መረጃዎች | 79ኛ የጨዋታ ቀን

በዕለተ ፋሲካ የሚደረጉ የ19ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ሁለት ጨዋታዎችን እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ወላይታ ድቻ

በአሥራ ሦስት ነጥቦች እና በስምንት ደረጃዎች ተበላልጠው 3ኛ እና 11ኛ ላይ ያሉትን ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻን የሚያገናኘው ጨዋታ መድኖች ከዋንጫ ፉክክሩ ላለመራቅ ድቻዎች ከናፈቁት ድል ጋር ለመታረቅ ጥሩ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከተከታታይ ድል የተመለሱት ኢትዮጵያ መድኖች በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ቢገኙም በሊጉ ሰባተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (25) ማስተናገዳቸው እና ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ መረባቸውን ሳያደፍሩ መውጣት አለመቻላቸውን በጊዜ ካላስተካከሉ ለዋንጫው በሚያደርጉት ግስጋሴ እክል ሊፈጥርባቸው ይችላል። ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት ግቦች ብቻ ያነሱ 37 ግቦችን ማስቆጠር የቻሉት መድኖች በሊጉ አራተኛውን የግብ መጠን (16) ካስተናገዱት እና ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ካላቸው ወላይታ ድቻዎች ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ያስቀጥሉታል ወይ የሚለው ይጠበቃል።
\"\"
በመጨረሻ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድም ድል ያላሳኩት እና ማግኘት ከነበረባቸው 18 ነጥቦች 4 ነጥብ ብቻ ያገኙት የጦና ንቦቹ በሊጉ ከለገጣፎ ለገዳዲ (13) በመቀጠል ሁለተኛውን ዝቅተኛ የግብ መጠን (14) ያስቆጠሩ መሆናቸው ፊት መስመራቸው ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ይጠቁማል። ባደረጓቸው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ ቅድሚያ ግብ ማስቆጠር ቢችሉም በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩባቸው ግቦች በፋሲል ከነማ የ 2-1 ሽንፈት ሲገጥማቸው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በነገው የመድን ጨዋታም ሜዳ ላይ ከሚያሳዩት እንቅስቃሴ በተጨማሪ በአዕምሮም ዝግጁ ሆነው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ ተገናኝተዋል። እኩል አንድ አንድ ጊዜ ተሸናንፈው በአንዱ አቻ ተለያይተዋል። በሦስቱ ግንኙነትም ድቻ ሦስት መድን ደግሞ አንድ ግብ አስቆጥረዋል።

መቻል ከ ፋሲል ከነማ

በአንድ ነጥብ እና በሦስት ደረጃዎች ተበላልጠው 10ኛ እና 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን መቻል እና ፋሲል ከነማን የሚያገናኘው የምሽቱ መርሐግብር ሁለቱም ቡድኖች ባለፈው ሳምንት ካስተናገዱት ሽንፈት ለማገገም ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በድሬዳዋ የመጨረሻ ቆይታቸው አስደናቂ ለውጥ ማሳየት ችለው የነበሩት መቻሎች በአዳማ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ግን ሽንፈት አስተናግደዋል። በመጨረሻ ባደረጓቸው 6 ጨዋታዎች 12 ግቦችን ያስተናገዱት መቻሎች በየጨዋታው የሚፈጥሯቸውን በርካታ የግብ ዕድሎች ካለመጠቀማቸው በተጨማሪ በራሳቸው ሳጥን ውስጥ ጠንካራ አለመሆናቸውንም ቁጥሮች ይጠቁማሉ። በነገው ጨዋታም  ሦስት ደረጃዎችን የሚያሻሽሉበትን ድል ለማሳካት ከፋሲል ከነማ ጋር ጠንካራ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
\"\"
ካለፉት 10 ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ መርታት የቻሉት ፋሲል ከነማዎች በአራቱ አቻ ወጥተው በአራቱ ሽንፈት አስተናግደዋል። ይህም ውጤትም የክለቡን ደጋፊዎች ያስደሰተ አይደለም። ከባህርዳር ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታም እስከ ዕረፍት መምራት ቢችሉም የኋላ የኋላ በተቆጠረባቸው ሁለት ግብ ለመሸነፍ ተገደዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣት ያልቻሉት ዐጼዎቹ በነገው ዕለትም በአንድ ነጥብ ብቻ ከሚበልጡት መቻል የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል አይሆንም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለአስር ጊዜያት የተገኙ ሲሆን ፋሲል ከነማዎች በአምስቱ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖራቸው መቻሎች ደግሞ ሦስቱን ረተዋል ፤ የተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች በበኩላቸው በአቻ ውጤት የተፈፀሙ ናቸው።