ሪፖርት | ጥሩ ፉክክር በታየበት ጨዋታ መድን እና ድቻ ነጥብ ተጋርተዋል

በዕለተ ፋሲካ የተደረገው የኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በድንቅ የሜዳ ላይ ፉክክር በአራት ግቦች ታጅቦ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ በ18ኛ ሳምንት ከተጫወቱበት ስብስብ በተመሳሳይ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ለገጣፎ ለገዳዲን 7ለ1 ያሸነፈው መድን ሀቢብ ከማልን በኪቲካ ጅማ ሲተካ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ተጋርቶ የነበረው ድቻ ደግሞ ያሬድ ዳዊትን በደጉ ደበበ ለውጧል።

\"\"

ጨዋታው ገና በተጀመረ በሰላሳ ሰከንዶች ውስጥ ወላይታ ድቻዎች እግጅ በጣም ወርቃማ ዕድል ፈጥረው ነበር። በዚህም የመድኑ አማካይ ባሲሩ ዑመር የተሳሳተውን ኳስ ዘላለም አባተ በፍጥነት ግብ ለማድረግ ቢሞክረውም የግብ ዘቡ አቡበከር ኑሪ አምክኖታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ መድኖች ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ፈጣን ምላሽ በባሲሩ አማካኝነት ሰንዝረው በተመሳሳይ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ መልሶባቸዋል።

ገና ከጅምሩ ፈጣን እንቅስቃሴ ያስመለከተው ጨዋታው በ7ኛው ደቂቃ ግብ አስተናግዶ መሪ ሊያገኝ ነበር። በዚህም በረከት ወልደዮሐንስ ብሩክ ሙሉጌታ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ሀብታሙ ሸዋለም መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። ባመከኑት ዕድል ብዙም ያልተበሳጩት መድኖች ከየአቅጣጫው ሌሎች ሙከራዎችን ለማድረግ ሞክረዋል። 21ኛው ደቂቃ ላይ ግን ወላይታ ድቻዎች ግብ አስቆጥረውባቸዋል። በዚህም በሚገርም የማጥቃት ሂደት ቃልኪዳን ዘላለም ከአበባየሁ ዮሐንስ የተረከበውን ኳስ በጥብቅ ምት ከመረብ ጋር አገናኝቶታል።


ጨዋታውን በሚፈልጉት መልኩ እየከወኑ የሚገኙት ወላይታ ድቻዎች ምንም እንኳን በጣም የበለጠ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ባይወስዱም በድብልቅ አጨዋወት የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ የተሻሉ ነበሩ። መድኖች በአንፃሩ እንደ ከዚህ ቀደሙ ጨዋታውን መቆጣጠር ባይችሉም በቻሉት መጠን የአቻነት ጎል ፍለጋቸውን ተያይዘዋል። በ35 እና 37ኛው ደቂቃም ከቆመ ኳስ እና ከክፍት ጨዋታ ጥሩ ዕድል ፈጥረው ተመልሰዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ግን ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም ቻላቸው መንበሩ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ በግንባሩ ግብ አድርጎታል። አጋማሹም አንድ አቻ ተጠናቋል።


በሁለተኛው አጋማሽ የታመመውን የአማካይ መስመራቸው ለማከም የተጫዋች ለውጥ ያደረጉት መድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ለማጥቃት ሲጥሩ ነበር። በ51ኛው ደቂቃም ከእንቅስቃሴ ባለፈ ለውጣቸው ፍሬ አፍርቶ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። ዮናስን ለውጦ የገባው ወገኔ ጥሩ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ወደፊት ልኮ 8 ቁጥር መለያ ለባሹ ብሩክ የውድድር ዓመቱን 8ኛ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ደጉ ደበበ የተሳሳተውን ኳስ ሲሞን ፒተር ሦስተኛ ጎል ሊያደርገው ተቃርቦ ነበር።


የእንቅስቃሴም ሆነ የጎል ብልጫ የተወሰደባቸው ወላይታ ድቻዎች በ56ኛው ደቂቃ በአበባየሁ ዮሐንስ አማካኝነት የአጋማሹን የመጀመሪያ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል። አሠልጣኝ ፀጋዬ ዳግም በጨዋታው ህይወት ለማግኘት የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች አከታትለው አስገብተዋል። በ68ኛው ደቂቃም እንደ መድን ለውጣቸው ፍሬ አፍርቶ አቻ ሆነዋል። በዚህም በፈጣን መልሶ ማጥቃት ስንታየሁ ያስጀመረውን ኳስ ሀብታሙ ለሌላኛው ተቀይሮ የገባው አጥቂ ዮናታን ኤሊያስ አመቻችቶለት ፈጣኑ አጥቂ በግራ እግሩ ግብ አስቆጥሯል። በቀሪ ደቂቃዎች ሌላ የጠራ የግብ ዕድል ሳይፈጠር ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ ምክትል አሠልጣኝ ለይኩን ታደሠ ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ገልፀው ቡድናቸው በተለይ በተከላካይ ክፍሉ ላይ ስህተቶችን ሲሰራ እንደነበርና ወላይታ ድቻዎች ስህተቱን እንደተጠቀሙበት ተናግረዋል። በጨዋታው መምራት ቢችሉም ማስጠበቅ እንዳልቻሉ ሲናገሩ ተደምጠዋል። የወላይታ ድቻው አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው ከጠንካራ ቡድን ጋር እንደተጫወቱ ጠቁመው በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር እንዳደረጉ እና ከሌላ ጊዜው በተለየ የተሻለ ለማጥቃት እንደሞከሩ በማስረዳት የአቻ ውጤቱ ፍትሀዊ እንደሆነ አመላክተዋል።