም ጭምር ነው፡፡ ዘንድሮ ወደ ሊጉ ባደገው አዳማ ከነማ ውስጥ የሚጠቀስ ድንቅ ብቃት ያሳየ ሲሆን ሁለት ግቦችንም በዚህ ወር አስቆጥሯል፡፡ በቦታው የመከላከያው ሽመልስ ተገኝ ፣ የመብራት ኃይሉ አወት ገ/መድህን እና የባንኩ አዲሱ ካሳ በዚህ ወር ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳዩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ግራ ተከላካይ – አብዱልከሪም መሃመድ (ሲዳማ ቡና)


ይህ ወር ለሲዳማ ቡናው ፉልባክ ድንቅ ነበር፡፡ በይርጋለሙ ክለብ ያሳየውን ብቃት ተከትሎ ማላዊን የገጠመው ብሄራዊ ቡድን ቋሚ ተሰላፊ ሆኖ ተጫውቷል፡፡ ተፈጥሮአዊ ቦታው የቀኝ መስመር ተከላካይ ቢሆንም በግራ መስመር ላይም የተዋጣ እንቅስቃሴ ማድረግ ይችላል፡፡

የመሃል ተከላካይ – አቤል አበበ (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ)

የንግድ ባንኩ ተከላካይ የሃምራዊዎቹ መሪ ሆኗል፡፡ የቡድኑን የተከላካይ መስመር ሲመራና ከአጣሪው ቢንያም ሲራጅ እና ከፊቱ የሚገኘው ታዲዮስ ወልዴ ጋር ያለው መናበብ ድንቅ ነው፡፡

የመሃል ተከላካይ – አንተነህ ተስፋዬ (አርባምንጭ ከነማ)

የአርባምንጩ ተከላካይ ሊጉ ላይ ብዙም ግምት ካልተሰጣቸው ድንቅ ተከላካዮች አንዱ ነው፡፡ የአርባምንጭ ጠንካራ ጎን የሆነው የተከላካይ ክፍል መሪ ሲሆን ቡድኑ ዘንድሮ ያስተናገደው የግብ መጠን 1 ብቻ መሆኑን ከግምት ስናስገባ የአንተነህ እና ጓደኞቹን ጥንካሬ ምን ያህል እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ቀኝ አማካይ – እንዳለ ከበደ (ሲዳማ ቡና)

አምና ተዳክሞ የነበረው እንዳለ ዘንድሮ በአርባምንጭ የምናውቀው ብቃቱን ማሳየት ጀምሯል፡፡ እንደ አብዱልከሪም ሁሉ የአሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ጥሪ የደረሰውም በዚህ ወር ያሳየውን ብቃት ተከትሎ ነው፡፡

ግራ አማካይ – ታደለ መንገሻ (ደደቢት)

ድንቅ ክህሎትን የታደለው ታደለ መንገሻ ዘንድሮም ማንፀባረቁን ቀጥሏል፡፡ በብሄራዊ ቡድን
መደላደል ቢከብደውም አሁንም የደደቢት ሁነኛ የማጥቃት መሳርያ ነው፡፡

መሃል አማካይ – ዊልያም ኤሳድጆ (መብራት ኃይል)

በመብራት ኃይል በፍጥነት ተላምዷል፡፡ ከሲቲ ካፑ ጀምሮ የቀዮቹ ልዩነት ፈጣሪ መሆኑን የቀጠለ ሲሆን በዚህ ወር መብራት ኃይል በሊጉ ያስቆጠራቸውን ሁለቱንም ግቦች ከመረብ ያሳረፈውም ካሜሩናዊው ነው፡፡

አጥቂ አማካይ – አብዱልከሪም ሃሰን (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ)

የንግድ ባንኩ የአጥቂ አማካይ አሁን በፕሪሚር ሊጉ ከሚገኙ ድንቅ አማካዮች አንዱ ሆኗል፡፡ ‹‹ ምርምር ›› ሁለገብና በክህሎት የበለፀገ አማካይነቱን በአራቱ የንግድ ባንክ ጨዋታዎች ላይ አሳይቷል፡፡ በዚህ ወር በቀኝ መስመር ፣ በመሃል አማካይ እና ከአጥቂ ጀርባ ቦታዎች ላይ የተሰለፈው አብዱልከሪም ከሳሚ ሳኑሚ ቀጥሎ በእስካሁኑ ጨዋታዎች ኮከብ ተጫዋች ነው፡፡

አጥቂ – ፊሊፕ ዳውዚ (ኢትዮጰያ ንግድ ባንክ)

አምና ጥሩ የውድድር አመት ያሳለፈ ሲሆን ዘነድሮ ደግሞ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ግብ የማስቆጠር አቅም እንዳለው እያሳየ ነው፡፡ ዳውዚ በብቸኛ አጥቂነት የሚሰለፍ ሲሆን እስካሁን 3 ግቦች አስቆጥሮ

አጥቂ – ሳሚ ሳኑሚ (ደደቢት)

በመብራት ኃይል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀኝ መስመር አማካይነት እና የመስመር አጥቂነት የምናውቀው ሳሚ ሳኑሚ ዘንድሮ በፊት አጥቂነት ለማቆም አስቸጋሪ ተጫዋች ሆኗል፡፡ በ3 ጨዋታዎች በእያንዳንዳቸው ላይ ሁለት ግቦች ያስቆጠረ ሲሆን ከቦታው ጋር ለረጅም ጊዜ የሚተዋወቅ መስሏል፡፡

የጥቅምት/ ህዳር ወር ኮከብ ተጫዋች – ሳሚ ሳኑሚ (ደደቢት)

ካለጥርጥር የዘንድሮ ክስተት ነው፡፡ በደደቢት የተመለከትነው በሲቲ ካፑ እና በ3 የሊግ ጨዋታዎች ላይ ብቻ ቢሆንም አጀማመሩ አስፈሪ ነው፡፡ እስካሁን በ3 ጨዋታ 6 ግቦች ያስቆጠረ ሲሆን በዚህ አካሄዱ ከቀጠለ የዮርዳኖስ አባይን ሪኮርድ በሰፊ ግቦች ልዩነት መስበሩ የማይቀር ነው፡፡

የጥቅምት / ህዳር ወር ኮከብ አሰልጣኝ – ንጉሴ ደስታ (ደደቢት)

ደደቢት ከአምና ደካማ አቋሙ እንዲያገግም አሰልጣኙ ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ ደደቢት እስካሁን ቀላል ተጋጣሚዎች በማግኘቱ የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥን ለመቆናጠጥ እንደበቃ የሚከራከሩ ቢኖሩም የንጉሴ ደስታ የዘንድሮ ደደቢት በብዙ መልኩ ተሻሽሏል፡፡ በቀላሉ ግቦች ቢቆጠሩበትም ግብ ለማስቆጠር አይቸገርም፡፡
አሰልጣኙ አምና በመስፍን ኪዳኔ ላይ የተገበሩትን ውጤታማ ውሳኔ ዘንድሮ በሳሚ ሳኑሚ ላይ ደግመው የበለጠ ውጤታማ ሆነውበታል፡፡ ሁለቱም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሲመጡ የመስመር አማካይ የነበሩ ቢሆንም ንጉሴ ደስታ ወደ ግሩም አጥቂነት ለውጠዋቸዋል፡፡

ያጋሩ