ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ወደ አሸናፊነት ተመልሰዋል

በመቀመጫ ከተማቸው እየተጫወቱ የሚገኙትን አዳማ ከተማዎች የገጠሙት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ ከተለያየበት ስብስብ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርጓል። በዚህም ምኞት ደበበ፣ ሔኖክ አዱኛ እና ቸርነት ጉግሳ አርፈው አማኑኤል ተርፉ፣ ሱሌይማን ሀሚድ እና ዳዊት ተፈራ ወደ ሜዳ ገብተዋል። በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ የተሸነፉት አዳማ ከተማዎችም የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ጨዋታውን ቀርበዋል። በለውጦቹም መስዑድ መሐመድ፣ አዲስ ተስፋዬ እና አሜ መሐመድ የአማኑኤል ጎበና፣ ደስታ ዮሐንስ እና ቢኒያም አይተንን ቦታ ተክተዋል።

\"\"

አዳማ ከተማ በመጀመሪያው ደቂቃ ቦና ዓሊ ከቀኝ መስመር የተሻማን ኳስ አብርዶለት መስዑድ መሐመድ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ባደረገው ሙከራ ወደ ግብ መድረስ ችሏል። ቡድኑ የቅዱስ ጊዮርጊስን የኳስ ምስረታ ሂደት ከጅምሩ በማፈን ዕሎችን ለመፍጠር ሲሞክር በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ይህንን ጫና ወደ ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በሚጥሏቸው ረጅም ኳሶች በማለፍ አደጋ በመፍጠር ምላሽ መስጠትን መርጠዋል። 15ኛው ደቂቃ ላይም ቅዱስ ጊዮርጊሶች በራሳቸው በኩል የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ከቆመ ኳስ ሰንዝረዋል። በዚህም ኳስ በእጅ በመነካቱ ሳጥኑ ጫፍ የተገኘውን የቅጣት ምት ቢኒያም በላይ ሞክሮት ለጥቂት ወጥቶበታል።


ጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር ማስመልከት የቀጠለው ጨዋታው በ28ኛው ደቂቃ እጅግ የሰላ ሙከራ አስተናግዶ መሪ ሊያገኝ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም አዳማዎች ተጭነው የተቀበሉት ኳስ የደረሰው ዮሴፍ በጠንካራ ምቱ ወደ ግብ ቢልከውም የግብ ዘቡ ቻርለስ ሉክዋጎ መልሶታል። አጋማሹ ምንም እንኳን ተደጋጋሚ የጠሩ የግብ ሙከራዎች ባይበረክቱበትም ለዐይን ማራኪ ፍልሚያ አስመልክቶ ያለ ግብ ተጠናቋል።


ሁለተኛው አጋማች እንደተጀመረ አዳማ ከተማዎች በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ጥሩ ዕድሎችን በመስዑስ አማካኝነት ፈጥረው ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። በቅድሚያ ተጫዋቹ ለቦና ጥሩ ዕድል ፈጥሮ ሉክዋጎ ሲያከሽፈው ሁለተኛውን ደግሞ ጀሚል ተረክቦ ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ዮሴፍ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያላደረጉት ጊዮርጊሶች በ51ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም አዳማዎች የተሳሳቱትን ኳስ እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ለአቤል ያለው አቀብሎት ፈጣኑ አጥቂ ረጅም ርቀት በመግፋት ከመረብ ጋር አገናኝቶታል።

ወደ መሪነት የተሸጋገሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። አዳማ ከተማዎች በተቃራኒው በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ብልጫ ቢወሰድባቸውም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ማድረጋቸውን ተያይዘዋል። ይህ ቢሆንም ግን በ71ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። በዚህም ቢኒያም ከርቀት ከራር ኳስ መትቶ ለጥቂት ተጨርፎ ወጥቶበታል። ተጨርፎ የወጣው ኳስ ከመዓዘን ሲሻማ ግን ግቡ አልቀረም። እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ከመዓዘን የተሻማው ኳስ በሚገባ መፅዳት ሳይችል ቀርቶ ደርሶት በጉልበቱ ነክሮ መረብ ላይ አሳርፎታል።


አዳማዎች ሁለተኛውን ግብ ካስተናገዱ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በቀሪ ደቂቃዎች ተስፋ እንዲሰንቁ ያስቻላቸውን ግብ ዳንኤል ደምሴ በማራኪ ሁኔታ አስቆጥሮላቸዋል። ከዚህ ግብ በኋላ ቡድኑ በአንፃራዊነት የተነቃቃ የማጥቃት አጨዋወት ቢሰነዝርም አቻ አልፎም ድል ለማግኘት የነበረው ውጥን አልሰመረም ፤ ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ አሠልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የዛሬው ሦስት ነጥብ እጅግ አስፈላጊ እንደነበር ተናግረው በከባዱ ጨዋታ ያሳኩት ድል እንዳስደሰታቸው እና ከነጥብ መጋራት በፊት የነበራቸውን ሪትም ማስቀጠላቸው ጥሩ እንደሆነ ጠቁመዋል። አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው ሁለቱም ጎሎች የተቆጠሩት በራሳቸው ስህተቶች እንደሆነ ጠቁመው በቡድናቸው ብዙም እንደማይከፉ በማንሳት ብዙ እያደገ የሚሄድ ነገር እንዳለ ተናግረዋል።